ሃኑካ እና ቤተ-እስራኤላዉያን በኢትዮጵያ
ሐሙስ፣ ጥር 1 2017
ሃኑካ ዘንድሮ በሰሜን ሸዋ ደብረ-ብርሃን ተከበረ
ታህሳስ 17 ቀን ፤ በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን (ቀበሌ 5) የሚኖሩ ቤተ-እስራኤላውያን የሁለተኛውን ቀን የሃኑካን በዓል የገዳማቱ አባቶች በተገኙበት በደብረብርሃን ሞፈር ቤት ወይም (ማረፊያ) ተብሎ በሚታወቀዉ ቦታ በደመቀ ሁኔታ ማክበራቸዉን በኢትዮጵያ ፅዮናዊ አራማጅ እና የአፍሪቃ አይሁዳዉያን የምርምር ጥናት ማዕከል አባል አቶ መስፍን አሰፋ ተናግረዋል። አይሁዶች የድል መታሰቢያ እና የተዓምር በዓል ብለዉ በየዓመቱ የሚያከብሩትየሃኑካ በዓል በአለፈዉ ዓመት መዲና አዲስ አበባአደባባይ ላይ በድምቀት መከበሩ የሚታወስ ነዉ። ሃኑካ በተለያዩ የዓለም ሃገራት ሃኑካ ሻምን በማብራት በአደባባይ ሲከበር ማየት የተለመደ ሆንዋል። ሃኑካ፤ በጥንት ዘመን የተፈጸሙ ታሪካዊ ክስተቶች አንዱ የሆነው የሃኑካ በዓል የአይሁድ ህዝብ በፈጣሪው መደገፉ፤ እንዳልጣለዉ ያሳየ የእግዚአብሔር ተአምር የታየበት ነው ሲሉ አይሁዳዉያን ይገልፁታል። ሃኑካ ለሳምንት የሚከበር በዓል ነው። በዓሉ የአይሁዳዊያን ወጎችን የሚያሳይ በእያንዳንዱ ቤት ለስምንት ቀናቶች በየቀኑ ሻማ በማብራት የሚከበር፤ የክብረ በዓሉ ወቅት ቅዝቃቄ በመሆኑ ቤትን የሚያሞቅ ክብረ በዓል በመባልም ይታወቃል። ለክብረ በዓሉ አይሁዳዉያን በዘይት የሚሰሩ ጣፋጭ ምግቦችን ይዘጋጃሉ። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ የዘይትን ተአምር ለማስታወስ እንደሆነ ይነገራል። በኢትዮጵያ ፅዮናዊ አራማጅ እና የአፍሪቃ አይሁዳዉያን የምርምር ጥናት ማዕከል አባል አቶ መስፍን አሰፋ በአይሁዳዉያን ዘንድ በየዓመቱ ለስምንት ቀናት ስለሚከበረዉ ሃኑካ በዓል ታሪካዊ ዳራ አጫዉተዉናል።
ሃኑካ መከበር ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ፤ ሮማዉያን የእስራኤላዉያንን ቤተ መቅደስ በማፍረሳቸዉ አይሁዳዉያን የሃኑካን ባህልላዊ ክንዉን ይዘዉ በመላዉ ዓለም መሰደድ መጀመራቸዉን አቶ መስፍ አሰፋ ተናግረዋል። ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አይሁዳዉያን ግን የሃኑካን ክንዉን አያቁትም ነበር ብለዋል። ምክንያቱ ደግሞ ከጦርነቱ በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸዉ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል።
እንደ አቶ መስፍን አሰፋ አሁን አሁን ኢትዮጵያ የሚገኙየቤተ እስራኤላዉያንከምንግዜም በላይ ሃይማኖታቸዉን እና ባህላቸዉን በአደባባይ እና በድፍረት እያከበሩ ይገኛሉ። ሃኑካ እና ፑሪም የተሰኙት የአይሁዳዉያን በዓላት በቤተ እስራኤላዉያን የሚታወቁ በዓላት አልነበሩም።ምክንያቱም ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አይሁዳዉያን ከጦርነቱ በፊት በመሰደዳቸዉ ነበር። ቤተ እስራኤላዉያን ሃኑካን እና ፒሪዮምን ማክበር የጀመሩት ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት ነዉ።
ይሁን እና የኢትዮጵያ ቤተ-እስራኤላዉያን ስግድ የሚባል የአይሁዳዉያን በዓልን ለዘማናት አቆይተዉ በአሁኑ ወቅት በመላ አይሁዳዉያን ዘንድ ይከበራል። እስራኤልም የስግድ በአልን በይፍ ብሔራዊ በአል አድርጋ ተቀብላለች ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁኑ ወቅት ወደ 300 ሺህ የሚሆኑ ቤተ እስራኤላዉያን የአይሁድ ሃይማኖትን በይፍ ይተገብራሉ ከነዚህ መካከል 14 ሺህ ተቀባይነትን አግኝተዋል። ሌሎቹ ከእስራኤል መንግሥት መልስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። አብዛኞቹ የሚገኙት በሰሜን ሸዋ አዲስ አበባ እና አካባቢዋ፤ በጎንደር በደቡብ ትግራይ እና በሰሜን ወሎ ራያ ዉስጥ ነዉ።
በ 1980ዎቹ ከሰሜን ወሎ በረሃብ ምክንያት ተፈናቅለዉ ወለጋ ዉስጥ ለአስርተ ዓመታት ይኖሩ የነበሩ ፤ ቤተ እስራኤላዉያን በኦነግ ሸኔ ጥቃት ተፈናቅለዉ ፤ ገሚሱ ወደ ሱዳን ተሰደዋል፤ ገሚሶቹ ደግሞ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመጠለያ ጣብያ ይኖራሉ። እነዚህ ማህበረሰቦች ወለጋ ዉስጥ የዛሬ ሰባት ዓመት ገንብተዋቸዉ የነበሩ ሁለት ትልልቅ ሙክራቦችም በኦነግ ሸኔ ተቃጥለዋል።
«እዉቅና አግኝተዋል ተብለዉ በመዝገብ የተያዙት፤ ወደ 14,000 ነበሩ፤ ከነሱ መካከል ወደ እስራኤል ሄደዉ ወደ 10 ሺህ የሚሆኑት በጎንደር እና አዲስ አበባ በሚገኘዉ ጣብያ ጉዞዋቸዉን እየተጠባበቁ ይገኛሉ። ከዚያ ዉጭ ግን እንደ ጺዮናዊነት፤ እኛ ተንቀሳቅሰን ባደረግነዉ ጥናት፤ በኢትዮጵያ ዉስጥ በአሁኑ ሰዓት ወደ 300 ሺህ የሚጠጉ ቤተ-እስራኤላዉያን ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ቤተ እስራኤላዉያን ነን የሚል ጥያቄ አንስተዋል። አይሁዳዊ ስርዓትንም ማክበር ጀምረዋል። ለምሳሌ ደቡብ ትግራይ ራያ ላይ፤ ፀሎት ቤት ተከፍቷል። እዝያ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ህጋዊነት አግኝተዉ የመቀብር ቦታ ሁሉ ተሰቷቸዋል። ደቡብ ወሎ ላይ ላሊበላ አካባቢ የሚገኙ ቤተ-ስራኤላዉያን ነን የሚሉ ማህበረሰቦች ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ደቡብ ትግራይ ላይም እንዲሁ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ስለዚህ በሰሜን ሸዋ ላይ የሚገኙትን ቤተ-እስራኤላዉያንን ጨምሮ ኢትዮጵያ ዉስጥ ወደ 300 ሺህ የሚሆኑ ቤተ እስራኤላዉያን ይገኛሉ።
አዲስ አበባዉ ዉስጥም ሆነ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስንት የቤተ- እስራኤላዉያን ፀሎት ቤት ማለትም ሙክራብ ይገኛል?
« በአጠቃላይ ሰባት ሙክራቦች ይገኙ ነበር። አዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ እዉቅና የተሰጣቸዉ ሦስት ሙክራቦች ይገኛሉ። መገናኛ አካባቢ የሚገኝ እና ሌላዉ ቀጨኔ መድሐንያለም አካባቢ ሁለት ሙክራቦች አሉ። ደብረብርሃን ላይ ይም ሌላ ሙክራብ ይገኛል። እዚህ ላይ መናገር የምፈልገዉ፤ የዛሬ ስድስት እና ሰባት ዓመት ላይ ሁለት ሙክራቦች ወለጋ ዉስጥ ሰርተን ነበር። እነዚህ ወለጋ ላይ ታንፀዉ የነበሩት ሙክራቦች በይፋ የአይሁድ ስርዓት ይከናወንባቸዉ ነበር። ሙክራቦቹ ከሰሜን ወሎ ዉስጥ የዛሬ 40 ዓመት ግድም በረሃብ ምክንያት በሰፈራ ወደ ወለጋ የሄዱ ቤተ-እስራኤላዉያንማህበረሰቦች ሃይማኖታዊ ክንዉኖችን የሚያካሂዱበት ነበር። እነዚህ ማህበረሰቦች በገነቧቸዉ ሁለት ሙክራቦች ለሁለት እና ለሦስት ዓመታት ሃይማኖታዊ ስርአቶችን ያከናዉኑባቸዉ እና ይገለገሉባቸዉ ነበር። ይሁን እና በአካባቢዉ ላይ ኦነግ ሸኔ የተባለዉ ታጣቂ ቡድን በሚያደርሰዉ ጥቃት አካባቢዉ ላይ ለአስርተ ዓመታት ይኖሩ የነበሩት ቤተ እስራኤላዉያን ተፈናቅለዋል፤ ቤተ መቅደሶቹም ኦነግ ሸኔ በተባለዉ ታጣቂ ቡድን የዛሬ ሁለት አመት ተቃጥለዋል። እነዚህ ማህበረሰቦች ገሚሱ ወደ ጎረቤት ሱዳን ገብተዋል ገሚሶቼ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተሰደዉ በመጠለያ ጣብያ በመኖር ላይ ይገኛሉ። እናም ኢትዮጵያ ወለጋ ዉስጥ የተቃጠሉትን ሁለት ሙክራቦች ጨምሮ በአጠቃላይ ሰባት ሙክራቦች ይገኙ ነበር። አምስቱ ዛሬም በግልጋሎት ላይ ናቸዉ። ሁሉም ሙክራቦች ባለፉት 20 እና 25 ዓመታት የጺዎናዊነት እንቅስቃሴን ከጀመርን በኋላ የከፈትናቸዉ ወይም ያነጽናቸዉ ናቸዉ» በኢትዮጵያ ፅዮናዊ አራማጅ እና የአፍሪቃ አይሁዳዉያን የምርምር ጥናት ማዕከል አባል አቶ መስፍን አሰፋ ተናግረዋል። አቶ መስፍን አሰፋን በDW ስም እያመሰገንንን፤ ሙሉዉን ጥንቅር የድምጭ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ