ሀገራዊ የምክክር ሂደት እና በጀርመን የኢትዮጵያውያን ስጋት
ዓርብ፣ ግንቦት 30 2016
በኢትዮጵያ በተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ላይ ስጋት እንዳላቸው በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተናገሩ፡፡
ለተሳካ የምክክር ሂደት እና ውጤት መፍትሄ ያሏቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ከተመሰረተ ከሁለት ዓመታት በኋላ በአዲስ አበባ ደረጃ ቀዳሚውን የምክክር መድረክ በማካሄድ አንድ ያለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከጅማሮው ስጋቶች እና ጥያቄዎች እየተነሱበት ነው።
ለዶቸ ቬሌ አስተያየታቸውን የሰጡ በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉት፣ በምክክር ሂደቱ ላይ ስጋት አላቸው።
የፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት የአለማቀፍ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ልዑል ዶ/ር አስፋወሰን አስራተ ካሳ በኢትዮጵያ የሚደረግ ምክክርም ሆነ ድርድር በሀገሪቱ ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ ካልሆነ ጥቅም የለውም ይላሉ።፧
መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ሀገራዊ ምክክር
“ኢትዮጵያ ውስጥ ያለፉትን ሰላሳ ዓመታት ሕዝባችን እርስ በእርሱ እንዲተላለቅ ያደረገው ምንድነው ብለን መጀመሪያ ራሳችንን ስንጠይቅ፥ የዚህ ሁሉ በሽታ፣ የዚህ ሁሉ ጣጣ መንስኤ ይኼ የአፓርታይድ ሕገ መንስግት ነው። እሱን ለመለወጥ እስካልተቻለ ድረስ የምናደረገው ነገር ሁሉ ከንቱ ነው።”
የድርጅቴን አቋም ሳይሆን የግል ኃሳቤን ነው የምናገረው ያሉት ዶ/ር አስፋወሰን፣ አሁን በአገራዊ ምክክር ስም ለማካሄድ የሚሞከረው የፖለቲካ ጨዋታ ነው ሲሉም ወቅሰዋል።
“ይኼ ለማታለያ እና ሰዉን ወደ ሌላ ሁኔታ ለመለወጥ የወጣ አስተሳሰብ ነው እንጂ፥ ለዚህ ላለንበት ትልቅ ፕሮብሌም [ችግር] መፍትሄ ይሆናል ብሎ የወጣ እንዳልሆነ ማንም የፖለቲካ ተንታኝ ወዲያው ሊያየው ይችላል። ይኼን ፈረንጆቹ ምን ይሉታል - ‘ፖለቲካል ጊሚክ’ ይሉታል እንዲህ ዓይነቱን፤ ጨዋታ ማለት ነው።”
የፖለቲካል ኢኮኖሚ ባለሙያ እና ደራሲው ዶ/ር መስፍን ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ የምክክር ሂደቱ መጀመር በእጅጉ አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን የአካታችነት ጉዳይ ትልቁ ስጋት ነው ይላሉ።
“ከአካታችነት አንጻር የሚነሱ ስጋቶች አሉ። ምክንያቱም ተመሳሳይ ኃሳብ ያላቸው ሰዎች ብቻ ተወያይተው የሚያመጡት መፍትሄ የጋራ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ የእርስ በእርስ ጦርነት ባለበት፣ እየተዋጉ ያሉ ኃይሎች አሉ፤ እነሱን ወደ ውይይት መድረክ ማቅረብ ባልተቻለበት ሁኔታ ፍሬያማ የሆነ ውጤት ላትጠብቅ ትችላለህ።
በአገራዊ ምክክሩ ላይ የዳያስፖራውን ተሳትፎ በተመለከተ ከአባላት እና ደጋፊዎቼ ጋር ውይይት አደርጋለሁ ያለው፣ የኢትዮጵያዊያን የውይይት እና ትብብር መድረክ በጀርመን ሊቀ መንበር አቶ አፈወርቅ ተፈራ ደግሞ፣ የምክክር ሂደቱ ተጠናቆ የሚቀርቡ ምክረ-ሃሳቦችን መንግስት ይተገብራቸዋል ወይ?” የሚለው ትልቅ ጥያቄ እንደሆነ ይናገራሉ።
“የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አገራችን ውስጥ አሉ የሚባሉትን ችግሮች በሙሉ ባለድርሻ አካላት አወያይቶ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመንግስት ለመጠቆም መምጣቱን ሰምተናል። እነኚህ የሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦችን መንግስት ተቀብሎ ስራ ላይ ለማዋል ምን ያልህ ቁርጠኛ ነው የሚለው ነገር እስካሁን ድረስ ያለ ያለ ጥያቄ ነው።”
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓመተ ምሕረት በአዋጅ ተቋቁሞ ስራ ከጀመረ አንስቶ በሂደቱ አንሳተፍም ያሉ የታጠቁ ቡድኖች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ እልባት አልተበጀለትም። አንዳንድ የታጠቁ ኃይሎች ከመንግስት ጋር በቀጥታ የመደራደር ኃሳብ ማቅረባቸውም ይታወቃል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ኃሳባቸውን የሰጡት ዶ/ር አስፋወሰን አስራተ ካሳ፥ በተለይ በአማራ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት መንግስት በቀጥታ ከፋኖ ኃይል ጋር በሶስተኛ ወገን አደራዳሪነት ንግግር መጀመር እንዳለበት ነው የሚናገሩት።
“ቀጥታ ከፋኖ ድርጅት ጋራ በሶስተኛ ሰው አማካይነት በውጭ አገር መድረክ ተፈጥሮ መነጋገር ውስጥ መግባት አለባቸው ብዬ ነው የማምነው። በኦነግ ሸኔ ተሞክሮ አልነበረም ታንዛኒያ ላይ? ታዲያ የአማራው ሁኔታ ከኦነግ ሸኔ ሁኔታ ያነሰ ነው ብለን በማሰብ ነው?”
“የምክክሩ ሂደት ውጤቱን ይወስናል” የሚሉት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር መስፍን ሙሉጌታ በበኩላቸው፥ ውክልና የለንም የሚሉ ወገኖችን ማካተት ካልተቻለ ውጤቱ ያማረ አይሆንም ይላሉ።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለታጣቂዎች ያቀረበው የሰላም ጥሪ ምን ላይ ደረሰ?
“እስካሁን በተሄደበት አካሄድ ያልተወከሉ የፖለቲካ ኃይሎች ይኖራሉ የሚል ስጋት አለኝ። እነሱን ደግሞ ያላካትተን ከሆነ ውጤቱም ያማረ ሊሆን እንደማይችል ከውዲሁ መገመት ይቻላል የሚል እምነት ነው ያለኝ።”
እንደ ዶ/ር መስፍን ገለጻ፥ የምክክር ኮሚሽኑ ስራ የተሳካ እንዲሆን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን ማሳተፍ በእጅጉ ያስፈልጋል።
መሳይ ወንድሜነህ
ታምራት ዲንሳ
ሸዋዬ ለገሰ