1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ሃገራዊ ምክክር በአሜሪካና ካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር

ሐሙስ፣ ጥር 9 2016

በኢትዮጵያ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት፣ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ። ኮሚሽኑ ጥሪውን ያቀረበው በአሜሪካና በካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ ነው።

Äthiopien Kommission für den nationalen Dialog
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር የበይነ-መረብ ውይይት

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት፣ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ጥሪ አቀረቡ። ዋና ኮሚሽነሩ፣ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ጥሪውን ያቀረቡት፣ ኮሚሽኑ በአሜሪካና በካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ ነው።  

የውይይቱ ዓላማ በዋና ኮሚሽነሩ

ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንዳሉት፣ ከዚህ ቀደም ኮሚሽኑ በእስያ፣አውስትራሊያና ኒውዚላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር፣በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ላይ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ዐሳቦች የተንጸባረቁበት ውይይት አካሂዷል። በዚህኛው ውይይት ደግሞ፣ ኮሚሽኑ በአሜሪካና ካናዳ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ራሱን  በማስታወቅ፣ በሃገራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ  ስለሚኖራቸው ተሳትፎና ድጋፍ ለመመካከር የበይነ መረብ ውይይት ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

"የዛሬው ስብሰባ ዋነኛ ዓላማ፣እኛን ወደ እናንተ ለማስተዋወቅ፣ እናንተን ደግሞ ወደኛ ለማምጣት እና ከእናንተ ምክረ ዐሳቦችን ለመውሰድ ነው።"

በኢትዮጵያ ሃገራዊ መግባባት ባልተያዘባቸው ጉዳዮች ላይ ተመካክሮ መግባባት ይቻል ዘንድ፣በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን ገንቢ አስተዋጾ ማድረግ እንደሚገባቸው ዋና ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።

የኮሚሽኑ አደረጃጀትና የባለድርሻ አካላት ልየታ

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ፣የሚያካሂደው እንቅስቃሴ የዘገየ ነው በሚል አስተያየት ሲሰጥ ይሰማል። ፕሮፌሰር መስፍን ግን፣ ኮሚሽኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ራሱን ለማደራጀት ሲሰራ መቆየቱን ለውይይቱ ተሣታፊዎች በሰጡት ገለጻ አስረድተዋል።

  የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርአያ ፎቶ ከማኅደርምስል Solomon Muchie/DW

"የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ሲጀምር ካደረገው ነገር አንዱ፣የቅድመ ዝግጅት ጊዜ ቢሮ ማቋቋም፣ባለድርሻ አካላትን በየክልሉ ሄዶ በመለየትና በትልልቅ ደረጃ ያሉትን ልዒቃን በሚገባ በማነጋገርና ዓለም አቀፉ ማኀረሰብ ጭምር በማነጋገር ነው ሥራውን የጀመረው።"

ሃገራዊ የመግባባት ጥያቄ በኢትዮጵያ

የኮሚሽኑ አባል የሆኑት ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው፣ የሀገራዊ መግባባት ጥያቄ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ሲጠየቅ የኖረ ጥያቄ ቢሆንም ምላሽ ሳያገኝ ለብዙ ጊዜያት መቆየቱን አውስተዋል።

"በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዚህች ሀገር የሚበጃት ሀገራዊ መግባባት ለመምጣት የሚያስችል ምክክር ነው ብለው ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተው ነበር፤ይኼ ግን ምላሽ አላገኘም በተለያዩ ምክንያቶች።አሁን ግን ጊዜው ፈቅዶ ሊሆን ይችላል፣ይኼ ጥያቄ ያው በመንግስትም በኩል ተቀባይነት አግኝቶ፣ተቀባይነት አገኘ የምንለው አዋጅ እንዲወጣ በመፈቀዱ፣ይኼ አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።"

የኮሚሽኑ ተቀባይነትና ተአማኒነት

በውይይቱ ላይ ገለጻ ካደረጉ ኮሚሽነሮች መኻከል፣አምባሳደር መሐሙድ ድሪር፣ኮሚሽኑ ተቀባይነትና ተአማኒነትን በማረጋገጥ፣ መሰረታዊ በሆኑ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያካሂድ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ፤ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያምስል Solomon Muchie/DW

"የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅርቡ በአዲሱ ዓመት፣የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።ይኼ የጋራ መግለጫ በሚያማክላቸው ምክር ቤት  አማካይነት የወጣ ነው። ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር አብረን እንሰራለን የሚል ነው።የኼ በጣም የሚደገፍ ከዚህ ቀደም ያልነበረ፣ እንደተባለውም በሂደት ውስጥ ተአማኒነትንና ተቀባይነት ለማረጋገጥ እንጥራለን። መሠረታዊ በሆኑ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ነው ለማወያየት የምንሻው።"

በውይይቱ ላይ፣ ስለ ሀገራዊ ምክክር መሠረታዊ ጽንሰ-ዐሳብ፣ኮሚሽኑ ስለተቋቋመበት ዓላማ፣ ስለሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ፣ እንዲሁም ኮሚሽኑ ስለሚከተለው የአሰራር ሥርዓትና ዋና ዋና ተግባራት፣ በኮሚሽኑ አባላት ገለጻ ተሰጥቷል። ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያኑም፣ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር በሚሰሩባቸው መንገዶች ላይ ሰፊ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፣ የተለያዩ ምክረ ዐሳቦችንም ሰንዝረዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW