ሀገር አቀፍ የተማሪዎች ፈተና መጀመር
ሰኞ፣ ሰኔ 3 2011በተለያዩ ክልሎች የፈተናው አሰጣጥ ሂደት የተጀመረ ሲሆን በተለይ በትግራይ ክልል በተረጋጋ ሁኔታ ፈተናው እየተካሄደ መሆኑን ከመቀሌ ዘጋቢያችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ የላከል ዘገባ ያስረዳል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ እንደገለፀው ዘንድሮ በትግራይ ክልል 223 ሺህ ተማሪዎች ሀገራዊ እና ክልላዊ ፈተና ይወስዳሉ። ከነዚህ መካከል 89 ሺህ ተማሪዎች የአስረኛ ክፍል ተፈታኞች ናቸው።
የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳኘው አይጠገብ ፈተናው በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ከፌደራል ትምህርትና ምዘና ሴክተር መሥርያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የፀጥታ አካላትና ሌሎች ጋር ሲሰራ መቆየቱ ገልጸዋል።
አብዛኛው አካባቢው በኮማድ ፖስት ሥር የሚገኘው ቤንሻንጉል ክልልም የዘንድሮው የሀገር አቀፍ ፈተናዎች በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ነው። በግጭቶች ምክንያት ከትምህርት ጊዜያቸው ዘግይተው የጀመሩ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዝግጅቱ ተጠናቆ እየተፈተኑ እንደሆነ ከአሶሳ ዘጋቢያችን ነጋሳ ደሳለኝ በላከው ዘገባ ገልጿል። በተለይም በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች የሚገኙ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ዛሬ ፈተና መጀመራቸው ነው የተገለፀው።
በአማራ ክልልም ፈተናው መሰጠት መጀመሩ ቢነገርም፤ ከ7ሺህ በላይ ተማሪዎች ከዛሬ ጀምሮ የሚሰጡትን የ10ኛ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎች እንደማይፈተኑ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል። ወላጆች እና ተማሪዎች በምዕራብ ጎንደርና ማዕከላዊ ጎንደር ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች ምክንያት ተማሪዎቹ ትምህርት ማቋረጣቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ በመላው የክልሉ አካባቢዎች ፈተናው በመልካም ሁኔታ እተካሄደ እንደሆነ አመልክተዋል። ይህ በእንዲህ አንዳለ በቅርቡ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ካነጋገራቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሰው መሆን አበረና የሺወርቅ አዘናው በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ትምህርት ማቋረጣቸውን፣ ለፈተናም እንደማይቀመጡ ገልጸውለታል።
የተማሪ ወላጆችም መንግሥት ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ሚያደርገው ጥረት መልካም ቢሆንም የትምህርት ተቋማትን በማደረጀት ትምህርት እንዲቀጥሉ ማድረግ እንዳለበት በጭልጋ ወረዳ የጉንትር ቀበሌ ነዋሪ አቶ ስጦታው ክብረት ተናግረዋል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ እንዳረጋገጡት በወቅቱ በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸውና በመፈራረሳቸው ከ3ሺህ በላይ የሚቆተሩ የ10ኛና የ12ኛ ተማሪዎች አይፈተኑም።
በተመሳሳይ በቀጣይ ሳምንት ለሚካሄደው የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናም በተመሳሳይ 3,400 ያህል ተማሪዎችም እንደማይፈተኑ ነው ምክትል ቢሮ ኃላፊው የተናገሩት። በአማራ ክልል 804ሺህ ተማሪዎች የ8ኛ፣ የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል ፈተና ተፈታኞች ናቸው። የ10ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተና ረቡዕ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ /ነጋሳ ደሳለኝ / ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ