1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያ በጅቡቲ የወደብ ሽርክና ጠየቀች

እሑድ፣ ሚያዝያ 21 2010

ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር በሽርክና ወደብ ለማልማት ጥያቄ ማቅረቧን፤ በጅቡቲ መንግሥት በኩልም አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቷን አንድ ከፍተኛ ዲፕሎማት ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ አየር መንገድ እና ቴሌኮም በመሳሰሉ ተቋማት እና የመሰረተ-ልማት ግንባታ ዘርፎች ጅቡቲ በሽርክና እንድትሠራ መስማማቱ ተገልጧል።

Dschibuti Hafen
ምስል DW/J. Jeffrey

የኢትዮጵያ መንግሥት ከጅቡቲ ጋር በሽርክና ወደብ ለማልማት ጥያቄ አቀረበ። ጥያቄው የቀረበው ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በጅቡቲ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ወቅት ነው። በጅቡቲ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ አዴቦ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ጉዳዩ «በይፋ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰፊው የተጠየቀ እና በሁለቱ መሪዎች ደረጃ ንግግር የተደረገበት» ነው። አምባሳደሩ የወደብ ሽርክና ጉዳይ «ቀደም ሲል አልታሰበም» ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ምኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ «በጅቡቲ ውስጥ ያሉ ወደቦች በለሙትም አዲስ በሚለሙት ውስጥም» ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ሁለቱ አገሮች መግባባታቸውን ተናግረዋል። 

የጅቡቲ መንግሥት «ኢትዮጵያ በምታካሒዳቸው ማንኛውም መሰረተ-ልማት ይሁን የአገልግሎት መንግስታዊ የልማት ድርጅቶች በጠቅላላ በሚኖር ስምምነት መሰረት ኢንቨስት እንድታደርግ» ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል። 

ከአዲስ አበባ ጋር በባቡር የትራንፖርት አገልግሎት የተሳሰረችው ጅቡቲ ለኢትዮጵያ የገቢ እና የወጪ ንግድ ዋንኛ ማመላለሻ ሆና ታገለግላለች። የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች እንደሚሉት 97% የኢትዮጵያ ገቢ እና ወጪ ሸቀጥ የሚጓጓዘው በጅቡቲ ወደብ በኩል ነው። አገሪቱ የሱዳን እና የበርበራ ወደቦችን በአማራጭነት መጠቀም ብትጀምርም በጅቡቲ ወደብ በኩል ያለውን ጫና ማቃለል አልቻሉም። የኢትዮጵያ መንግሥት 30 በመቶ የገቢ እና ወጪ ሸቀጦችን በበርበራ 10 በመቶውን ደግሞ በሱዳን ወደብ በኩል ለመከወን እቅድ አለው። አምባሳደር ሻሜቦ «ኢትዮጵያ የጋራ ወደብ ከጅቡቲ ጋር ብታለማ የባለቤትነቱ ጉዳይ ይጠነክራል ተብሎ ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ደግሞ ሁለቱን አገሮች ይበልጥ ያስተሳስራቸዋል» ሲሉ ፋይዳውን አስረድተዋል።

ምስል picture-alliance/Photoshot/Xinhua/S. Ruibo

አምባሳደሩ እንዳሉት ጥያቄው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌሕ በሚመሩት የጅቡቲ መንግሥት በኩል አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌሕ ጉዳዩ «ሊፈለግ በሚችል ጊዜ ፈጥኖ እንዲፈጸም» አቅጣጫ ማስቀመጣቸው የተናገሩት አምባሳደር ሻሜቦ ኢትዮጵያ ባለድርሻ የምትሆነው በነባር ይሁን አዲስ ወደብ ላይ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም ብለዋል። የጥያቄውን ዝርዝር ጉዳይ የሚመለከት ኮሚቴ መቋቋሙንም አክለው ገልጸዋል። «አዲስ ወደብ መገንባት ይሁን ነባር ወደቦች ላይ ድርሻ የማግኘት ይሁን በቀጣይ ከሁለቱ ወገኖች የተውጣጡ ኮሚቴዎች ምክረ-ሐሳብ የሚያቀርቡበት ነው» ብለዋል።

ኢትዮጵያ በምትኩ ለጅቡቲ አየር መንገድ እና ቴሌኮምን ከመሳሰሉ ተቋማት የተወሰነ ድርሻ ለጅቡቲ መንግሥት ለመስጠት ፈቃደኝነት አሳይታለች። አምባሳደር ሻሜቦ የተቋማቱን ዝርዝርም ይሁን ለጅቡቲ ሊሰጥ የሚችለውን የድርሻ መጠን አልገለጹም። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ በጅቡቲ ጉብኝታቸው ባደረጉት ውይይት «ከፈለጉ በአየር መንገድ ከፈለጉ በቴሌኮም የተወሰነ ድርሻ እንዲኖራቸው የተገለጸ ጉዳይ ስላለ በዝርዝር የሚሰራ ነው የሚሆነው» ሲሉ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌሕ በውይይታቸው ሶማሊያ እና ጅቡቲን ጨምሮ በአካባቢው ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ አዴቦ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  ጠቅላይ ምኒስትሩ በጅቡቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ንግግር ያደረጉ ሲሆን የጅቡቲን ወደብ እና የዱራሌሕ ግዙፍ ጭነት ማስተናበሪያ ጎብኝተዋል። ኢትዮጵያ ከጥቂት ወራት በፊት ዲፒ ወርልድ በሚያስተዳድረው የበርበራ ወደብ 19 በመቶ ባለድርሻ መሆኗ አይዘነጋም።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW