ህወሓትን 'ሕገወጥ እና ኃላቀር' ያለዉ አዲሱ 'ስምረት' ፓርቲ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 1 2017
ህወሓትን 'ሕገወጥ እና ኃላቀር' ያለዉ አዲሱ 'ስምረት' ፓርቲ
በቅርቡ የተመሰረተው በእነ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው 'ስምረት' ፓርቲ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በትግራይ ባለው 'ሕገወጥ ቡድን' ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠየቀ። ይህ ቡድን ከኤርትራ ጋር በመተባበር፥ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈል ዝግጅቱ ጨርሶ ይገኛል ሲልም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ፓርቲ ከሷል።
በሌላ በኩል አፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ በትግራይ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፕሪቶርያ ውል ያፈራረሙ አካላት በህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሰት መካከል ያለውን አደገኛ ሁኔታ ለመፍታት ይስሩ ብለዋል።የግንቦት 20 አከባበር፣ የዴሞክራስያዊ ስምረት ትግራይ ምሥረታ እና የኢሳያስ አፈወርቂ ንግግር
በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራውን ህወሓትን 'ሕገወጥ እና ኃላ ቀር ቡድን' በማለት የጠራው በቅርቡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቅድመ እውቅና ምዝገባ ፍቃድ የተሰጠው በእነ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትላንት ባወጣው መግለጫ በዚሁ ቡድን ምክንያት የትግራይ ህዝብ ወደከፋ ሁኔታ እያመራ ነው ብሏል። ህወሓት ሕገመንግስት በመጣስ ከኤርትራ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈል ዝግጅቱ አገባዷል ያለው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት፥ የዚህ አካል የሆነ ደግሞ በዓፋር ተደጋጋሚ ትንኮሳ እያደረገ ነው ሲል ከሷል። ጦርነት ለማወጅ ጫፍ ላይ ያለ ቡድን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ከመጠን በላይ ሊያስታምመው አይገባም ሲሉም በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው አዲሱ ፓርቲ ጥሪ አቅርቧል። ፓርቲው ለትግራይ ሐይሎች ባቀረበው ጥሪም ከኃላ ቀር ቡድኑ ራሳችሁን አርቁ፣ ከህዝብ ጎን ተሰለፉ ብሏል።
በህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለው ልዩነት በሰፋበት እንዲሁም የጦርነት ስጋት ባጠላበት በአሁኑ ወቅት ኃላቀር ቡድን ባለው ህወሓት ምክንያት የትግራይ ህዝብ ወደ ዳግም ጦርነት እንዳይገባ እና መሰረታዊ አገልገሎቶች እንዳይስተጓጎሉ እንደሚሰጋ ገልፆ፥ የኢትዮጵያ መንግስት ሐላፊነቱ ይወጣ ሲል 'ስምረት' አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌላው በዚህ ጉዳይ ዙርያ መግለጫ ያወጣው በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፥ የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ህዝብ ችግሮች ለማቃለል እንዲሁም የፕሪቶርያ ውል ይዘቶች ለመፈፀም ከመስራት ይልቅ የጦርነት ማስፈራርያ ላይ ተጠምዷል ሲል ከሷል። የተፈጠረው አስጊ ሁኔታ ለመቅረፍ ደግሞ አፍሪካ ሕብረት ጨምሮ ሌሎች የሰላም ውሉ አፈራራሚዎች ሐላፊነታቸውን ይወጡ ብሏል። ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ መሥራች ጉባኤውን በቅርቡ መቐሌ ላይ እንደሚያደርግ አስታወቀ
የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ሃይሉ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ ፓርላማ ፊት ቀርበው ጦርነት ከተጀመረ ከበፊቱ ጦርነት የከፋ ይሆናል ማለታቸው ስጋት የሚፈጥር ነው። ያለፈው ጦርነት ያስከተለው ጥፋት ይታወቃል ፥ ሲሉ ለዶቼቬለ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሌላው አስተያየት የሰጡን ፖለቲከኛ አቶ ደጋፊ ጎደፋይ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት የተያያዙት አካሄድ አደገኛ ነው ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ የተናገሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በተሳሳተ አረዳድ እና ድምዳሜ ምክንያት ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጀነራል ታደሰ፥ ያሉ ልዩነቶች እና ያልተፈፀሙ የፕሪቶርያ ስምምነት ይዘቶች በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ፍላጎት በትግራይ በኩል አለ ያሉ ሲሆን፥ በትግራይ በኩል የሚጀመር ትንኮሳ ይሁን ጦርነት ግን አይኖርም ሲሉም ተደምጠዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ