ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች “በአጀንዳ ልየታ አንሳተፈም” አሉ።
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 19 2017
ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች “በአጀንዳ ልየታ አንሳተፈም” አሉ፡
ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች በአማራ ክልል በሚካሄደው የአጀንዳ መረጣ እንደማየሳተፉ አስታወቁ፡፡ ፓርቲዎቹ በአማራ ክልል ያለው ጦርነትና በአንዳንድ ይክልሉ አካባቢዎች የታየው የምግብ እጥረት መጀመሪያ መፈትሔ ማግኘት አለበት ብለዋል፡፡
የመኢአድና የእናት ፓርቲ ውሳኔ
የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና እናት ፓርቲ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹት የአማራ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎቸ በአየርና በምድር ጭምር ጥቃት እይደረሰበት ባለበት በአሁኑ ሰዓት፣ በጸጥታ ችግር ምክንያት መንገዶች በተደጋጋሚ በሚዘጉበተ ሁኔታ፣ በርካታ ወገኖች በድርቅ ተጎድተው እርዳታ በራቃቸው ሰዓት በአጀንዳ ልየታ ስራ አይሳተፉም፡፡
የእናት ፓርቲ ሰብሳቢ ዶ/ር ሰይፈስላሴ አያሌው ተጨማሪ አስተያየት ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየት የሚከተለውን ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል በበርካታ ችግሮች ውስጥ ነው
“የአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በሚባል መልኩ የጦርነት ቀጠና ሆነው የክልሉ ሕዝብ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአየርና በምድር በከባድ መሣሪያና በተደጋጋሚ በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ጭምር እያለቀ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገበት ጊዜ ያበቃ ቢሆንም ክልሉ ሙሉ በሙሉ በኮማንድ ፖስት እየተዳደረ ባለበት ኹኔታ፣ በርካታ ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸውና ማንነታቸው ታሥረው በሚገኙበት ሁኔታ፣ ጦርነቱ መጠኑን አሥፍቶ እየተባባሠ በመጣበትና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ አልፎ አልፎ ሙሉ በሙሉ እንዲገደብ በሚደረግበት ኹኔታ በክልሉ በተቀሰቀሰው የትጥቅ ትግል ምክንያት መንግሥት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን እርዳታ የማድረስና የመታደግ ፍላጎት በራቀበትና በዚህ ምክንያት ሕዝቡ በአንዳንድ አካባቢዎች ለአስከፊ ረሃብ በተጋለጠበት ኹኔታ በክልሉ የአጀንዳ ልየታ ሥራማስብ ከፈረሱ ጋሪው የቀደመበትና ኮሚሽኑ እውነተኛ ምክክር የማድረግ እንቅስቃሴ ሳይሆን የሥርዓት ዓላማ ማስፈጸሚያ መሣሪያ ወደ መሆን ገባ ወይ? እንድንል አስገድዶናል።” ሲሉ ነው በደብዳቤያቸው የገለተሱትን ሀሳብ የነገሩን፡፡
በአማራ ክልል ያለው ጦርነት በገለልተኛ አካል ሊሸመገል ይገባል
ተፈላጊውና ዘላቂ ሰላም በክልሉ ለማስፈን መንግስት እውነተኛ የሰላም ፍላጎት ማሳየትና ተግበራዊ ማድረግ እንዳለበት ዶ/ር ሰይፈስላሴ ጠይቀዋል፡፡
“ምክክሩ እውነተኛ ምክክር ሆኖ አገር በእጅጉ የምትሻውን ውስጣዊ ሰላምና ለሕዝባችን አንድነትን እንዲያመጣ ከተፈለገ በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት በገለልተኛ አካል አሸማጋይነት እልባት እንዲያገኝና በአንድ እጅ ጠመንጃ በሌላ እጅ የምክክር አጀንዳ ይዞ መጓዝ እንደማይቻልና ከኹሉ አስቀድሞ በትግራይ ክልል የተካሄደው ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት እንደተቋጨ ኹሉ አሁንም በሌሎች የአገራችን አካባቢዎች በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶች ቀደም ሲል በተቋጨበት መልኩ ተቋጭተው ወደ ምክክር ሊኬድ እንደሚገባ ይህ ሊሆን ባልቻለበት ኹኔታ የአገራችንን ቀጣይ እጣ ፋንታ ምናልባትም አገራዊ ምክክሩ ሳይሆን የጦርነቶቹ ሂደት ሊወስን እንደሚችል በተደጋጋሚ ጊዜያት በአገኘነው አጋጣሚ ኹሉ ሥጋታችንን በመግለጽ ምክረ ሀሳብ ስናቀርብ ቆይተናል።” ሲሉ ክለዋል፡:
ፓርቲዎቹ በደበዳቤያቸው “ክልሉ በዚህሁለንተናዊ ምስቅልቅል ውስጥ ባለበት ኹኔታ ተወካዮቻችንን ልከን በአጀንዳ ልየታ ተሳተፉ ማለት ሕወሓት ከከፈተው ጦርነት ጊዜ ጀምሮ በመከራ ውስጥ እያለፈ በሚገኝው የክልሉ ሕዝብ እንዲሁም የሚበሉት አጥተው አጽማቸው ገጥጦ የሚታዩ ሕጻናት ላይ እንደመሳለቅና በታሪክም የሚያስጠይቅ ጭምር በመሆኑ በተጠቀሰው የክልሉ የአጀንዳ ልየታ እንደማንሳተፍ ለኮሚሽኑ በአክብሮት እንገልጻለን።” ነው ያሉት፡
በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጡን ለኢትዮጰያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ታደሰ ደውለን የደብዳቤውን ይዘት መመልከታቸውን ጠቁመው በደብዳቤው ዙሪያ ከኮሚሽኑ ኃላፊች ጋር የጋራ ግንዛቤ ከያዙ በኋላ በቅርቡ ምላሽ እንደሚሰጡ አመልክተዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር