1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እስክንድር፣ አንዷለም እና ኡስታዞቹ ከፍቺ በኋላ

ረቡዕ፣ የካቲት 7 2010

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው መሠረት በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የነበሩ 746 ታራሚዎች እና ተጥርጣሪዎች ዛሬ ከእስር ተለቅቀዋል፡፡ ዛሬ ከተፈቱት ውስጥ አንዷለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ አህመዲን ጀበል እና አህመድ ሙስጠፋ ይገኙበታል።

Äthiopien Kaliti Gefängnis
ምስል Befekadu Hailu

እስክንድር፣ አንዷለም እና ኡስታዞቹ ከፍቺ በኋላ

This browser does not support the audio element.

የቀድሞው አንድነት ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ አመራር የነበሩት እና ላለፉት ስድስት ዓመት ከአምስት ወር በእስር የቆዩት አንዷለም አራጌ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ከሚገኘው የፌደራል ማረሚያ ቤት ሲወጡ አካባቢው በጩኸት ተናጠ፡፡ ከማረሚያ ቤት ደጃፍ የተሰበሰቡት ሰዎች «አንዷለም ጀግና» በሚል ቃል ፖለቲከኛውን ሲያውድሱ ተደምጠዋል። ከአንዷለም ጋር አብሮ የተፈታውን እስክንድር ነጋን በትከሻቸው ተሸክመው ሲጨፍሩም ተስተውለዋል። የመኪናቸውን ጡሩንባ እያስጮኹ ደስታቸውን ሲገልጹ የነበሩም በርካቶች ነበሩ። 

ምስል Befekadu Hailu

ከእስር ከወጡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ከዶይቼ ቬለ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ አንዷለም የህዝቡ አቀባበል «ከአቅማቸው በላይ» መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከአንዷለም ጋር በአንድ መዝገብ በሽብር ወንጀል ተከስሰው 18 ዓመት ተፈርዶባቸው የነበሩት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም ተመሳሳይ ሀሳብ አለው፡፡ የህዝቡ ስሜት የሚያመላክተው «የዲሞክራሲው ጥያቄ እየበሰለ፣ ውጤት ለማምጣት ጫፍ ላይ መድረሱን ነው» ይላል።  

ከእነ እስክንድር ቀደም ብለው ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት የወጡት አራት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እና አጋሮቻቸውም በማረሚያ ቤት ደጃፍም ሆነ በመንገድ ታጅበው ሲጓዙ ባጋጠማቸው አቀባበል መደነቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ኮሚቴውን በዋና ጸሐፊነት ሲያገለግሉ የነበሩት እና 15 ዓመት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የቆዩት ኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋ ሁኔታውን «በጣም ስሜት የሚነካ» ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ሃያ ሁለት ዓመት ተፈርዶባቸው የነበሩት የኮሚቴው የሕዝብ ግንኙት ኃላፊ ኡስታዝ አህመዲን ጀበልም ለህዝቡ መስተንግዶ ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው። «መጀመሪያውኑ ምንም አድርገን ስላልታሰርን እስር ቤት ብንሆንም እስረኛ አልነበርንም። ያው አሰሩን፤ ፈቱን ነው» ሲሉ ስለእስራቸው እና ፍቺያቸው ተናግረዋል።

ምስል DW/Y. G. Egziabher

እነ አንዷለም እና የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ዛሬ ከእስር ከመለቀቃቸው አስቀድሞ በቀረበላቸው የይቅርታ ደብዳቤ ላይ «አልፈርምም» በማለታቸው በቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ዘንድ ጭንቀትን ፈጥሮ ነበር፡፡ ዛሬም ከእስር ሲወጡ «የይቅርታ የምስክር ወረቀት እንደተሰጣቸው ነገር ግን በምንም ሰነድ ላይ አለመፈረማቸውን» ሁሉም ጠንከር አድርገው ገልጸዋል፡፡ ኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋ ሂደቱን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።  

የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት እነርሱን ጨምሮ 746 ታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች በሁለተኛው ዙር ከእስር መለቀቃቸው ምን አንደምታ እንዳለው የተጠየቁት ፖለቲከኛው አንዷለም እርምጃው «በጎ ጅምር ነው» ይላሉ፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር የእስረኞች ፍቺ «አንድ እርምጃ ወደፊት ነው። ግን መቋጫው አይደለም» ባይ ነው፡፡ 

ቀድሞ በቅንጅት ፓርቲ በስተኋላ በቀድሞው ለአንድነት ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ በአባልነት እና አመራርነት ለረጅም ዓመታት በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ የቆዩት አቶ አንዷለም ስለወደፊት እቅዳቸው ተጠይቀው «በሰላማዊ ትግል እንደሚቀጥሉ» ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ምስል Befekadu Hailu

በእስር ላይ ባለበት ወቅት በርካታ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኝነት እና የሰብዓዊ መብት ሽልማቶች የተበረከቱለት ጋዜጠኛ እስክንድር ወደ ሙያው እንደሚመለስ ተናግሯል፡፡ ኡስታዝ አህመድ በበኩላቸው ወደፊት የሚያከናውኗቸውን ተግባራት «ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብረን የምንማከር ይሆናል» ብለዋል፡፡ 

ዛሬ ቃሊቲ ከሚገኘው የፌደራል ማረሚያ ቤት ከእስር ከተፈቱት ውስጥ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ኦኬሎ አኳይ፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር ኦልባና ሌሊሳ፣ ፖለቲከኛ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)፣ ናትናኤል መኮንን እና ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ እንደዚሁም ድምጻዊት ሴና ሰለሞን ይገኙበታል፡፡ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬም ከዝዋይ ማረሚያ ቤት መፈታቱ ታውቋል፡፡  

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።   

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW