1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልሎች አጀንዳ ማሰባሰብ ሊጀምር ነው

ረቡዕ፣ ሐምሌ 10 2016

ችግር ውስጥ ባለው በአማራ ክልል ይህ ሥራ በሌሎች ክልሎች ከተከናወነ በኋላ የጦርነቱ እና ግጭቱ ሁኔታ ሲስተካከለ እንሄድበታለን ያሉት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ ከጦርነት ማግስት በሚገኘው በትግራይ ክልል ግን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን ጀምሩ የሚል ማረጋገጫ ሲሰጠን ለመግባት ዝግጅት ጨርሰናል ብለዋል።

Äthiopien Kommission für den nationalen Dialog
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልሎች አጀንዳ ማሰባሰብ ሊጀምር ነው

This browser does not support the audio element.

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በሦስት ክልሎች እና አንድ ከተማ አስተዳደር በተመሳሳይ ጊዜ አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ ሊጀምር ነው።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ የሚጀመረውን አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ ለማከናወን ከዛሬ ጀምሮ የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች መሰማራት ጀምረዋል ተብሏል።

በአማራ ክልል ይህንን ሥራ ለማከናወን የጦርነት ሁኔታውን ማብቃት እንደሚጠብቅ ያስታወቀው ኮሚሽኑ፣ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ማረጋገጫ ሲሰጥ ሥራውን ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን፣ በአፋር አሁን ከፍተኛ ሙቀት ያለ በመሆኑ ጥቅምት መግቢያ ላይ ሥራው እንደሚጀመር  ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተናግረዋል።

የኮሚሽኑ የቀጣይ ሥራዎች ምንድን ናቸው?

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሦስቱ ክልሎች እና በድሬዳዋ የሚያደርገውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ እስከ ነሐሴ 30 ለማጠናቀቅ ውጥን ይዟል። ችግር ውስጥ ባለው በአማራ ክልል ይህ ሥራ በሌሎች ክልሎች ከተከናወነ በኋላ የጦርነቱ እና ግጭቱ ሁኔታ ሲስተካከለ እንሄድበታለን ያሉት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ ከጦርነት ማግስት በሚገኘው በትግራይ ክልል ግን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን ጀምሩ የሚል ማረጋገጫ ሲሰጠን ለመግባት ዝግጅት ጨርሰናል ብለዋል።

የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያምስል Solomon Muchie/DW

ሃምሳ ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ ጋር አብረው እየሠሩ ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ ይሁንና ኮከስ በሚባለው ስብስብ ውስጥ ያሉ "ተጽእኖ ፈጣሪ" ያሏቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች "አሁንም ከእኛ ጋር እየሠሩ አይደለም" ብለዋል። ከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ያሉትን በተመለከተም ዛሬም ጥሪ አድርገዋል።

ይህ የምክክር ሂደት በአዋጅ ከተሠጠው የሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ዓመት ከአምስት ወራት ያህሉን እስካሁን ሠርቶበታል። በሥራው ላይ ከገለልተኝነት ጀምሮ እስከ የመሳካት እድሉ ድረስ ብዙ ጥያቄዎች ይነሱበታል፣ ሥጋቶችም ይንፀባረቁበታል። ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የሚሉት ግን ከዚህ ተቃራኒውን ነው።

የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሚደናቀፍባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች 

ምስል Solomon Muchie/DW

ኮሚሽኑ "የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሚደናቀፍባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድናቸው"? ሲል ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው የጽሑፍ መግለጫ "በተለያዩ ቡድኖች መካከል እጅግ ሰፊ የሆነ የኃይል አለመመጣጠን ሲኖር እና "የገነገኑ" ያላቸው ኃይሎች አቅማቸውን ተጠቅመው የሀገራዊ ምክክሩን አቅጣጫ የማስቀየር አዝማሚያ ሲያሳዩ፤ በምክክር ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና ሊኖራቸው የሚችሉ ባለድርሻ አካላት በአግባቡ ተደራጅተው ሀሳባቸውን ማቅረብ ሳይችሉ ሲቀሩ፤ አንዳንድ ባለድርሻ አካላት እና ቡድኖች በሀገራዊ ምክክሩሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝቅተኛ ተነሳሽነት ሲያሳዩ ወይም ለመሳተፍ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ እና የምክክሩ ሂደት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ የሆነ የግዜ ጫና ሲያጋጥም" የሚሉት ናቸው ብሏል። ኮሚሽኑ ይህንን ያለው የምክክር ሂደቱ ሊሳካ የማይችልበት አዝማሚያ አለ ማለቱ ይሆን? በሚል ላቀረብነው ጥያቄ ከሌሎች ምክክር ካደረጉ ሀገሮች በጥናት ላይ ተመስርቶ የወጣ እንጂ የመግለጫው መነሻ ከኢትዮጵያ 
እንዳልሆነ ኮሚሽነር አምባሳደር ሙሐሙድ ድሪር ምላሽ ሰጥተዋል።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአጀንዳ ልየታ ወቅት ተወካዮች በሚያነሱት ሀሳብ ምንም አይነት ጉንተላ እና ችግር እንደይደርስባቸው የማረጋገጫ ዋስትና እንደሚሰጥ ከዚህ በፊት አስታውቋል። በክልሎች በሚደረገው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ሀሳብን ከመግለጽ ጋር ተያይዞ ጫና እና ማሸማቀቅ እንዳይኖር ኮሚሽኑ የሚያደርገውን ክትትል በተመለከተ የተጠየቁት የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች፣ ዜጎች አካባቢያዊ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ገዳዮችን ጭምር  ያነሱ እንደሆን እንጂ በዚህ ሂደት ምንም አይነት ሥጋት አይኖርም ብለዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ

  

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW