1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሁለተኛው ዙር የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት በጀርመን

ረቡዕ፣ ሐምሌ 29 2012

ጀርመን እስከአሁን የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝን በመከላከሉ ረገድ በአንጻራዊነት ጥሩ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት። በበጋው የእረፍት ጊዜ ወደሌላ አካባቢ የተጓዙ ሰዎች መኖራቸው ወረርሽኙ ዳግም እንዳያገረሽ ስጋት ፈጥሯል። ከሚቀጥለው ሳምንት አጋማሽ አንስቶ ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ። በየግል የሚደረገው ጥንቃቄ በተማሪዎች በኩል ይከበር ይሆን?

Deutschland Coronavirus - Covid-19 Test in Berlin
ምስል Reuters/F. Bensch

«በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው»

This browser does not support the audio element.

ጀርመን እስከአሁን የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝን በመከላከሉ ረገድ በአንጻራዊነት ጥሩ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት። ከሰሞኑ ግን በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወቅት ወደተለያዩ አካባቢዎች የተጓዙ ነዋሪዎቿ መመለስ በመጀመራቸው በተሐዋሲው የተያዙት ቁጥር መጨመሩ እየተነገረ ነው። በቅርቡ ደግሞ ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ። ሜክለንቡርግ ፎርፖመረን፤ ሀምቡርግ፣ በርሊን፤ ብራንደርቡርግ፣ ሽሌቪግ ሆልሽታይን እና ኖርድር ራይን ቬስትፋለን እስከመጪው ሳምንት አጋማሽ ድረስ ከጀርመን 16 ፌደራል ግዛቶች መካከል ትምህርት ቤት የሚከፈትባቸው ናቸው። ባለፈው መጋቢት ወር በወረርሽኙ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ትምህርቱ በርቀት ለወራት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን አሁን ዳግም ወደ ተለመደው የትምህርት ገበታ ለመመለስ ነው ያታቀደው። ይሳካ ይሆን?

የማርቡርገር የህክምና ባለሙያዎች ማሕበር ሊቀመንበር የሆኑት ዙዛነ ዮሐና እንደሚሉት ምንም እንኳን ሁላችንም ያጊዜ ተመልሶ እንዲመጣ ብንናፍቅም የተለመደው አኗኗር  እንዲቀጥል ከማይፈቅድ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። በእሳቸው እምነትም በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች በመበራከታቸው ሁለተኛው የወረርሽኝ ማዕበል እየተቃረበ ነው።  እናም ገና መከላከያ መድኃኒት ላልተገኘለት ወረርሽኝ ራስን የመጠበቂያው ብቸኛ መንገድ ርቀትን ጠብቆ ተገቢውን የመከላከያ ርምጃዎችን በደንብ ማክበር ነው። ይህ ሥርዓት ደግሞ አሁን ብዙዎች በአግባቡ እያከበሩት አይደለም። በዚህ መሀል ከረዥም ወራት በኋላ ትምህርት ቤት ሲከፈት ተማሪዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ ደንቡን ምን ያህል ያከብሩ ይሆን የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው። በተለይ ደግሞ በርካታ ሕዝብ በሚገኝበት በኖርድራይን ቬስትፋለን ግዛት ተማሪዎች በአንድ በኩል ትምህርት ቤት ውስጥ ደንቡን እንዲያከብሩ ማድረግ ቢቻል እንኳ በየመንገዱ ሊኖር የሚችለው መተቃቀፍ ብሎም ትከሻ ለትከሻ ተጠጋግቶ መጫወት መጓዙን ማስቀረት የመቻሉ ነገር አሳሳቢ ሆኗል። ሆኖም በትምህርት ቤት ደረጃ ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲያደርጉ ተወስኗል። ከእረፍት ጉዞ የተመለሱ ዜጎች በፈቃደኝነት የኮቪድ 19 ምርመራ እንዲያደርጉ በተደረገው መሠረት ውጤቱ ከተመረመሩት 2,5 በመቶው መያዛቸውን አሳይቷል። ለዚህ ፈቃደኛ የሆኑት ደግሞ ከተጓዙት 40 በመቶው ብቻ ናቸው። በዚህ ምክንያትም የጀርመን የጤና ሚኒስትር የንስ ሽቴፋን ለተጓዦች መመርመር ግዴታ እንዲሆን ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

ምስል picture-alliance/SvenSimon/F. Hoermann

«የመጀመሪያውን ረቂቅ አዘጋጅተናል ሆኖም በዚህ ላይ ፌደራል ግዛቶች ሁሉ ለትብብር እንዲስማሙበት እየሠራን ነው። ምክንያቱም በአውሮፕላን ማረፊያዎችና በባቡር ጣቢያዎች ላይ ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል። እስከዚያው ግን ስጋት ካለባቸው አካባቢዎች የሚመለሱ ተጓዦች ለሁለት ሳምንት ተገልሎ መቆየት ተግባራዊ ይሆናል።»  

እንዲያም ሆኖ ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ጥቂት መሆናቸው ነው የሚነገረው። አንዳንዶቹም ራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩ በሚጠበቅባቸው ጊዜ ተገቢውን ጥንቃቄ አለማድረጋቸውም የችግሩን አሳሳቢነት አጉልቶታል። የህክምና ባለሙያዎች ግን የሚመክሩት የበሽታው መስፋፋት ስጋት ካሳደረባቸው አካባቢዎች የተመለሰ ሰው በቀናት ውስጥ ተደጋጋሚ ምርመራ አድርጎ እንደሌለበት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልገው ነው። በዚህ መሀል የታማሚዎች ቁጥር ቢበረክት በሚል ስጋት ሃኪም ቤቶች አቅማቸውን ማጠናከር ይዘዋል። ሁሉም የማይፈልገው ግን ድጋሚ አጠቃላይ የእንቅስቃሴ ገደብ በኩባንያዎች፣ ሱቆችና ትምህርት ቤቶች ላይ መጣሉን ነው። አብዛኞቹ ፖለቲከኞችም ተስፋቸውን ቴክኒዎሎጂ ላይ አድርገዋል። በተለይም በኮቪድ 19 ተሐዋሲ የተያዘ ሰው በአቅራቢያ መኖሩን ያመላክታል በተባለው መተግበሪያ። እስካሁን ጀርመን ውስጥ 16,5 ሚሊየን ሕዝብ ይህን መተግበሪያ በፍላጎት እየተጠቀመበት ነው። ሮበርት ኮህ ተቋም ያዘጋጀው ይህ መተግበሪያ ከዚህም ሌላ የልብ ምትን ጨምሮ እርምጃን ሳይወር ወደ ተቋሙ የመረጃ ቋት ይልካል። ከፈቃደኞች በየዕለቱ የተሰባሰበውን መረጃ ተጠቅሞም በሀገሪቱ የትኩሳት መጠን የት እንደደረሰ መገመት እንደሚያስችለው የተቋሙና የበርሊን ሁምቦልት ዩኒቨርሲቲ የበሽታዎች ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ ዲርክ ብሮክማን ገልጸዋል።

ምስል picture-alliance/Eibner-Pressefoto

«በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ የልብ ምትና የርምጃቸውን መረጃዎቻቸውን ቁጥር ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆኑ ወገኖች  የተገኘውን የርምጃ ልክና የልብ ምት መመዘን ከጀመርን ጥቂት ሳምንታት ሆኖናል። በዚህ አማካኝነትም የቀደመውንና የአሁኑን የሙቀት ነጠን ልክ እናያለን። ይህ ብቻም አይደለም የታማሚዎችን ቁጥር ወይም ከመተንፈሻ አካላት ህመም ጋር በተገናኘ የሙቀት መጠኑንም መለካት እንችላለን።»

ተመራማሪው እንደሚሉትም በዚህ አማካኝነት በመላዋ ጀርመን የኮሮና ተሐዋሲ ያለበትን የመዛመት ደረጃም መመልከት ይቻላል።

 ሸዋዬ ለገሠ/ ዛቢነ ኪንካርትስ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW