ሀገራዊ መፍትሔ አፈላላጊ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም “ኢትዮጵያን የማዳን መድረክ” ጥሪ አቀረበ
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 20 2016
የፍኖተ ካርታው አዘጋጆች፣ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያና በውጭ ሃገራት የስራ ልምድ ያካበቱ፣ በትምህርት ደረጃም በየዕርከኑ በቂ ዕውቀትና ስልጠና ያላቸው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ የሚካሄደው የእርስ በርስ እልቂትና መዘዞቹን በመረዳትና የሃገሪቱን መጻኢ ዕድል ምን ሊሆን እንደሚችል በስጋት በማሰብ፣ ሰነዱን ለማዘጋጀት መነሳታቸውን በበይነ መረብ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል።
ባለፉት 63 ዓመታት ያህል በጥፋት ላይ ጥፋት የነበረው ጉዞ፣ ኢትዮጵያን ለከፋ ችግር እንደዳረጋት፣የመድረኩ አባል ዶክተር ሰለሞን ወልደአብ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አስረድተዋል።
"የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግሮች ህገ መንግስታዊ፣ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ናቸው ነው የሚባሉትና እነዚህን እድሎች ሲያመልጡ፣ምን ሊቀይሩ መጥተው ምን አመለጠ የሚለው ነገር የዚህ ሰነድ አዘጋጆች፣በራሳቸው እነዚህ ናቸው ያመለጡ አንኳር አንኳር ዕድሎች ናቸው በማለት ለማቅረብ ሞክረዋል" ሲሉ ዶክተር ሰለሞን ተናግረዋል።
ለአካታች መንግስት ምስረታ ያመለጡ ዕድሎች በማለት፣ዶክተር ሰለሞን ከጠቀሷቸው መኻከል፣የ2010-2011 ዓ.ም ሕዝባዊ አመጽ፣የ1997 ምርጫ፣በ1983 የተደረገው የመንግስት ለውጥና በ1966 የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ ይገኙባቸዋል።
ኢትዮጵያ አሁን በተጋረጡባት ፈተናዎች፣ እንደ ሀገር እንዳትጠፋ ማድረግ አለብን ያሉት ሌላው የመድረኩ አባል ዶክተር አቻምየለህ ደበላ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኝበትን ሁኔታ አብራርተዋል።
በሃገሪቱ አሁን የሚታየው ነባራዊ ሁኔታ፣በዚሁ ከቀጠለ ሊሆኑ ስለሚችሉ አደጋዎች ዶክተር አቻምየለህ "መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች ለድርድር ዝግጁ ሳይሆን ከቀረ፣ ሰላማዊ የሆነው መንገድ ሁሉ ተዘግቶ፣ችግሮችን በጦርነት ብቻ ለመፍታት የሚደረገው ሙከራ ይቀጥላል።ህዝቡም ውጊያውን በስንቅና በሚችለው ይተባበራል። በአጭሩ መቶ ሺህ በሚሆነው መከላከያ ላይ ከ30 እና 40 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ጋር ይገጥማል ማለት ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ የመጨረሻ ውጤት ይፋ ሆነ
ፍኖተ ካርታውን ያዘጋጁት የመድረኩ አባላት፣ ኢትዮጵያን ከአስከፊ ሁኔታ ለማዳን፣የሃገራዊ መፍትሄ አፈላላጊ ግብረ ኀይል ምስረታን በመፍትሔነት አቅርበዋል። በአሜሪካ ሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ "ግብረ ሃይሉ የሚሰራው ወደመጨረሻው ላይ፣ ሰላማዊ የሆነ በህዝብ የተመረጠ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ማቋቋም ነው።ከዚያ በፊት ግን የሃገራዊ መፍትሄ አፈላላጊ ግብረ ኀይሉ ሁሉንም አሳታፊ በሆነ መልኩ ይሰበሰብና አንድ የስድስት ወር ጊዜ ተሰጥቶት በእዛ ውስጥ ሁኔታዎችን በየፈርጁ እያስቀመጠ መፍትሄ እየፈለግለት ይሄዳል" ብለዋል።
ለዚህ ሃገራዊ ጥሪ የኢትዮጵያ መንግስት አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ የጠየቁት የመድረኩ አባላት፣ያን አለማድረግ ማለት በታሪክ የሚያስጠይቅ ከመሆኑም በላይ ሃገሪቱን ለከፋ ችግርና አደጋ መዳረግ መሆኑን አመልክተዋል። ስለፍኖተ ካርታው ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተያየት ለማግኘት ጥረት ብናደርግም ለጊዜው ምላሽ አላገኘንም።
ታሪኩ ኃይሉ
እሸቴ በቀለ