1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሁለቱ የቴክ አፍሪካ አሸናፊ ጀማሪ ቴክኖሎጅዎች

ረቡዕ፣ ጥቅምት 9 2015

በአፍሪቃ በሴቶች ባለቤትነት ስር ያሉ የቴክኖሎጂ ጅምሮችን የሚደግፈው «ቴክ አፍሪካ ውሜን»የተባለው ድርጅት በኢትዮጵያ ፣ሴኔጋል ታንዛኒያ እና ቱኒዚያ ከ300 በላይ ቴክኖሎጅዎችን በቅርቡ አወዳድሯል።ከነዚህ ውስጥ ስምንት ቴክኖሎጅዎች አሸናፊ ሆነዋል።ከኢትዮጵያም ጤና ሰብ እና መቆያ ሞምስ የተባሉ ሁለት ጅምር ቴክኖሎጅዎች ተመርጠዋል።

Äthiopien Startups "Tena seb" und "Mekoya Mom"
ምስል privat

ጤና ሰብ እና መቆያ ሞምስ የተባሉ ሁለት የቴክኖሎጅ ሃሳቦች ተሸላሚ ሆኑ

This browser does not support the audio element.


የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት «ቴክ አፍሪካን ውሜን»/ Tech African Women/  የተባለ  ድርጅት በቅርቡ በአፍሪቃ ደረጃ ባካሄደው የቴክኖሎጅ  ውድድር ከኢትዮጵያ ተሸላሚ በሆኑ ሁለት ጀማሪ ቴክኖሎጅዎች ላይ ያተኩራል። 
መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው እና  በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን/ECA/ ስር የሚገኘው ቴክ አፍሪቃን ውሜን/ Tech African Women/ የተባለው ድርጅት በቅርቡ በአራት የአፍሪቃ ሀገራት የሚገኙ ጅምር የቴክኖሎጅ ሀሳቦችን አወዳድሯል።
በሴቶች ባለቤትነት ስር ያሉ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ጅምሮችን የመደገፍ  ዓላማ ያለው  ይህ  ድርጅት ውድድሩን ያካሄደው በኢትዮጵያ ፣ሴኔጋል ታንዛኒያ እና  ቱኒዚያ  በሚገኙ በአጠቃላይ የማህበረሰብን ችግር  በተለዬ ሁኔታ ደግሞ የሴቶችን ችግር  በሚፈቱ ቴክኖሎጅዎች ላይ ነው።
 ካለፈው ጥር 2022 ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው በዚህ ውድድር ከአራቱ ሀገራት 338 አመልካቾች የቀረቡ ሲሆን 74ቱ ሴቶች ናቸው።ከነዚህም ውስጥ ከአራቱ ሀገራት ሁለት ሁለት በድምሩ ስምንት ቴክኖሎጅዎች የመጨረሻ ሆነው ተመርጠዋል።
ከኢትዮጵያም ጤና ሰብ እና መቆያሞምስ የተባሉ በሴቶች ባለቤትነት ስር ያሉ ሁለት ቴክኖሎጅዎች በዚህ የውድድር መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው መመረጣቸው ይፋ ሆኗል። በአለርት ሆስፒታል ጠቅላላ ሀኪም የሆነችው እና የጤናሰብ ሀሳብ አመንጭ  ዶክተር ዝማሬ ታደሰ ውድድሩን እንደሚከተው ታብራራለች።
«እንግዲህ ፕሮግራሙ በመጀመሪያ ደረጃ  በሴቶች የሚመሩ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮረ «ስታርትአፕ» ላይ የሚሠራ ስለሆነ ብዙ ሴቶች ተወዳደሩ። ከነዚያ ውስጥ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከተወዳደሩት ውስጥ 12 የምንሆን ይመስለኛል። እና የመጀመሪያውቹን ሦስት ቀናት ስልጠና ከሰጡን በኋላ ውድድር ተካሄደ።በዚህ ውድድር የተለያዩ ዳኞች ተሳትፈው ነበር። እነሱ ናቸው። ለእነሱ አቅርበን አንደኛ እና ሁለተኛ ብለው የመረጡት።እና አንደኛ እና ሁለተኛ የሆንነው ወደ ሚቀጥለው ፕሮግራም አለፍን ማለት ነው።የመጀመሪያው ውድድር ሽልማቱ 2000 ዶላር ነው። በተመሳሳይ ከአራቱ ሀገራት ታንዛኒያ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያ እና ኢትዮጵያ ።»
ጤና ሰብ /Tenaseb / ስለ-ሥነ ተዋልዶ ጤና ሴቶችን በማማከር ትምህርት የሚሰጥ መተግበሪያ ነው።ወጣቷ የጤና ባለሙያ ዶክተር ዝማሬ እንደምትገልፀው የተመረጠውም  ከችግር ፈችነቱ አንፃር ነው።
«እንግዲህ ዳኞች የሚያዩበት የተለያዬ መስፈርት ይኖራል።ነገር ግን ዋናው ችግር ፈች የሆነ ሀሳብ ነው ወይ? የሚለው ነው።እኛ እያቀረብን ያለነው በሀሳብ ደረጃ ያለ «ስታርታአፕ»ስለሆነ ማለት ነው።» ካለች በኋላ በዚህ ሃሳብ በተጨባጭ ያለ ችግርን ለይተው መቅረባቸውን ጠቅሳለች።ይህንን ስራ ሲሰሩም «ቀጣይነት ባለው የልማት ግቦች ውስጥ ቢያንስ ሶስቱን መድረስ እንችላለን። የሴቶች ደህንነትን፣ ጤናን እና ስራ የመፍጠር አቅምን» ስትልም ሀሳቧን አጠናክራለች።
ባለሙያዋ  ከዚህ ቀደም የተለያዩ ዲጅታል አማራጮችን  እንዲሁም ዩቲብ፣ ፌስቡክ፣ዋትስ አፕ እና ቴሌግራም የመሳሰሉትን የዘመኑ ቴክኖሎጅ የወለዳቸውን የማህበራዊ መገኛኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ይህንን አገልግሎት ስትሰጥ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት የተገነዘበችው የሴቶች የጤና ችግር ስፋት ግን አገልግሎቱን ወደ  መተግበሪያ የማሳደግ ሀሳብ አሳድሮባታል።
 «ይህንን ፕሮግራም ጤና ሰብን  የጀመርኩት መጀመሪያ በዩቱብ ነበር።ቪዲዮችን «ሸር» በማደርግበት ስዓት ላይ የተለያዩ ቪዲŠceን ነበር ሸር የማደርገው ግን ከነዚያ ውስጥ የጾታዊ እና የሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ይበልጥ ማተኮር ጀመርኩ።ወደዚያ እያተኮርኩ ስመጣ፤ ብዙ ሴቶች «ኮሜንት» ያደርጋሉ። እዚያው ላይ ችግሮቻቸውን «ኮሜንት» የሚያደርጉ የሚፅፉ አሉ። ግን ደግሞ በግል ማማከር የሚፈልጉ አሉ።ቴሌግራም ከፈትኩ እና ማማከር ጀመርኩ።ብዙ ሴቶችን እንዲያካትት ይህ ነገር እንዴት ነው የበለጠ ተደራሽ የሚሆነው የሚለውን ማሰብ የጀመርኩት ከዚያ ጀምሬ ነው።» በማለት አሁን የተወዳደረችበትን የሴቶች የሥነ-ተዋልዶ ጤና መተግበሪያን የማበልፀግ ሀሳብ እንዴት እንደመጣ ገልፃለች።
ስለሆነም የጤና ሰብ መተግበሪያን ማበልፀግ እና ጥቅም ላይ  ማዋል በሀገር ውስጥ ያሉ ሴቶች ከሚያጋጥማቸው እና ብዙም በግልፅ ከማይወራበት የሴቶች የሥነ-ተዋልዶ  ጤና ችግር በተጨማሪ በተለይ በአረብ ሀገራት  እና በሌሎች ውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሴቶች ከባህል እና ከቋንቋ ችግር አንፃር  የሚገጥማቸውን ክፍተት ለመሙላት ያግዛልም ትላለች።
ድርጅቱ በሴቶች የሚመሩ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ሀሳቦችን ለመደገፍ ባካሄደው ውድድር ከኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ የተመረጠው «ማቆያ ሞምስ» የተባለው ዲጅታል መድረክ ነው።ከመስራቾቹ መካከል አንዷ የሆነችው ምንታምር ሲሳይ እንደምትገልፀው ይህ መድረክ እናቶች ለልጆቻቸው  ተንከባካቢ በቀላሉ እንዲያገኙ የሚረዳ ዲጅታል መድረክ ነው።
የመድረኩ መስራች እንደምትለው መቆያ ሞምስ፤አዲስ ለተመረቁ ወጣት የጤና ባለሙያ ሴቶችም የስራ ዕድል ይፈጥራል። እሷ እና  የሀሳቡ ጠንሳሽ ጓደኞቿ ይህንን ዲጅታል መድረክ የመሰረቱትም በአካባቢያቸው ከተመለከቱት ተጨባጭ ችግር በተለይ  እሷ ካጋጠማት የግል ችግር በመነሳት ጭምር ነው።«አሁን ባለው ሁኔታ ሰዎች ልጆቻቸውን የሚያቆዩበት ቦታ «አክሰስ» ለማድረግ አዲስ አበባ ውስጥ በጣም ከባድ ነው።የህፃናት ማቆያ ለማግኜት ይከብዳል።ይህንን ደግሞ «ፐርሰናሊ» ልጅ ወልጄ «አክሰስ» የማገኝበት ሁኔታ አልተፈጠረም ነበር። » ካለች በኋላ የትኛው የህፃናት ማቆያ የትኛውን አገልግሎት ይሰጣል የሚል የተደራጄ የመረጃ ቋት የለም ስትል ያጋጠማትን ችግር ገልፃለች።«ሰራተኛ ሲታጣ ስው በስራ ላይ ሆኖ ልጄን  የት ላቆየው የሚለውን በግሌ ስለተቸገርኩኝ»ምን ማድረግ እንችላለን የሚለውን ከማየት ከዚያ የተነሳ ነው።» በማለት የሃሳቡን መነሻ ገልፃለች።  

ምስል privat
ምስል privat
ምስል privat
ምስል privat
ምስል privat

በውድድሩ ጤናሰብ እና መቆያ ሞምን ጨምሮ  በግብርና፣ በጤና፣ በገንዘብ አያያዝ፣ በአየር ንብረት ጥበቃ እና የሴቶችን የስራ ጫና የሚያቀሉ የቴክኖሎጅ ሀሳቦች ከቱኒዚያ፣ ከሴኔጋል እና ከታንዛኒያም ተመርጠዋል።
እነዚህ በውድድሩ አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ ምርጥ ጅምር የቴክኖሎጅ ሀሳቦችም ወደ ቀጣዩ ደረጃ አልፈዋል። የእያንዳንዱ አሸናፊ ቡድንም የ2000 ዶላር የገንዘብ ሽልማት አሸንፏል።በጎርጎሪያኑ በመጭው ታህሳስ 2022 ዓ/ም በአዲስ አበባ የመጨረሻዎቹ ስምንት ቴክኖሎጅዎች የውድድሩ የአሸናፊዎች አሸናፊ ለመሆን እና የመጨረሻውን የ7000 ዶላር ሽልማት ለማግኘት ሌላ ዙር  ውድድር ያካሂዳሉ።
እስከዚያው ግን ስምንቱን የመጨረሻ እጩዎች ለገበያ እና ለንግድ  ብቁ ለማድረግ እና  ስራዎቻቸውን በማሳደግ ወደ ተግባር ለመቀየርም የሁለት ወር  የበይነመረብ የስልጠና መርሀ-ግብር በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።በዚህ ስልጠና ምንታምር እንደምትለው ጥሩ እውቀት እና ልምድ እያገኙበት ነው።
 ዶክተር ዝማሬም ውድድሩ መተግበሪያውን ዕውን ለማድረግ ከሚረዳት የገንዘብ ሽልማት ባሻገር  በስልጠና የተገኘው ዕውቀት እና ከሌሎች ሀገራት ተወዳዳሪዎች የቀሰሙት የቴክኖሎጅ ልምድ ቀላል አይደለም ትላለች።
በመሆኑም እሷ እና ቡድኗ ከዚህ በተገኘው ልምድ  ዲጅታል ቴክኖሎጅን በመጠቀም በተሻለ መልኩ በስፋት የመስራት ዕቅድ ይዘዋል።ከችግሩ ስፋት አንፃር ግን ሌሎች ባለሙያዎችም የዘመኑን ቴክኖሎጅ ተጠቅመው የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት ቢጥሩ መልካም መሆኑንም የጤና ባለሙያዋ  ጨምራ ገልፃለች።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW