ከመቅደላ እስከ በርሊን
ማክሰኞ፣ ግንቦት 10 2013ከትምኖርበት ከጀርመን ፣ሀገር ቤት የሚገኙ የጾታዊ ጥቃት ሰለባዎችን እንዲሁም በአረብ አገር የሚገኙ ሴት ኢትዮጵያውያን ለመርዳት የተለያዩ ጥረቶችን ታደርጋለች። ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ገንዘብ ማሰባሳብ፣ ባለሞያዎችን ለበጎ አድራጎት ስራ ማስተባበር ከጥረቶቿ መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ።በራስዋም የደረሰው፣ ጾታዊ ጥቃት፣ በኔ ይብቃ፤ ስደትም በኔ ይብቃ ስትል የጀመረቻቸው ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች አሁን ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል።ከመካከላቸው በቅርቡ መሠረቱ የተጣለው የህጻናትና የሴቶች የህክምና ማዕከል አንዱ ነው።ሌሎች እቅዶችም አሏት።
ደቡብ ወሎ መቅደላ ማሻ አደሁያ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ስትወለድ የወጣላት ስም ሙሉጠየህ ነው፤ ሙሉጠሃይ ክብረት ፋሪስ ።ከዛሬ 10 ዓመት ወዲህ ግን ሃያት መሐመድ አሊ ሆኗል መጠሪያዋ ። ለምን_የምትሉ ከኛ ጋር ከቆያችሁ ምክንያቱን ትነግረናለች።ሃያት ከትውልድ መንደሯ ከተሰደደች በአጠቃላይ 18 ዓመት ሆኗታል።የሃያት ስደት የሚጀምረው በሃገር ቤት ገና በ13 ዓመቷ ነው ያኔ ቤተሰቦቿ ሊድሯት ሲዘጋጁ ጠፍታ አዲስ አበባ ሄደች።እዚያ ደግሞ ሌላ ያልጠበቀችው ችግር ገጠማት። ከነበረችበት ቤት አምልጣ በአቅራቢያው በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ያገኟት ጥበቃ ላይ የነበሩ ወታደሮች ለምን እዚያ እንደመጣች ጠይቀዋት ችግሯን ሲረዱ፣ ወደ ካምፓቸው ወስሰዷት።በማግስቱ ስትመረመር ነፍሰ ጡር መሆናዋ ታወቀ።እነርሱም አስጠግተዋት በሄዱበት ይዘዋት እየሄዱ ሲረዷት ከቆዩ በኋላ ሃያት በድብቅ ውሳኔ ላይ ደረሰች።ያኔ የፈጸመችውን ልጅ በመሆኔ ያደረግኩት ነው ትላለች ።ሃያት እንደምትለው መጀመሪያ ለመሄድ የተዘጋጀችው ሱዳን ሳይሆን ወደ ሌላ አረብ ሃገር ነበር። ይህን ያሰበችውም ነፍስ በጠፋበት ወንድሟ ምክንያት እርስዋን ጨምሮ ቤተሰቡ በሙሉ ችግር ላይ በመውደቁ ነው ትላለች።በአካባቢው ባህል ሊከተል የሚችለውን ደም መቃባት ለማስቀረት ገንዘብ ለማግኘት ወደ ሱዳን ተሰደደች።በ2002 ዓም ሱዳን የሄደችው ሃያት በዚያ ለተወሰኑ ዓመታት ሕጋዊ ሆና መኖርዋንና መስራትዋን ትናገራለች።ሱዳን እንደገባችም የርስዋን ቁስል የሚቀሰቀስ ነገር አጋጠማት
ሃያት ሱዳን 5 ዓመት ከቆየችች በኃላ ኢትዮጲያ ለመኖር ወስና ብትመለስም ሁኔታዎች ሳይመቻቹላት በመቅረታቸው እንደገና ወደሱዳን ሄደች ሕገ ወጥ በሚባለው መንገድ።ሱዳን ጥቂት ዓመት ከሰራች በኋላ በአደገኛ የበረሃ ጉዞ ወደ ሊቢያ አቀናች።ሊቢያም ታስራ ገንዘብ ሰትሰጥ ከተለቀቀች በኋላ በሕገ ወጥ ደላሎች አማካይነት ህይወቷን ለአደጋ አጋልጣ በሜዴትራንያን ባህር በለንቋሳ ጀልባ አውሮጳ ገባች ኢጣልያ።ከኢጣልያም ወደ ፈረንሳይ ተሻግራ በመጨረሻ ጀርመን ጥገኝነት አገኘች።ይህ አውሮጳ የመጣችበት የስደት ጉዞዋ ጠቅለል ብሎ ሲነገር እንጂ፣ በመካከሉ ሃያት የደረሰባት ስቃይ፣ ያጋጠማት ውጣ ውረድ ቀላል አልነበረም።
ሃያት ጀርመን መኖር ከጀመረች የፊታችን መስከረም ሰባት ዓመት ይሆናታል።ዋና ከተማዋ በርሊን ነው የምትኖረው።ጀርመን በመድረሴ እድለኛ ብሆንም ግን እዚህ ከመጣሁ በኋላ ብዙ ፈተና ደርስብኛል ትላለች
ኢትዮጵያ በደረሰባት ጾታዊ ጥቃት የጤና እክል የገጠማት ሃያት ጀርመን ባገኘችው ህክምና በኋላ ተሽሏት አሁን የልጅ እናት ናት።ያገኘችው የስነ ልቦናዊ ድጋፍና የኢትዮጵያውያንም እገዛ አሁን ላለችበት ደረጃ እንዳበቃት ትናገራለች።ሃያት ጀርመን ደረስኩ ብላ እጅዋን አጣጥፋ አልተቀመጠችም።በርስዋ የደረሰ በሌሎች ወገኖቿ ላይ እንዳይደርስ እየጣረች ነው።
ሃያት በትውልድ ስፍራዋ በመቅደላ ወረዳ ማሻ ቀበሌ የህጻናትና ሴቶች የጤና ችግሮችን ለመከላከል ሆስፒታል የመስራት ሃሳብ ጠንስሳ ሥራው ተጀምሯል። የአካባቢው አስተዳደር ፣በጎ ፈቃደኞች የአካባቢው ህብረተሰብ ፣ ቃል-ኪዳን የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትና ሀያት በዋናነት በሚሳተፉበት ጥረት በማሻ ለማዕከሉ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።ዶክተር ሩት ምትኩ ቃልኪዳን በመባል የሚጠራው የህጻናት ጤና እንክብካቤ ድርጅት የበላይ ሃላፊ ናቸው። ሃያት ሆስፒታሉን ለማስገንባት የሁሉም ኢትዮጵያውያንን እገዛ ያስፈልጋል ትላለች።ሃያት ከዚህ ሌላ በሃገር ውስጥ የመሰረተችው ስንቅ የበጎ አድራጎት ድርጅትም ትናንት ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቷል።እዚህ ጀርመን ሆና በተለያዩ የአረብ ሃገር ላሉ ሴት ኢትዮጵያውያንንም ልዩ ልዩ ድጋፎችን ትሰጣለች ።የስደት ተሞክሮዋን ያካፈለችበት «የማይደርቅ ቁስል የማይድን በሽታ« ስትል ርዕስ የሰጠችውን ከመቅደላ እስከ በርሊን የሕይወት ጉዞዋን የሚያስቃኝ ባለ አራት መቶ ገጽ መጸሀፍ ጽፋ እርማትና ማሳተም እንደሚቀረው ተናግራለች።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ