1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአውሮጳ

ፋይዘር እና ባዮንቴክ ከአስትራዜኔካ ጋር የፈጠሩት ጥምረት ያስገኘው ውጤት

ረቡዕ፣ ሰኔ 23 2013

ሰሞኑን በእንግሊዝ እና ጀርመን ሀገራት የተደረጉ ጥናቶች ፤ ደረስኩበት ባለው ምርምሩ የአስትራዜኔካ እና የባዮንቴክ ክትባቶች ጥምረት ከሁለት የአስትራዜኔካ መጠን በበለጠ ተሐዋሲውን የመከላከል አቅም እንዳለው አመላክቷል።

የሁለት የኮሮና ክትባቶች በጥምረት መሰጠት ያስገኘው ውጤት እና አንድምታው

This browser does not support the audio element.

ጤና ይስጥልን አድማጮች በዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መሰናዷችን በእንግሊዝ እና ጀርመን  የተደረጉ የተናጥል የሁለት የኮሮና ክትባቶች ጥምረት ጥናት ውጤት እና አንድምታውን እንዳስሳለን አብራችሁን ቆዩ።

ሰሞኑን በእንግሊዝ  ሀገር የተደረገ ጥናት ፤ ደረስኩበት ባለው ምርምሩ የአስትራዜኔካ እና የባዮንቴክ ክትባቶች ጥምረት ከሁለት የአስትራዜኔካ መጠን በበለጠ ተሐዋሲውን የመከላከል አቅም እንዳለው አመላክቷል።

ይህ ሁለቱን ክትባቶች በማጣመር ተገኘ የተባለው ውጤት በተለይ አሁን ላይ በተለያዩ ሀገራት ባሕሪውን እየቀየረ ታላላቆቹን ሀገራት ጭምር በመፈታተን ላይ የሚገኘውን የኮሮና ተሐዋሲ በዘላቂነት ሊያቆመው ይችል ይሆን ፤ ለአፍታ እንመልከተው። ባለፈው የጥር ወር የአውሮጳ መድኃኒቶች ኤጄንሲ የአስትራዜኔካ ክትባት ለአዋቂዎች ብቻ እንዲሰጥ ከወሰነ በኋላ እዚህ ጀርመን ሀገር ክትባቱ ለአዋቂዎች ብቻ እየተሰጠ ይገኛል። ክትባቱ ቀደም ሲል ወጣቶችን በተለይም በአንጎል ውስጥ አደገኛ የደም መርጋት አደጋ ተጋላጭ ማድረጉ እንደተደረሰበት ኤስቲኮ በሚል ምህጻር የሚታወቀው የጀርመን የክትባት ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ምክረ ሀሳብ መሰረት ክትባቱ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች ብቻ እንዲሰጥ ተደርጓል። ይህ አንደኛው የአስትራዜኔካ የተናጥል የጎንዮሽ ችግር ተደርጎ እንዲመዘገብ ብሎም አንዳንድ ሀገራት ክትባቱን መስጠት እስከማቆም የደረሱበትን ውሳኔ ጭምር እንዲወስዱ አስገድዶ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል።

ምስል Douglas R. Clifford/Tampa Bay Times/ZUMA/picture alliance

በወቅቱ የመጀመርያውን ዙር የአስትራዜኔካ ክትባት የወሰዱ ሰዎች የጎንዮሽ ጉዳቱን ሽሽት ሁለተኛውን ዙር የፋይዘር እና ባዮንቴክ አልያም ሞደርና የተባለውን ክትባት ለመውሰድ ይገደዱ ነበር። በእርግጥ አሁን ያ ተለውጦ ተከታቢው ግለሰብ ከሐኪም ጋር በሚያደርጉት ምክክር ብቻ በየትኛውም የዕድሜ ደረጃ ላይ ይሁኑ ሁለቱንም ዙር አስትራዜኔካን መከተብ ተችሏል። ነገር ግን ባህሪውን ቀይሮ የመጣው ተሐዋሲው ሌላ ስጋት ፤ ስጋቱ ሌላ ጥረት እና ምርምር ጠይቆ የክትባቶች ውጤት ያስገኘ የክትባቶች ውህደት አስገኝቷል።

 

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ሰሞኑን ይፋ ባደረጉት ጥናታቸው በመጀመርያው ዙር የፋይዘር እና ባዮንቴክ ክትባትን ወስደው ከአራት ሳምንታት በኋላ የአስትራዜኔካ ክትባትን የወሰዱ ሰዎች ሁለቱን ዙር የአስትራዜኔካ ክትባትን ከወሰዱ ሰዎች በተሻለ የሰውነት የበሽታ የመቋቋም አቅም አዳብረው እንደተገኙ አረጋግጧል። ይህ ደግሞ የውህድ ክትባቱ ውጤት ጊዜያዊ አስቸኳይ መፍትሄ ከመሆን ይሻገራል ባይ ናቸው ተመራማሪዎቹ ። ምክንያቱ ደግሞ የሰው ልጅ ተሐዋሲውን በዘላቂነት መከላከል የሚያስችለውን ውጤት ስለሚሻ ነው።

ተመራማሪዎቹ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ በሆኑ 850  በጎ ፈቃደኞችን አሳትፈው ውጤታማ መሆናቸውን አሳይተዋል። በዚህም ሁለቱን ዙር የፋይዘር እና ባዮንቴክ ክትባትን አልያም አስትራዜኔካን እንዲወስዱ ከተደረጉት ይልቅ የአስትራዜኔካ አልያም የፋይዘር እና ባዮንቴክ ክትባትን በማስቀደም አልያም በማስከተል የወሰዱ ሰዎች አንድ አይነቱን ብቻ ከወሰዱት ሰዎች እጅጉን በተሻለ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም አዳብረው መገኘታቸው ተመልክቷል።

በጥናቱ ዋና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማቲው ስናፕ እንዳሉት የጥምር ክትባቱ ውጤት የአስትራዜኔካን ክትባትን ብቻ በመስጠት  የተገኘውን በሽታውን የመከላከል ስትራቴጂ ውጤት ዋጋ አያሳጣውም  ።

«አዲሱ የጥምር ክትባት ውጤት ዴልታ የተሰኘውን አዲስ ባሕሪ ያመጣውን ተሐዋሲ መከላከልን ጨምሮ በተሐዋሲው ተይዘው በብርቱ የታመሙትን እና በሆስፒታል ክትትል ለሚሹት ሁሉ ውጤታማ መሆኑን አስቀድመን ደርሰንበታል። እናም  በእውነቱ እነዚህን ክትባቶች ሲጠቀሙ ብዙ አማራጮች እንዳሉና ማወቅ እና  እርስዎ ለመጀመሪያው ተመሳሳይ ክትባት ከመጠቀም ይልቅ ሁለተኛው አማራጭ የተሻለነገር ይዞ መጥቷል።»

በእንግሊዝ የኮሮና ክትባት መርኃ ግብር መሰረት በሁለት ዙር ይሰጥ የነበረው የክትባት የጊዜ ልዩነት አብዛኛውን ጊዜ ከስምንት እስከ አስራ ሁለት ሳምንታት የሚደርስ ነበር። በአዲሱ ጥናት ግኝት መሰረት  በሁለት የተለያዩ የክትባት አይነቶች መካከል የሚኖረው የሳምንታት ልዩነት እንደቀደመው ከስምንት እስከ አስራ ሁለት የሚደርስ  ሳይሆን የአራት ሳምንታት ጊዜ ብቻ ነው። እንደ ስናፕ  ገለጻ። ውጤታማውን ጥናት ምናልባትም ከተያዘው የጎርጎርሳውያኑ የሐምሌ ወር ጀምሮ ገቢራዊ የሚደረግበትን ሂደት እየተመለከቱ እንደሚገኙም ጭምር ነው ፕሮፌሰሩ የተናገሩት።

ጥምር ክትባቶች ከሚኖራቸው ዓለማቀፍ ተቀባይነት  እና በሌሎች ክትባቶች ላይ ሊያሳድሩሩ ከሚችሉት ተጽዕኖዎች አንጻር ፕሮፌሰሩ ሲገልጹ «እነዚህ ክትባቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ለማሰብ እና  ጥናቱ  የቻይና ፣እና ስፑትኒክ ክትባቶችን ጨምሮ ከሌሎች ክትባቶችን ጋር ማጣመር ይቻል እንደሁ እድል የሚፈጥርም ነው። ምክንያቱም እነዚህ የክትባቱ አቅርቦት ሊተነብይ በማይችልበት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ውስጥ የበለጠ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ክትባቶችን ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል።  ስለዚህ ክትባቶችን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ጨምረን የተሻለ ሀሳብ እንድናገኝ በእውነቱ አስፈላጊ የምርምር መስክ ይመስለኛል »

 

ይህንኑ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጥናት የጀርመን ተመራማሪዎችም አረጋግጠውታል። በምዕራባዊ ጀርመን በሚገኘው የሳርላንድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡት  ሁለቱንም ጊዜ ተመሳሳይ የክትባት አይነት ከወሰዱ ሰዎች ይልቅ የተለያዩ ክትባቶችን ማለትም የአስትራዜኔካ እና የፋይዘር እና ባዮንቴክ ክትባቶችን በማፈራረቅ የተከተቡ ሰዎች በተሻለ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅማቸው እጅጉን ጎልብቶ መገኘቱን አ,ረጋግጠዋል።

ስለዚህ የዓለም የክትባት መርሃግብርን በጥናቱ መሰረት በሁሉም ሰዎች ላይ ገቢራዊ ማድረግ ጊዜው አሁን ይሆን  ፤ አይደለም ይላል ጥናቱ ። ምክንያቱ ደግሞ ጥናቱ በቅድመ ጥናታዊ የህትመት ደረጃ እንጂ በገለልተና የሳይንስ ሊቃውንት ግምገማ ሂደት ውስጥ ማለፍ ስለሚኖርበት። ጥናቱ ምንም እንኳ በተሟላ የመረጃ ምዘና ማረጋገጫ ውስጥ ባያልፍም ጥናቱን ያካሄደው ቡድን በተገኘው አመርቂ ውጤት መገረሙን አልሸሸገም ።

በሳርላንድ ዩኒቨርሲቲ የንቅለ ተከላ እና የኢንፌክሽን በሽታዎች መከላከያ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርቲና ሴስተር እንደሚሉት የተንዛዛውን ሳይንሳዊ የመረጃዎች ማጠናቀርያ እና ግምገማ ሳይጠብቁ ውጤቱን ይፋ ማድረጋቸው ምክንያታዊ መሆኑን በጽሁፍ ባወጡት ጋዜጣዊ መግለጫው እንደጠቆሙት። «እኛ የሳይንሳዊ ምዘና ሂደቱን ሳንጠብቅ ውጤቱን አሁኑኑ ማካፈል የፈለግነው በምክንያት ነው»

ባለፉት ጥቂት ወራት ዩኒቨርሲቲው ሀምቡርግ ውስጥ በ250 በጎ ፈቃደና ሰዎች ላይ ባደረገው የሙከራ ጥናት የተወሰኑቱ ተመሳሳይ የፋይዘር እና ባዮንቴክ ክትባቶችን እንዲወስዱ የተወሰኑቱ ደግሞ ተመሳሳይ የአስትራ ዜኔካ ክትባቶችን እንዲሁም የተወሰኑቱ ደግሞ የአስትራዜኔካ እና የባዮንቴክ ክትባቶችን ባማስቀደም አልያም በማስቀጠል እንዲወስዱ ተደርጓል። ውጤቱ ደግሞ ያው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከደረሰበት ጋር ተመሳሳይ ነው።

ምስል Chris Aluka Berry/REUTERS

ፕሮፌሰር ማርቲና ሴስተር ውጤቱን ይፋ ባደረጉበት መግለጫቸው እንዳሉት ጥምር ክትባቶችን የወሰዱ ሰዎች በሁለተኛ ሳምንታቸው ከፍተ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም አዳብረው መታየታቸውን ነው። ሲያስረዱ፤

« በጥናቱ የተሳተፉ ሰዎችን የኮሮና ተሐዋሲን የመከላከል አቅማቸው ምን ያህል እንደዳበሩ ብቻ አይደለም የተመለከትነው ፤ ይልቁንም በሂደቱ ተፈጥሯዊ በሽትን የመከላከል አቅም ምን ያህል ሳይዛባ ዳብሮ ቆይቷል የሚለውን ከግምት ውስጥ አስገብተናል» ይህም ይላሉ ፕሮፌሰር ሴስተር « ይህ ውጤት የሚነግረን ጸረ እንግዳ ሕዋሳቱ ተሐዋሲው ወደየሰውነታን ህዋሲ እንዳይገባ ለመከላከል ምን ያህል ጥሩ እንደሆነ ነው »

ተመራማሪዎቹ የበጎ ፈቃደኞችን ከክትባት በኋላ የሰውነት በሽታን የመቋቋም አቅምን ተመልከተው እንደደረሱበት ጥምር ክትባት የወሰዱ ሰዎች ተመሳሳይ የአስትራዜኔካ ክትባት ከወሰዱት ይልቅ በአስር እጅ ከፍ ያለ  በሽታን የመቋቋም አቅም ሲያዳብሩ የፋይዘር እና ባዮንቴክን ክትባት ከወሰዱ ሰዎች አንጻር ደግሞ በመጠኑ የተሻለ ሆነው ተገኝተዋል።

ሂደቱ ከሰውነት በሽታን ከመከላከል አቅም አንጻር በተጨባች የታየው ነገር ከድርብ የፋይዘር እና ባዮንቴክ አልያም የአስትራዜኔካ ክትባቶች ይልቅ የሁለቱ ጥምር አማራጭ የበለጠ ውጤታማ እንደነበር ያረጋገጠ ስለመሆኑ ተመራማሪዋ አስረድተዋል።

ምስል Yui Mok/PA Wire/empics/picture alliance

ምንም እንኳ የእንግሊዝ እና የጀርመን ተመራማሪዎች ደረስንባቸው ያሉት የመጀመርያዎቹ የጥምር ክትባቶች ውጤታማ ቢሆኑም የዓለም የጤና ድርጅት አሁንም ቢሆን ክትባቶች  ተቀላቅለው እንዲሰጡ አልመክርም ይላል። የእስካሁኑ ውጤት ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ የተካሄደ ስለመሆኑ ለመገምገም በቂ መረጃ የለም ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ቃል  አቃባይ ማርጋሬት ሃሪስ ተናግረዋል።

ምስል WHO

በክትባት መርኃግብር ላይ የፖል ኤርሊች ተቋም መመርያን የምትከተለው ጀርመን ግን  ሁለቱን ጊዜ ተመሳሳይ ክትባቶችን አልያም ተዛማጅ ጥምረት ያላቸውን ክትባቶችን የወሰዱ ሰዎች  ሙሉ ክትባት እንደወሰዱ ትቀበላለች።

ነገር ግን ይህ በሁሉም ሀገሮች ተመሳሳይ አይደለም። ለምሳሌ ካናዳ ጥምር የክትባት መርኃግብርን ተቀብላ አጽድቃለ,ች። ዩናይትድስቴትስ ገና በጥናት ላይ ናት። የአውሮጳ ህብረት ደግሞ ከሐምሌ ወር ጀምሮ የጥምር ክትባቱ ተግባራዊ ተደርጎ በዲጂታል የክትባት ማለፊያ ስረዓት ዕውቅና ይቸረው ይሆን ገና አልታወቀም። ምዕራባውያኑ ክትባቱን በበለጠ ለማበልጸግ የሚተጉትን ያህል በማደግ ላይ ያሉቱ ሀገራት ግን ከክትባቱ አሁንም በርቀት ላይ መገኘታቸው ዓለም ከተሐዋሲው ለምታደርገው ትግል አንድ እርምጃ ወደ ኋላ መጎተቱ አይቀሬ ስለመሆኑ የሚያሳስቡም አልጠፉም ። ለዛሬ ያልነው ይህን ይመስል ነበር ሳምንት በሌላ ዝግጅት እንጠብቃችኋለን ። ከዝግጅቱ ጋር ታምራት ዲንሳ አብሬአችሁ ቆየሁ ጤና ይስጥልን።

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ ሐሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW