ህጻናትን ከፖሊዮ የመታደግ ዘመቻ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 3 2018
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ24 ሚሊየን በላይ ሕጻናትን ለመከተብ ዕቅድ የተያዘበትን ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ዛሬ በይፋ ጀምራለች ፡፡ ሀዋሳ ላይ የክትባት ዘመቻውን ያስጀመሩት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ቤተሰቦችና ማህበረሰቡ ህፃናትን የማስከተብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አድርገዋል ።
ህጻናትን ከፖሊዮ የመታደግ ዘመቻ
ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ የማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ዛሬ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል። በማስጀመሪያው መረሃ ግብሩ ላይ እንደተገለጸው ዘመቻው ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት ይከናወናል ፡፡ በዘመቻው ከ24 ሚሊዮን በላይ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል ፡፡ የክትባት ዘመቻውን ያስጀመሩት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ማህበረሰቡ ህፃናትን የማስከተብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አድርገዋል ፡፡
የድጋፍ መቀነስ
ዓለምአቀፍ ነባራዊ ሁኔታው እንደሚያሳየው በጤናው ዘርፍ የሚደረገው ድጋፍ የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱን የጠቀሱት ዶ/ር መቅደስ " እንደ ሀገር ራሳችንንን ለመቻል መጣር አለብን ፡፡ ከዘመቻ ሥራዎች መውጣት ይጠበቅብናል " ብለዋል ፡፡
አሁን ላይበሀገራችን ፖሊዮን ጨምሮ ከ15 በላይ ክትባቶችን በመደበኛነት በመከተብ የማህበረሰቡ የጤና ስጋት የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር መቅደስ ለአራተኛ ዙር በሚሰጠው የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻም አንድም ህፃን ሳይከተብ እንዳይቀር ሁሉም በቁርጠኝነት እንዲሰራ አሳስበዋል።
ቅንጅታዊ ሥራዎች
ኢትዮጵያ እንደአውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2009 ዓም ከዋይልድ ፖሊዮ ነጻ መሆኗ ይታወቃል ፡፡ ይሁንእንጂ ሌላኛው የፖሊዮ አይነት መነሻውን ከድንበር አካባቢ በማድረግ መታየቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ ጠቅሰዋል ፡፡
አሁን ላይ የቅኝት መረጃዎችን በማጠናከር የተቀናጀ የአደጋ ስጋት ተግባቦት እየተከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ በአሁኑ ዘመቻ ከ24 ሚሊዮን በላይ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ ከክልል የጤና ተቋማት ጋር በቅንጅት ተግባራዊ የማድረግ ሥራ ዛሬ መጀመሩን አመልክተዋል ፡፡
የወላጆች አስተያየት
ዛሬ ይፋ የተደረገው የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻን ተከትሎ ትምህር ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የክትባት ሥራው እየተከናወነ ይገኛል ፡፡ ዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የጠቀየቃቸው በሀዋሳ ከተማ ሚሊኒየም ጤና ጣቢያ ልጆቻቸውን ለማስከተብ የተገኙት ወ/ሮ የኔነሽ አሰፋ እና ወ/ሮ ዘነበች ገብሬ ዘመቻው በተደረገው ቅስቀሳ መስማታቸውን ተናግረዋል ፡፡
ልጆቻቸው ክትባቱን መውሰድ እንዳለባቸው የጤና ባለሙያዎች እንደገለጹላቸው የጠቀሱት የኔነሽ እና ዘነበች " ክትባቱ ከጤና ጣቢያ በተጨማሪ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ቤት ለቤት እየተሰጠ ይገኛል ፡፡ በክትባቱ ልጆቻቸውን ከፖሊዮ በሽታ ለመታደግ ያስችልልናል የሚል እምነት አለን " ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ