1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በአማራ ክልል እየቀነሰ ነው ፤ ባለስልጣናት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 2 2016

ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ከ72 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በውጪ ሀገር የስራ እድል እንዲገኙ ማድረጉን የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ አስታውቋል። በአንፃሩ በህገወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ የነበሩ ከ1ሺህ 500 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን አመልክቷል።

Äthiopien | Amhara National Regional State Labour and Training Bureau
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በአማራ ክልል እየቀነሰ ነው መባሉ

ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ከ72 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በውጪ ሀገር የስራ እድል እንዲገኙ ማድረጉን የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ አስታውቋል።  በአንፃሩ በህገወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ የነበሩ ከ1ሺህ 500 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን አመልክቷል። በህገወጥ መንገድ ሰዎችን ሲያዘዋውሩ ከነበሩ ደላሎች መካከል 16ቱ ከ7 እስከ 25 ዓመት የእስራት ቅጣት እንደተላለፈባቸውም ዞኑ አስታውቋል፡፡

የዞን ሥራና ስልጠና መምሪዎች አስተያየት

መንግስት አስፈላጊውን ስልጠና ወስደው ዜጎች በህጋዊ መንገድ የውጪ ሀገር የስራ ስምሪት እንዲያገኙ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር እየቀነሰ መምጣቱን የአማራ ክልል አንዳንድ ዞኖች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ቀደም ሲል በስፋት ሰዎች ለስራ በሚል ከሚፈልሱባቸው አካባቢዎች አንዱ የደቡብ ወሎ ዞን ሲሆን አሁን ግን ህጋዊ መንገድን በመከተል የውጪ አገር የስራ ስምሪት መሰጠት በመጀመሩ ሥራ ፍለጋ በሚል በህገወጥ መንገድ ወደ ሌሎች አገሮች መሄድ በእጅጉ መቀነሱን የዞኑ ሥራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ ተናግረዋል፣ በዚህም 30ሺህ ያክል ሰዎች በህጋዊ መንገድ ወደ ተለያዩ አገሮች የስራ ስምሪት ማግኘታቸውንም ገልፀውልናል፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና መፍትሄው

ስራ ለማግኘት ወደ ሌሎች አገሮች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ መጓዝ ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን ዜጎችአ እየተረዱ መምጣታቸውን ኃላፊው ጠቁመው፣ ዜጎች መንግስት ስምምነት ባደረገባቸው የመካከለኛው ምስራቅ አገራት የስራ ስምሪት ያገኛሉ ብለዋል፡፡ ወደ አገራቸው ሲመለሱም ያለምንም እንግልት ማንነታቸው ተከብሮ ይመጣሉ ነው ያሉት፡፡   

ፎቶ ማህደር ፤ መንግስት አስፈላጊውን ስልጠና ወስደው ዜጎች በህጋዊ መንገድ የውጪ ሀገር የስራ ስምሪት እንዲያገኙ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር እየቀነሰ መምጣቱን የአማራ ክልል አንዳንድ ዞኖች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡ምስል Michele Spatari/AFP

አቶ ደምስ አክለውም 4 ሺህ ወጣቶች በቅርቡ የውጪ አገር የስራ ስምሪት ለማግኘት በዝግጅት ላይ ናቸው ነው ያሉት፡፡

በዚሁ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርም በርካታ ወጣቶች ወደ አረብ አገራት በህገወጥ መንገድ ለመውጣት መነሻቸውን ያደረጉበት አካባቢ ነው፣ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ሥራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም አልዬ እንደገለፁልን ግን በያዝነው ዓመት በህገወጥ መንገድ ወደ ውጪ አገር ለስራ ስምሪት የሚሄዱ ወጣቶች ቁጥር በጣም ቀንሷል፡፡

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተቆጣጣሪ ም/ቤት

የአማራ ክልል ስራና ስልጠና አስተያየት

በአማራ ክልል ሥራና ስልጣና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዳርጋቸው ጎፋ  የውጪ አገር ስምሪት ለመስጠት የሚያስችሉ ስልጠናዎችን በተለያዩ ማዕከላት ወስደው ከ73 ሺህ የሚሆኑ የአማራ ክልል ተወላጅ የሆኑ ወጣቶች በተለያዩ አገሮች በህጋዊ መንገድ  የስራ ስምሪት  አግኝተዋል ብለዋል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ዜጎች ወደ ውጪ አገር ለስራ ከመሄዳቸው በፊት የሙያ ስልጠና በክልሉ ባሉ  20 ማዕከላት ይሰጣል፣ ከዚያም እውቀትና ክህሎታቸው ተመዝኖ የ ስራ ስምሪት ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡ በ2016 ዓ ም 72 ሺህ 890 ዜጎች መስፈርቱን አሟልተው የስራ ስምሪት እንደተሰጣቸውና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ትርጉም ባለው ሁኔታ በአማራ ክልል እንደቀነሰም አብራርተዋል፡፡

ከስደት የሚመለሱ ዜጎችም ቅድሚያ የስልጠናና ሌሎች አስፈላጊ ሁኔታዎች ከተሟሉላቸው በኋላ በአገር ውስጥ የሚሰሩበት ሁኔታ እንደሚመቻች አቶ አንዳርጋቸው አመልክተዋል፡፡

የዓለም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚከላከል ቀን

በህገወጥ መንገድ ከአገር ሲወጡ በቁጥጥር ስርየዋሉ ሰዎች

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም በህገወጥ መንገድ ከሀገር ለመውጣት የሚሞክሩ ሰዎች እንዳሉ በአማራ ክልል የምዕራብ ጎንደር ዞን አመልክቷል፡፡ እየተገባደደ ባለው ዓመት 42 ጊዜ ደንበር አቋርጠው በሱዳን በኩል ለመውጣት የሞከሩ 1ሺህ 523 ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ የግጭት መከላከልና የእምነት ጉዳዮች ቡድን መሪ አቶ ዮናስ ጋዲሳ ለዶቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል፡፡

የሰዎች ለህገወጥ ዝውውር የሚፈልሱባቸው ክልሎች

የምዕራብ ጎንደር ዞን 400 ኪሎሜትር ያክል ከሱዳን ጋር የሚዋሰን ሲሆን ከ19 በላይ መውጫ በሮች እንዳሉ ቡድን መሪው ገልፀዋል፣ ሰዎቹ በዋናነት በህገወጥ መንገድ የሚወጡት በምዕራብ አርማጭሆ፣ በመተማና በቋራ ወረዳዎች በኩል እንደሆነም አመልክተዋል፣ አብዛኛዎቹ በህገወጥ መንገድ ለመውጣት የሚሞክሩት ዜጎች ከሶማሊያ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከደቡብና አልፎ አልፎ ከጋምቤላ ክልሎች የሚመጡ ዜጎች እንደሆኑም ገልጠዋል፡፡

በኢትዮ-ሱዳን ድንበር የሰዎች ዝውውር እና ችግሮቹ 

በደላሎች ላይ ተወሰደ እርምጃ

ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ ከነበሩ ደላሎች መካከል በ16ቱ ላይ ከ7 እስከ 25 ዓመት የእስራት ቅጣት እንደተወሰነባቸውም አቶ ዮናስ አመልክተዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ 

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW