1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ህግደፍ እና ህወሓትን ለማስታረቅ ጥረቱ ቀጥሏል

ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2011

የኤርትራው ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ፍትሕ (ህግደፍ) እና የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) «ለማስታረቅ» ያለመ የምሁራን እና የሀገር ሽማግሌዎች የምክክር መድረክ ትላንት በመቐለ ከተማ ተካሄዷል፡፡ የውይይቱ አዘጋጆች ፓርቲዎቹን ለማቀራረብ የሚደረገው እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል በጎ ምላሽ ማግኘቱን ገልፀዋል፡፡ 

Äthiopien Partei TPLF (Tigray) und EPLF (Eritrea)
ምስል DW/M. Hailessilase

ህግደፍ እና ህወሓትን ለማስታረቅ ጥረቱ ቀጥሏል

This browser does not support the audio element.

“ሰለብሪቲ ኤቨንትስ” በተባለ የግል ድርጅት አስተባባሪነት በተካሄደው የውይይት መድረክ ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የተውጣጡ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል። ህወሓት እና ህግደፍ በትጥቅ ትግል ወቅት እና ከዚያ በኋላ የነበራቸው ግንኙነት የሚዳስሱ ፅሑፎች በሁለቱ ሀገራት ምሁራን የቀረቡ ሲሆን ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተውባቸዋል። 

የ“ሰለብሪቲ ኤቨንትስ” ድርጅት ስራ አስከያጅ አቶ ሃፍቶም ገብረሊባኖስ ለዶይቸ ቬለ (DW) እንደገለፁት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው አለመግባባት መቋጫ ሊያገኝ ይገባል። አቶ ሃፍቶም አክለውም "ሁለቱን ፓርቲዎች ለማቀራረብ የምናደርገው እንቅስቃሴ በህወሓት እና የኤርትራው ህግደፍ በኩል በጎ ምላሽ አግኝቷል" ብለዋል። 

በሰላም መድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ፅሑፍ ካቀረቡት አንዱ የሆኑት ኤርትራዊው ምሁር አቶ ተመስገን አለም "ሁለቱ ፓርቲዎች በታሪክ የተሳሰሩ መሆናቸውን እና ለረጅም ጊዜ የቆየ ጸባቸው ብዙ ዋጋ ማስከፈሉን" ጠቅሰዋል። ህወሓት እና ህግደፍ ለህዝቦች ሲሉ በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። 

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች በተለይ ለሁለቱ ፓርቲዎች መቀራረብ ጫና መፍጠር እንደሚገባውም በመቐለው የውይይት መድረክ ተጠቁሟል። አዘጋጁ ሰለብሪቲ ኤቨንትስ በቀጣይነት የህወሓት እና ህግደፍ የቀድሞ ታጋዮች፣ የጦር ጉዳተኞች፣ የቀድሞ አመራሮች እና ሌሎች ተሳታፊዎች የሚገኙበት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እና አስመራ ለማድረግ አቅዷል። 

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW