1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ህልማቸውን በቀለም፣ ሸራና ቡርሽ የሚስሉ ወጣቶች

ኢሳያስ ገላው
ዓርብ፣ መስከረም 9 2018

ወጣቶች በነጻ የሥዕል ጥበብን የሚቀስሙበት የሥዕል ክለብ በአማራ ክልል ደሴ ከተማ ይገኛል። ፓሌት የወጣቶች የሥዕል ክበብ በርካታ ወጣቶች በውስጣቸው የተቀበረው የሥዕል ጥበብ እንዲወጣ ምክንያት መሆኑን ይናገሩለታል።

ፓሌት የሥዕል ስቱዲዮ
በአማራ ክልል ደሴ ወጣቶች በነጻ የሥዕል ጥበብን የሚቀስሙበት የሥዕል ክለብ ፓሌት የሥዕል ስቱዲዮምስል፦ Essays Gelaw/DW

ህልማቸውን በቀለም፣ ሸራና ቡርሽ የሚስሉ ወጣቶች

This browser does not support the audio element.

 

ቀለምን ከሸራ ጋር አዋህደው ህልማቸውን እውን ለማድረግ ባለፉት አራት አስርት ዓመታት በዚች ደሳሳ ቤት ውስጥ በርካታ ወጣቶች ፈፅመውታል፡፡ በኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ እድገት ውስጥም የራሳቸው ዘይቤ ይዘው የመጡ ወጣት ሠዓሊያንን በማፍራት ፓሌት የሠዓሊያን ክበብ የበኩሉን አስተዋጽዖ አበርክቷል።የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ መምህር ሠዓሊ መክብብ ገ/ፃዲቅ የእጅ ውጤት ያረፈባቸው ወጣት ሠዓሊያን በየዘመኑ ያፈራው ፓሌት የሠዓሊያን ክበብ አሁን በኢትዮጵያ ላሉ የሥዕል ጥበብ ትምህርት ቤቶች ማለትም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የተፈሪ መኮነን፣ የአለ ፈለገ ጥበብ ት/ቤቶች እና ሌሎች ተቋማትን በመሪነት እና በመምህርነት የሚያገለግሉ ወጣቶችን አፍርተዋል። መዳረሻቸውን በብሩሽ እና በቀለም የሚያሳምሩት ወጣቶች በየዕለቱ በፓሌት የሠዓሊያን ክበብ ራሳቸውን ይቀርፃሉ። ወጣት ሄኖክ ጌታቸው ከእነዚህ አንዱ ነው።

«በኮረና ጊዜ የምሠራው አልነበረኝም በዚያን ጊዜ ያገኘሁት ፓሌትን ነበር። ፓሌት ባይኖር ኖሮ ምን እንደምሆን ሳስበው ግራ ይገባኛል። ግን ፓሌት የሚገርም ቦታ ነው። ምንም ያህል ደረጃ መሄድ እንዳለብኝ ዓለምን ምን ያህል ደረጃ እንደደረሰ ያወቅኩት ፓሌት ስለገባሁ ነው።»

በነፃ የሚሰጠው የሥዕል ጥበብ ትምህርት

የጥበብ ነፃነትን በነፃ ለወጣቶች የሚያጋባው ፓሌት የሠዓሊያን ክበብ የሥነ-ሥዕል ፍላጎታቸውን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚተጉ ወጣቶች መዳረሻ ነው። አሁን ወጣቶቹ ዓለም የደረሰበትን የአሳሳል ስልት በመማር ለጀማሪ ሠዓሊያን ያስተምራሉ ይላል ወጣት ክብሩ ይስፋ ካሣ የክበቡ ሰብሳቢ።

«ፓሌት ለአንድ ሠዓሊ የጥበብ መተንፈሻ ናት ብየ ነው የማምነው እኔን ጨምሮ እዚህ ለሚሠሩ ወጣቶች በነፃነት ገብተው ወጥተው የሥነ-ጥበብ ፍላጎታቸውን በሥነ ሥርዓት የሚሳድጉበት ትልቅ ስቱዲዮ ነው። በጣም ነፃነት ስላለ አካዳሚ ስቱዲዮ የሚል ሃሳብ በመፍጠር ሰዎች ለሥነ ጥበብ ማርክ አይሰጠውም በሚል እሳቤ በነጻነት እንዲሠሩ በአጭር ጊዜ ፍላጎታቸውን እንዲሳድጉ የሚሠራ ነው ፓሌት።»

ወደ ፓሌት የሠዓሊያን ክበብ የሚያቀኑ ወጣቶች የሥዕልን ጥበብ መማር እስከፈለጉ ድረስ ምንም ዓይነት ክፍያ የለባቸውም። ብቻ በዚህ ነፃ ክፍል ውስጥ ያሰቡትን መሳል ከፍ ወዳለም ደረጃ መሸጋገር ነፃ ፈቃድ አለው።

«በነፃ አስተምሮ ወረቀት እዚህ ነው የሚሰጥህ ራሱ ነው የሚያስተምርህ፤ ከዚያም በራስህ ነው የምትለወጠው። ነጻነት ባይኖር ክፍያ ይኖር ነበር፤ ራስህ ነው እንደፈለክ መጥተህ ሥራህን አልሠራህ ሠራህ የሚናገርህ የለም፤ ግን የሚመጣው የሚሠራ ሰው ነው 24 ሰዓት ክፍት ነው። ከዚህ በላይ ነፃነት የለም።»

«በኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ እድገት ውስጥም የራሳቸው ዘይቤ ይዘው የመጡ ወጣት ሠዓሊያንን በማፍራት ፓሌት የሠዓሊያን ክበብ የበኩሉን አስተዋጽዖ አበርክቷል።» ፓሌት የሥዕል ስቱዲዮ ደሴምስል፦ Essays Gelaw/DW

በፓሌት የሥዕል ክበብ ሰልጥነዉ ዓለም አቀፍ የሥዕል አዉደርዕይ የሚያቀርቡ በርካቶች ናቸው

አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የ1ኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ናትናኤል ሽፈራው የሥዕል ጥበብን በከፍተኛ ትምህርት ቤት ለመማር የበቃው በዚሁ በፓሌት የሠዓሊያን ክበብ ተምሮ ነው። እናም ፓሌት የወደፊቱን መንገዴን አሳምሮልኛል ይላል። «1 ዓመት የፋይን አርት ተማሪ ነኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ ፓሌት በጣም ትልቅ ጥቅም አለው። እውነት ለመናገር ከሌሎች የተሻለ አቅም እናሳያለን፤ ጥሩ ስኪል ይዘን እንሄዳለን ጎልተንም እንታያለን።»

በበርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮች በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ የሥዕል ሥራዎቹን የሚያቀርበው እና በተፈሪ መኮነን የሥነ-ጥበብ ት/ቤት መምህር የሆነው ሠዓሊ ኃይሉ ክፍሌ በማህተም የመሳል ዘዴን በስፋት ያስተዋወቀ ሠዓሊ ነው። ሠዓሊው የተገኘው ከፓሌት የሠዓሊያን ክበብ ሲሆን ለበርካታ ሠዓሊያን ስኬትም ፓሌት እና ቀስተ ደመና የሠዓሊያን ክበቦች አስተዋጽዖ እንዳበረከቱ ይናገራል።

«የአማተር የሥዕል ሂደት ለእኔ ብቻ ሳይሆን ከደሴ ለሚመጡ ሠዓሊያን ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፤ 25 ተማሪ ለመቀበል አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ጥበብ ት/ቤት 900 እና 1000 ተማሪ ሊያመለክት ይችላል። በዚያ ፈተና መሀል ከደሱ አማተር የምንሄር ተማሪዎች በቀላሉ ነው የምናልፈው። ያስቆሙናል ፈታኞቹ ያ ክበብ ምን ያህል ለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ምስክሮች ነን።»

የቀደምቶቻቸውን ፍኖት የሚከተሉ ወጣቶች

ዛሬ በፓሌት የሠዓሊያን ክበብ ውስጥ የሚሠሩ ወጣቶች ቀደምቶቻቸው የደረሱበትን ስኬት በመመልከት ራሳቸውን ለተሻለ ስኬት ለማብቃት ይሰራሉ።

«እዚህ ደሳሳ ጎጆ እየሠራህ ቀደምቶቹን በማየት ዓለም የደረሰበትን ደረጃ ለመድረስ ነው ሁሉም ሠዓሊ የሚሠራው። ያ ነገር ጥሩ ዕድል ነው። የሥዕል ጠቀሜታን ለማኅበረሰቡ ለማሳየት። የሥዕል ደረጃን ለማስረዳት፤ የእነርሱ ጥሩ ደረጃ መድረስ ቤቷን ሳይሆን ነገ የሚደርሱበት የተሻለ ቦታ አለ በማለት ይሠራሉ።»

ፓሌት የሠዓሊያን ክበብ ባለፉት ከአራት አስርተ ዓመታት በላይ አሰልጥኖ በዓለም እና ሀገር አቀፍ ደረጃ አንቱታን እንዲያገኙ ያደረጋቸው ሠዓሊያን በርካታ መሆናቸውን ሠዓሊ ኃይሉ ክፍሌ ይገልፃል።  በተጨማሪም የባህል ሚኒስቴር አሰልጣኝ የነበሩት አቶ አዳፍሬ ብዙነህን ጨምሮ ሠዓሊ ሥዩም አያሌው የላቀ ድርሻም እንደነበራቸው ይናገራሉ። «አሁን ከማስታውሳቸው ብርሃኑ አሻግሬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ጥበብ ትምህርት ዳይሬክተር የነበረ፣ አሁን ቪየና ኦስትሪያ ሦስተኛ ዲግሪውን የሚሠራ፤ አክሊሉ ተመስገን፤ በጣም አንጋፋ ነው። ጥበብ ትምህርት ቤት ዳይሬክተርየነበረአሁን በኦስትሪያ ቬና 3 ድግሪውን የሚሰራ አክሊሉ ተመስገን በጣም አንጋፋ ነው፡፡ አለባቸው ተካ፣ ተስፋ ሰለሞን፤ ያሬድ ኦሪቬሪ፤ እንግዳየ፤ ለዐይኔ ጥላሁን፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራኖች ናቸው። በርካታ ሠዓሊያንን ያፈራ ክበብ ነው ፓሌት።»

«በፓሌት ቡርሽ፣ ሸራና ቀለም በየዕለቱ ተወዳጅተው አዲስ ሃሰብ፤ አዲስ ማንነትን ይፈጥራሉ።» ፓሌት የሥዕል ስቱዲዮ ደሴምስል፦ Essays Gelaw/DW

ጠንካራ ጓደኝነት በፓሌት

በፓሌት ዓመታት ያልገደቡት የሙያ ሽግግር አለ የሚለው ወጣት ክብሩ ይስፋ ካሣ ወጣቶቹ በፓሌት የሚፈጥሩት ጓደኝነት ዘመን የተሻገረ ነው ይላል። «የሙያ ሽግግሩ በፓሌት የሚመጣ ለጥበብ ቀና ልብ ያለው ለሥዕል ጉጉት ያለው፤ ለሰዎች ለማስረዳት ፍቅር ያለው፤ ሳይሰለች እንደ ቤተሰብ፤ እንደ ጓደኛ በማስረዳት ላይ የተመሰረተ ነው። ከኮምቦልቻ፤ ከሐይቅ ይመጣሉ መጥተው እዚህም ጓደኝነት ይመሰርታሉ። ያ ጓደኝነት ያድጋል።»

በፓሌት ቡርሽ፣ ሸራና ቀለም በየዕለቱ ተወዳጅተው አዲስ ሃሰብ፤ አዲስ ማንነትን ይፈጥራሉ። ይህ ለባለፉት አራት አስርት ዓመታት የቀጠለው የጥበብ ፍኖት ዛሬም በርካታ ወጣቶች ለሥኬታቸው እየተጉበት ነው።  

 ኢሳያስ ገላው

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW