1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሁለት ሱዳናውያን ስደተኞች በሊቢያ የባሕር በር ጠባቂዎች ተገደሉ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 21 2012

የሊቢያ የባሕር በር ጠባቂ ኃይል ሁለት ሱዳናውያን ስደተኞች መግደሉን እና አምስት ማቁሰሉን ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት አስታወቀ። ስደተኞቹ የሜድትራኒያን ባሕርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ሲሞክሩ ተይዘው ወደ ኹምስ እንዲመለሱ ከተደረጉ በኋላ ትንናት ምሽት የባሕር በር ጠባቂዎች በከፈቱት ተኩስ መገደላቸውን ድርጅቱ አስታውቋል

Libyen Migranten vor der libyschen Küste
ምስል፦ picture-alliance/AP Photo/O. Calvo

የሊቢያ የባሕር በር ጠባቂ ኃይል ሁለት ሱዳናውያን ስደተኞች መግደሉን እና አምስት ማቁሰሉን ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (IOM) አስታወቀ።

ስደተኞቹ የሜድትራኒያን ባሕርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ሲሞክሩ በሊቢያ የባሕር በር ጠባቂ ኃይል ኹምስ ወደ ተባለ የወደብ ከተማ እንዲመለሱ ከተደረጉ በኋላ ትንናት ምሽት የባሕር በር ጠባቂዎች በከፈቱት ተኩስ መገደላቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።

በኹምስ የሚገኙ የዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት ሰራተኛ ስደተኞቹ ከተጫኑበት ጀልባ በወረዱበት ቅጽበት ለማምለጥ ሲሞክሩ በተከፈተ ተኩስ ሁለት ሱዳናውያን መገደላቸውን እና ሌሎች አምስት መቁሰላቸውን እንዳረጋገጡ ተቋሙ በዛሬው ዕለት ባወጣው ገልጿል።

በመግለጫ መሠረት የቆሰሉ ስደተኞች በአካባቢው ወደ ሚገኝ ሆስፒታል ሲወሰዱ የቀሩት ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።

“በሊቢያ የስደተኞች ስቃይ መታገስ የማይቻል ነው” ሲሉ በሊቢያ ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት ኃላፊ ፌዴሪኮ ሶዳ ተናግረዋል።

“ያልተመጣጠነ ኃይል ጥቅም ላይ በመዋሉ እንደገና የሰው ሕይወት ትርጉም አልባ በሆነ መንገድ ጠፍቷል” ያሉት ፌዴሪኮ ሶዳ የስደተኞችን ደሕንነት ለመጠበቅ በአካባቢው ባለው አሰራር ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ የቀረበው ጥሪ ሰሚ ማጣቱን አስታውሰዋል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት በጦርነት ታምሳ መረጋጋት የራቃት ሊቢያ ያለው ነባራዊ ኹኔታ ለስደተኞች አስጊ በመሆኑ ተጋላጭ የሆኑትን ወደ አገሪቱ መመለስ አይገባም ሲል ለአውሮፓ ኅብረት ጥሪ አቅርቧል።

ድርጅቱ እንደሚለው በባሕር ላይ ሳሉ በጸጥታ አስከባሪዎች የሚያዙ ስደተኞች ደሕንነታቸው ወደሚጠበቅበት ወደብ የሚያመሩበት ሥርዓት ሊበጅ ይገባል። “በአውሮፓ አገራት እና ስደተኞቹ በቀጥታ የሚጓዙባቸው የሜድትራኒያን አካባቢ መንግሥታት ጠንካራ ትብብር ሊኖራቸው ያሻል” ሲልም ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (IOM) አሳስቧል።

ባለፉት አመታት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች የሜድትራኒያን ባሕርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ሲያቅዱ ሊቢያን እንደ መሸጋገሪያ ሲጠቀሙ ቆይተዋል።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW