ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ-ራስ ገዝ የመሆን ጉዞ
ሐሙስ፣ ግንቦት 28 2017
የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ የማገልገል ቀጣይ ተልዕኮ ከተሰጣቸው ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ሀረማያ ዩኒቨርሲቲበቀጣዮቹ ዓመታት ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ለመሥራት የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ዐሳውቋል ።
ወደ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲነት ለሚደረገው ጉዞ አንዱ የራስን የፈይናንስ ምንጭ ማመንጨት መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ኢስሀቅ በምርምር እና ሌሎች መስኮች በዚህ ረገድ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ለዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢስሀቅ ዩሱፍ ዩኒቨርሲቲው ለምርምር የሚውለውን ሰባ አምስት በቶ ያህል የበጀት ምንጭ በራሱ ማመንጨት መጀመሩን ተናግረዋል።-
በሀገሪቱ በቀጣይ ተልዕኳቸው የምርምር ተቋማት ተብለው ከተለዩ ስምንት ያህል ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በመንግስት የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት የተለያየ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢሳቅ ዩሱፍ ተናግረዋል።
አንጋፋ ከሚባሉ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ሀረማያ ከአራት ዐሥርተ ዓመታት በላይ የካበተ ልምድ ያካበተበት ግብር እና የጤናው ዘርፍ ቀጣይ ትኩረቶቹ መሆናቸው ተገልጿል ።
የተሰጠውን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ አሁን ያለውን የማህበረሰብ ብዛት እና ሌሎችነባራዊ ሁኔታዎች ትኩረት መስጠት አለበት ያሉት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ኢማና ጌቱ ናቸው።
ለዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት ፕሮፌሰር ኢማና ዩኒቨርሲቲው ዓላማውን ለማሳካት በቀጣይ ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማኅበረሰብ በሚሰጣቸው የተለያዩ ድግፎች እና አገልግሎቶች ዙርያ የሚወያይበት እና በአመቱ የተሰሩ የምርምር ስራዎች የሚቀርብበትን መድረክ ዘንድሮ ለአርባ ሁለተኛ ጊዜ አካሂዷል ።
መሣይ ተክሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ