1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሀኑካ አዲስ አበባ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ በአደባባይ ላይ ተከበረ

ሐሙስ፣ ጥር 4 2015

ሀኑካ አዲስ አበባ ላይ በድምቀት ተከበረ። የእስራኤላዊያን አይሁዶች የድል መታሰቢያ እና የተዓምር በዓል ነው። ቤተ እስራኤላዊያን ለመጀመርያ ጊዜ በአደባባይ በአዲስ አበባ ዉስጥ አክብረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ቤተ እስራኤላዊያን በተለይም በጎንደር፣ በትግራይ የተወሰኑ አካባቢዎች፣ በወሎ ፣ በሰሜን ሸዋና አዲስ አበባ ይኖራሉ።

Äthiopien Addis Abeba | Chanukka Feier
ምስል፦ Mesfin Assefa

ጎንደር ፣ ደቡብ ትግራይ ፣ በተወሰነ የጎጃም ክፍል እንዲሁም ሰሜን ውሎ ቤተ-እስራኤላዉያን ይኖራሉ

This browser does not support the audio element.

ሀኑካ የእስራኤላዊያን አይሁዶች የድል መታሰቢያ እና የተዓምር በዓል ነው። ጥንታዊ የግሪክ ነገስታት እስራኤላውያንን ለመደምሰስ እና የአይሁድ ሃይማኖታቸውን በማስለወጥ የጣዖት አምልኮን እንዲቀቡሉ በኃይል በወረራ የጫነባቸውን ጦርነት ከመከቱ በኋላ ይህንን ድል ታሳቢ በማድረግ ሀኑካ የተባለውን በመቅረጽ ብርሃንን ለሌሎች ማሳየት በሚቻልበት ሁኔታ ሻማን በማብራት የሚያከብሩት በዓል ነው።ቤተ- እስራኤላዉያን ሻናቶቫ

በሌላ በኩል ግሪኮች የአይሁድ ቤተ መቅደሶችን ተቆጣጥረው ስለነበር እስራኤላዊያኑ ያንን ወረራ ከቀለበሱና ከድላቸው በኋላ ቤተ መቅደሶችን ለማንፃት በሚል በወቅቱ መቅደሶቹ ውስጥ ይበራ የነበረን ዘይት ሲፈልጉ ለአንድ ቀን ብቻ ማብራት የሚችል አንድ ገንቦ ዘይት ማግኘታቸውን ታሪካቸው ይናገራል።

ቤተ-እስራኤላዉያን የሀኑካን በዓል ሲያከብሩምስል፦ Mesfin Assefa

ይህ ለአንድ ቀን ያበራል ተብሎ ታስቦ የነበረው ዘይት ለ ስምንት ተከታታይ ቀናት በማብራቱና እንደ ተዓምር በመታመኑ ይህንን የታሳቢ በማድረግ በአንድ በኩል ታምራቱን፣ በሌላ በኩል ግሪክን ድል ያደረጉበትን በማሰብ ጭምር የሀኑካን በዓል እስራኤላውያን ያከብሩታል።

የሀኑካ በዓል በእስራኤላዊያን አይሁዶች በየ ቤቱ ለሻማ መለኮሻ በተዘጋጀ መሀል ላይ እንድ መለኮሻ ያለው ባለ ስምንት ማብሪያ መቅረዝ በመስራት በየእለቱ ለ ስምንት ተከታታይ ቀናት በዋናነት ሻማ እንዲበራ ይደረጋሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በዓሉ አይሁዶች ባሉበት ዓለም ሁሉ አደባባይ መከበር ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ቤተ እስራኤላዊያን በተለይም በጎንደር፣ በትግራይ የተወሰኑ አካባቢዎች፣ በወሎ ፣ በሰሜን ሸዋና አዲስ አበባ ይኖራሉ።

እነዚህ ቤተ እስራኤላዊያን የአይሁድ እምነት ተከታዮች ሀኑካ የተባለውን በዓላቸውን ለመጀመርያ ጊዜ በአደባባይ በአዲስ አበባ ባለፈው ሳምንት አክብረዋል።ቤተ-እስራኤላዉያን እስራኤል ገቡ

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታላቁ ንጉሥ እስክንድር የግሪክን ጦር አዝምቶ እስራኤልን ጨምሮ ሌሎች የመካከላኛው ምስራቅ ሀገራትን በኃይል አስገብሮ እንደነበር ከትውልድ እስከ ትውልድ መጽሐፍ ላይ ሰፍሯል።

ይህ ታላቅ ንጉሥ ካረፈ በኋላ ግን በክንዱ ሥር የነበረው ግዛት ተበታትኗል። ሆኖም እሱን ተከትሎ በተተከለው ስርወ መንግሥት በአካባቢው የነበሩ ሕዝቦች በቁጥጥሩ ሥር መሆናቸው ግን አልቀረላቸውም። በራሱ ሥርዓትና ወግ፣ አምልኮ እንዲተዳደሩም አስገደዳቸው። ይህንን ተከትሎ የአይሁድ አምልኮ ሥነ ሥርዓቶች ማለትም ሰንበትን መጠበቅ፣ ግርዛት፣ የኦሪት ጥናት ፣ የቤተመቅደስ አገልግሎቶችን መከወን ክልከላ ተጣለባቸው። ጥንት በአይሁዶች ዘንድ ይከናወን የነበረው የአምልኮ ልማድ ቆሞ በግሪክ አማልክቶች እና አሳማን ለመስዋእትነት በማቅረብ ልማዶች ተተኩ። ብዙ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ይህንን ሲቀበሉ በዚያው ልክ አንቀበልም ብለው ጦር መማዘዙን ያዙ። ከብዙ ትግል በኋላም አሸንፈው ያንን የራሳቸውን ማንነት ይገልፃል ያሉትን ሥርዓት መመለስ ቻሉ።

በዚህ ምክንያት ሀኑካ በየ ዓመቱ በቤት ውስጥም በአደባባይም ይከበራል በማለት በኢትዮጵያ የቤተ እስራኤላዊያንን ጉዳይ በተመለከተ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉት አቶ መስፍን አሰፋ አጫውተውናል።

"ሀኑካ በአይሁድ እምነት ከሚደረጉ ታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓሎች አንዱ ትልቁ በዓል ነው። ይህን በዓል ለየት የሚያደርገው ሃይማኖታዊ ይዘት ስላለው ነው። ሀኑካ ማለት መቀደስ፣ መመረቅ ማለት ነው"

የአይሁድ እምነት ተከታይ እስራኤላውያን ሀኑካን በሚያከብሩበት ጊዜ ቤቶቻቸውን በልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ይሞላሉ። የዚህ ማህበረሰብ አባላት በምድረ በዳ ተበትነን ነበር ባሉበት ጊዜ በነበራቸው የሚንቀሳቀስ የአምልኮ ቤተ መቅደስ ውስጥ የእጣን ማጨሻ ፣ ለዳቦዎች ማስቀመጫ የሚሆን ጠረንጼዛ እና ሜሮን የተባለው ቁስ እንደነበራቸው ተጽፏል።

ሀኑካ ክብረ በዓል በአዲስ አበባ ምስል፦ Mesfin Assefa

"በየ ቀኑ ማታ ማታ ሃይማኖታዊ ፀሎት አለ። ፀሎት ከተደረገ በኋላ ምግብም፣ መጠጥም ለልጆች ይቀርባል" ዋናው ከሀኑካ ጋር የተያያዘው የበዓሉ የአከባበር ሥርዓት ስምንት ሻማዎችን በሚያበራው ሜኖራህ ወይም በቀጥተኛ መስመር እኩል የተሰራ የማብሪያ መቅረዝ ላይ ሻማን ማብራት ነው። በየ ዓመቱ በታኅሣሥ መጨረሻ እና በጥር ወራቶች መጀመሪያ ላይ ለስምንት ተከታታይ ቀናት ብርሃኑ ለሌሎች እንዲታይ ሆኖ ሻማዎች ይበራሉ። ጥንት በአይሁድ ቤተ መቅደሶች ውስጥ ይበራ የነበረውን የወይራ ዘይት ተምሳሌት በማድረግ ዛሬ ድረስ የወይራ ዘይት እንደ አስፈላጊነቱ ጥቅም ላይ ይውላል።

በኢትዮጵያ የቤተ እስራኤላዊያንን ጉዳይ በተመለከተ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉት አቶ መስፍን አሰፋ ይህን ሥነ ሥርዓት ሁሉም እድሜ እና ሌላ ደረጃ ሳይለየው አይሁዶች ያከብሩታል ብለዋል።

ቤተ እስራኤላዊያን በኢትዮጵያ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ማለትም ከንግሥት ሳባ እና ንጉሥ ሰሎሞን ግንኙነት በኋላ በስፋት ኖረዋል፣ አሁንም አሉ። በተለይ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር በጉልህ ተሰባጥረው ይኖራሉ።ቤተ-እስራኤላዉያንና የሊቀ- ራባናቱ እወጃ

በደርግ ውድቀት እና በኢህአዴግ መግቢያ ሰሞን በዘመቻ ሙሴ እና በዘመቻ ሰሎሞን በተለይ ከጎንደር እና አካባቢው በርካቶች ቤተ እስራኤላዊያልን የጽዮናዊነት ንቅናቄው አካል ሆነው እስራኤል ገብተዋል።

እንዲያም ሆኖ ግን የአይሀድ የአምልኮ ሥርዓታቸውን በተለይም ሀኑካን አቶ መስፍን አሰፋ እንደሚሉት አዲስ አበባ ላይ በአደባባይ ሲያከብሩ 2015 ዓ.ም የመጀመርያቸው ነው።

"ጎንደር ፣ ደቡብ ትግራይ ፣ የተወሰነ የጎጃም ክፍል ፣ ሰሜን ውሎ አካባቢ የሚኖሩ ቤተ እስራኤሎች አሉ። አብዛኞቹ በአሁኑ ሰዓት እስራኤል ገብተዋል። ከ 150 ሺህ በላይ የሰሜኑ አካባቢ ቤተ እስራኤላዊ እዛ ገብተዋል። የተወሰኑ ተበታትነው ሰሜን ሸዋ ውስጥ የቀሩ ገና እውቅና ለማግኘት እየሰሩ አሉ"

ሀኑካ በተከታታይ በሚከበርባቸው እለታት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ምንባቦች ይቀርባሉ። ይህ ክብረ በዓል በአደባባይ መከበር ከጀመረ ( በተለይ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ባሉባቸው አውሮጳና አሜሪካ አካባቢዎች ) ግማሽ ምእተ ዓመት እያለፈው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን ሊጎበኝ፣ ሊታይ፣ ብዙዎችን ሊስብና ሊያሰባስብ የሚችል በዓል ሆኖ ማየት የቤተ እስራኤላዊያኑ ኢትዮጵያውያን መሻት ነው።የመኖርያ ፈቃድ ለፈላሻሙራ ቤተ-ዘመዶች

"አይሁድ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን ለሎሎችም በማስተዋወቅ ቀጣይ አመታዊ ፊስቲባል እንዲሆን ለሚቀጥለው አመት አቅደን እየሰራን እንገኛል" በማለት አቶ መስፍን ገልፀዋል።

በመጨረሻም በኢትዮጵያ የቤተ እስራኤላዊያንን ጉዳይ በተመለከተ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉትን አቶ መስፍን አሰፋ የቤተ እስራኤላዊያኑ አኗኗር፣ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የነበራቸውና ያላቸው ግንኙነት፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በሃይማኖትና በባህል ያላቸው ትስስር እና ቁርኝት ምን መሳይ ነው? ብለን ጠይቀናቸዋል።

ሀኑካ አዲስ አበባ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ሲከበርምስል፦ Mesfin Assefa

"በአሁኑ ሰዓት የእስራኤል መንግስት በግማሽ እውቅና ሰጥቷቸው እየተጠባበቁ ያሉ ወደ አሥር ሺህ የሚጠጉ ወደ እስራኤል ለመሄድ በተለይ በጎንደርና በአዲስ አበባ ላይ የተቀመጡ አሉ። ከዚያ ውጪ ባደረግነው ቆጠራ በመላው ኢትዮጵያ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ቤተ እስራኤላዊ ገና እውቅና ያላገኘ ፣ ገና ወደ ማንነቱ እየተመለሰ ያለ ቤተ እስራኤላዊ እንዳለ ይገመታል። ቤተ እስራኤላዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው መኖር ከጀመሩ ከሦስት ሺህ ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። እስራኤላውያን ከተሰሰዱባቸው ሀገሮችም አንዷ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ናት።

በማናቸው በእምነት፣ በፖለቲካብ፣ በኢኮኖሚ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር እኩል ነው የኖሩት። ስለዚህ እስራኤልና ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ሀገሮች ናቸው" ብለዋል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW