1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሃይማኖት ተቋማት የሰላም ጥሪ በምዕራብ ኢትዮጵያ የዜጎች ጭፍጨፋ በአማራ ከተሞች የሰዓት እላፊ

ዓርብ፣ ነሐሴ 27 2014

በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉ፤ በትግራይ ክልል የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ያስተላለፉት የሰላም ጥሪ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች፤የተመድን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት መንግሥታት፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ዳግም የጀመሩትን ጦርነት እንዲያቆሙ እየወተወቱ ነዉ።

Uganda | Smartphone Nutzerin in Kampala
ምስል ISAAC KASAMANI/AFP/Getty Images

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

ሰሞኑን እንደ አዲስ የተቀሰቀሰውን የሰሜን ኢትዮጵያዉን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል። የሰዓት እላፊ ገደብ ከተጣለባቸዉ ከተሞች መካከል ደሴ፤ ደብረ ብርሃን፣ ሰቆጣና ኮምቦልቻ ከተሞች ይገኙበታል።  በሌላ በኩል የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚኖሩበትን የዩንቨርስቲዉን ቅፅር ግቢ እየለቀቁ መሆኑን ከባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።    

ክፍሌ ማሞ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ የተፈጥሮና ሠው ሰራሽ ችግሮች፤ በተከሠቱበትና ችግሮቹ ይከሠቱባቸዋል ተብለው፤ በሚገመቱ ቦታዎች ሀገሮች ሁሉ፤ ልዩ ልዩ አዋጆች ይደነገጋሉ ። ስለዚህ እነዚ ሰዓት እላፊ የተደነገገባቸው ቦታዎች እና፤ ሁኔታዉ ይህን ያህል የሚጋነን ዜና አይደለም ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል። 

እኛ ደሴዎች ወገናችንን ለማስተናገድ አንደክምም አብሽሩ ወገኖቸ አይዞችሁ ያልፍል ያሉት ደግሞ ሰላም ሞሐመድ ናቸዉ።  ሕዝቡ ሸሽቶ ሸሽቶ የት ሊደርስ ነው ? መንግስትም ማረጋጋት አለበት። ሕዝቡም ተረጋግቶ አካባቢውን ይጠብቅ ሲሉ ምክር አዘል አስተያየታቸዉን የሰጡት ጆን ሰርቤሳ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ናቸዉ። 

ምስል Diptendu Dutta/AFP

ፌኩ መና የተባሉ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ« ሰላም እርቅ ይሸለናል። እኛ ኢትዮጵያውያን ነን ።ሞት መፈናቀል ይብቃ። ለሌላው ጥሩ ምሳሌ እንሁን ። ፈጣሪ ሰላሙን ይስጥልን» ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። 

ፈጅቶ ከሚያጠግበኝ እስኪበርድ ይራበኝ እባላለሁ ብለዉ መለያ ስማቸዉን ያስቀመጡት የፌስቡክ ተከታታይ «ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይበልጣል የሚለውን፤ የአባቶቻችንን አባባል ሳንረሳ፤ ወደ የትም ቦታ ባለመፈናቀል ለሰራዊቱ ደጀን መሆን አለብን፤ ለጠላት በር አንክፈት» ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል። 

ሚሚ ላቭ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በአስተያየታቸዉ «ትግራዋይ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች የት ነው ያሉት ብላችሁ ጠይቁ እስቲ። እናቱ የሞተችበት እና ገበያ የሄደችበት እኩል ያለቅሳል ነው ነገሩ።» ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። ነገሰ ተስፋ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ «አዎ ተማሪዎች ሜዳ ላይ ተበትነዋል፤ ማንም ጠያቂ የላቸዉም ወዴት ናችሁ የሚል የለም። ትራንስፖርት የለም። እጅግ ከባድ ነው »ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል። 

«እኔኮ የሚገርመኝ ሰው ሲኖር ነው የሚማረው ምን ዋስትና ኖሯችሁ ነው በየክልልሉ ለመማር የምትሄዱት» ሲሉ የሚጠይቁት ትዝታ ኃይሌ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸዉ።  ሰለሞን ታደሰም ይጠይቃሉ በአስተያየታቸዉ« ተማሪዎቹ ዩንቨርስቲዉን ለቀዉ የመዉጣት መብት አላቸዉ ግን አሁን ዩንቨርስቲ ዝግ አይደለም እንዴ ወዳጆቼ? »ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። 

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በትግራይ ክልል የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ባለፈው ሳምንት ያስተላለፉት የሰላም ጥሪ እንዳስደሰተው ገልጿል። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ብሎም የተመድን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት መንግሥታት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚወዛገቡት እና አሁን ደግሞ ዳግም ጦርነት የጀመሩት መንግሥት እና ህወሓት ጦርነቱን እንዲያቆሙ እየወተወቱ ነዉ።  የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበርም የሰላም ጥሪን አስተላልፏል። 

ምስል Nasir Kachroo/ZUMA Press/imago images

ሚኪያስ አቡ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ሠላም ለኢትዮጵያውያን፤ ሙሉ ሠላም ለትግራይ ህዝብ፤ ጦርነት ይብቃን ሠላም ይሻላል፤ በጦርነት የማሻነፍ ኃይል የለም» ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። 

«አልኩ ለማለት ያህል ካልሆነ መከላከል መቼም የግድ ነው።ማን ጦርነት የወዳል።» ሲሉ አስተያየታቸዉን ያስቀመጡት ደግሞ ቢራ ጫላ የተባሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ ናቸዉ። ነብዩ ሃይሚ ታደሰ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ፤ የአስተማሪዎች ማኅበር ወሬ ብቻ ነዉ።  መጀመሪያ የሙያ ማህበሩ የሰራተኞቹን ጥቅማጥቅም ያስከብር» ብለዋል በአስተያየታቸዉ። በሌ ዘነበ የተባሉ የፌስኑክ ተከታታይ ፤ ኢሰመኮ የይስሙላ ተቋም ተፅኖ ማድረግ የማይችል ሆኖ አግንቸዋለሁ። ህፃናት ጦርነት ላይ ሲውሉ ለዓለም ማህበረሰብ ማሳየት የማትችሉት ለምድን ነዉ» ሲሉ አስተያየታቸዉን በጥያቄ ደምድመዋል። 

አስፋለይ ገብረአረጋዊ የተባሉ ተጠቃሚ «እነዚን የመሳስሉ ተቋማት ከእዚ በፊት ጦርነት እንደይደረግ ቢጡሩ ነበር ጥሩ።  ያንሁሉ ጥፋት እና መክራ አናይም ነበር። አሁንም ጦርነቱ እንዲቆም ግፊት ይደረግ። ስልክ፣መብራት፣ባንክ ፣መዳሐኒት ይክፈት። ጦርነት  ይቁም፤ ብለዋል በአስተያየታቸዉ።»

አባድ አባድ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ በበኩላቸዉ «የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እባካችሁ እዚህ እስራችሁ ጉራጌ ክልል ያለውን አፈና እስራትና ሰብአዊ ጥሰት ሳይቃጠል በቅጠል ድረሱልን። ሰው ከሞተ፤ ንብረት ከወደመ በዃላ ማልቀሱ ዋጋ የለውም። ፍትህ ፍትህ ለጉራጌ ክልል ማህበረሰብና አመራር እንደራሴዎች» ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።  

ደነቀ ዳና የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ፤ «አሁንም እላለሁ ሰላም ይሻላል። ሁለቱም የፖለቲካ መሪዎች ችግሮቻቸዉን ለመፍታት ወደ ሰላም መምጣት አለባቸው። ለኢትዮጵያ ህዝብም ሰላም ይሻላል። የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች አሁንም ትልቅ ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ ሰላም ሰላም ለሀገሬ ኢትዮጵያ» ሲሉ አስተያየታቸዉን በቃል አጋኖ ደምድመዋል። 

በምዕራብ ኦሮሚያ  ለአማራ ተወላጆች ጥበቃ አልተደረገም ሲል ሂውማን ራይትስ ወች በዚሁ ሳምንት መንግስትን ተቸቷል። በምዕራብ ኦሮሚያ ሰኔ 2022 የታጠቀ ቡድን በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆችን ሲገድል የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ከጥቃት ለመከላከል ያደረጉት ጥረት ብዙም አልነበረም ብሏል ድርጅቱ። ከሦስት ወራት ገደማ በኋላ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በህይወት ለተረፉ ነዋሪዎች እንኳ በቂ የመጠለያ፣ የጤና እና የደህንነት ጥበቃ  ስጋቶችን መፍታት አልቻለም ሲል ነዉ ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግስትን የወቀሰዉ። እንደ ድርጅቱ  ያለፈው ሰኔ 18 ቀን ለስምንት ሰአታት በዘለቀው ግድያ በቶሌ እና በሰኒ ቀበሌዎች  በሚገኙ መንደሮች በርካታ ሴቶችና ህፃናትን ጨምሮ ወደ 400 የሚጠጉ የአማራ ተወላጆችን ታጣቂዎች በጥይት ገድለዋል።   

ጳውሎስ ወሎ ቴክ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በአስተያየታቸዉ «የኦሮሚያ ክልል መንግስት ይህ ክፉ ጊዜ ያልፋል ብለን እንጅ አማሮች ላይ የሚሰራው ግፍ ታሪክ የማይረሳ  የቆሸሸ ጠባሳ ነው ።» ሲሉ ጽፈዋል።  ሶሪ ኬንታ ቦካ የተባሉ በበኩላቸዉ«በምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በፋኖ ከቀናት ጀምሮ ንፁኃን እየተጨፈጨፉ እየተፈናቀሉ ንብረታቸው እየወደመባቸው ቤት እያቃጠሉ መንግስት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል። Human Rights watch ይህንንስ አያይም» ሲሉ ጽፈዋል።    

ምስል Kirill Kudryavtsev/AFP via Getty Images

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ከቶሌ ቀበሌ ቢያንስ 4,800 ሰዎች ከምዕራብ ኦሮሚያ ደግሞ ከ500,000 በላይ የሚሆኑ ተፈናቅለዋል ብሏል። እንደቀልድ ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን የፃፉት ጆሲ ዜና ናቸዉ።  ሪች ጌታሁን በበኩላቸዉ«አጀንደችውን በደንብ ጠንቅቀን እናውቃለን።  እስከዛሬ የት ነበረ ነገሩ የሆነው ከወራቶች በፊት ነዉ። አውን በዚህ ሰዓት ይሄንን አጀንዳ ማንሳት ማለት የህዝቡን አንድነት ለመሸርሸር እና አቅጣጫ ለማስቀየር ነው ። ተውት ተነቅቶባቸዋል አትልፉ» ብለዋል። 

ፋይዱ አብዱላ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ «ያለቁት ህፃናት ና ሴቶች ገበሬዎች ለምን እንደተገደሉ እንኳን የማያውቁ ናቸው። ግን የሰው ልጅ በምን ሞራል ነው የወራት ዕድሜ ያለውን ህፃን የሚረሽነው? አራስ ሴትን በምን አቅም ነው የሚረሽነው ? አሁን ይሄንን የፈፀመ አካልን ሰው ማለትስ ይቻላል? ያረቢ በበዳዮች ምክንያት አትቅጣን። ያረቢ በዳዮችን ባሉበት ያዝልን። ህመማቸውን ሀዘናቸውን አሳየን። እኔማ የሆነው ሁሉ ከአይምሮዬ በላይ ነው። አላህ የሁሉ ተመልካች ነው። በሀገሬ ግፍ ሞልቶ ፈሷል። አንተው እየን» ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። 

ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉu።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW