1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ህወሓት ፈረሰ ማለት የፕሪቶርያው ውል ፈረሰ ማለት ነው" ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 7 2016

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ቢነፈግም ህወሓት 14ተኛ የፓርቲው ጉባኤ በመቐለ ማድረግ ጀመረ። በጉባኤው በሺዎች የሚቆጠሩ የፓርቲው አባላት የታደሙ ሲሆን፥ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ጨምሮ ሌሎች የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ራሳቸው ከጉባኤው አግለዋል።

Generalversammlung der TPLF wird von Nationaler Wahlbehörde Äthiopiens (NEBE) nicht anerkannt
ምስል Million Haileselassie/DW

ሕወሓት በከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ሆኖ 14ኛውን ድርጅታዊ ጉባዔ ጀምሯል

This browser does not support the audio element.

"ህወሓት ፈረሰ ማለት የፕሪቶርያው ውል ፈረሰ ማለት ነው" የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

 

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ቢነፈግም ህወሓት 14ተኛ የፓርቲው ጉባኤ በመቐለ ማድረግ ጀመረ። በጉባኤው በሺዎች የሚቆጠሩ የፓርቲው አባላት የታደሙ ሲሆን፥ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ጨምሮ ሌሎች የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ራሳቸው ከጉባኤው አግለዋል። በጉባኤው መክፈቻ የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ህወሓት ፈረሰ ማለት የፕሪቶርያው ውል ፈረሰ ማለት ነው ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና የህወሃት ውዝግብ

 

ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መሪዎች፣ ጥቂት ከማይባሉ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ እና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ተቃውሞ እና ሌሎች ተቃውሞ የገጠመው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ከሰዓት ጀምሮ መካሄድ ጀምሯል። በጉባኤው ከአብዛኛው የደቡብ ትግራይ ዞን መምጣት ይገባቸው የነበሩ ተሳታፊዎች ያልተገኙ ሲሆን ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ከትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የተወከሉ የህወሓት አባላት ለጉባኤው ተሰይመዋል። በመክፈቻ ስነስርዓቱ የተናገሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በፓርቲው ውስጥ አለ ያሉት አንድ ቡድን ህወሓት ለማጥፋት እየሰራ መሆኑ ተከትሎ፥ ይህ ለማስቆም ጉባኤ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ጉባኤው መጠራቱ ተናግረዋል።

በጉባኤው መክፈቻ የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ህወሓት ፈረሰ ማለት የፕሪቶርያው ውል ፈረሰ ማለት ነው ብለዋል።ምስል Million Haileselassie/DW

 

ደብረፅዮን "በፓርቲያችን ውስጥ ተፈልፎሎ ያደገ፣ ፓርቲያችን ለመበተን እየሰራ ያለው የጥፋት ቡድን ያደረገው እና እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ፥ በየሰዓቱ እየፈጠረው ባለው ማደናገርያ ሁኔታችን ከመጥፎ ወደ ከፋ ደረጃ ተሸጋግሯል። ይህ ለማስቆም በዘላቂነት ለመቀየር ብቸኛ መፍትሔው 14ተኛ ጉባኤ ማካሄድ እና ማካሄድ ብቻ ነው" ብለዋል።

ሕወሃት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ ተቃወመ

የህወሓቱ ሊቀመንበር ጨምረውም ህወሓት ፈረሰ ማለት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ፈረሰ ማለት ነው በማለት ተናግረዋል። ደብረፅዮን "በዚህ ግዜ ህወሓት ከፈረሰ የፕሪቶርያው ስምምነት አይኖርም ብቻ ሳይሆን ከነአካቴው ታሪክ ሆኖ ይረሳል ማለት ነው። ስምምነቱ ከፈረሰ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ለበይ አሳልፎ መስጠት ማለት ነው። በአጠቃላይ እነዚህ ችግሮች እና አደጋዎች ለመፍታት ነው እንግዲህ ጉባኤአችን በዚህ ፈታኝ ወቅት ለማድረግ የፈለግነው ብቻ ሳይሆን የግድ ልናደርገው የተገደድነው" ብለዋል።

በውስጣዊ ክፍፍል ውስጥ ያለው ህወሓት የምርጫ ቦርድን መልስ እየተጠባበቀ ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፥ ህወሓት ለሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤም ሆነ በጉባኤው ላይ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች በሙሉ እውቅና እንደማይሰጥ ትላንት ማስታወቁ ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪ ጉባኤው ተቃውመው ከመድረኩ ከቀሩት መካከል ከሆኑት የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ በፅሑፍ ባስተላለፉት መልእክት፥ መደረግ የጀመረው ጉባኤ በጥድፍያ፣ የጋራ መግባባት ሳይደረስበት፣ አደራጀነው ባሉት ኔትዎርክ ይቃወሙናል ያሉት የተወሰነ መሪነት ለማስወገድ ብቻ የሚደረግ ጉባኤ ብለው የተቹት ሲሆን፥ ይህም የከፋ አደጋ የሚፈጥር እና ሊወገዝ የሚገባው ሲሉ ገልፀውታል። ሊቀመንበሩ ደብረፅዮን ግን ህወሓት አይፈረስም፥ ራሱን እየፈተሸ ይቀጥላል ሲሉ በጉባኤው መክፈቻ ተናግረዋል።

 

በተጀመረው የህወሓት ጉባኤ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW