1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለመንግስት የመገናኛ ብዙኃን ብቻ ክፍት የሆነ የምክር ቤት ጉባኤ

ረቡዕ፣ ሰኔ 26 2016

አንድ የምክር ቤት አባል ከበጀቱ ጋር በተያያዘ "የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለምን አይካሄድም" የሚል ጥያቄ መቅረቡን ጠቅሰው ከተለመደው ውጭ የግል መገናኛ ብዙኃን እንዳይገቡ የሚያደርግ ጉዳይ ነበር ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።

Äthiopien FDRE-House
ምስል Ethiopian Press Agency

የምክርቤቱ ውሎ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ያደረገዉን 35ኛ መደበኛ ጉባኤው የግል እና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ገብተዉ እንዳይከታተሉት አግዷል።ምክር ቤቱ በዛሬ ጉባኤዉ የፌዴራል መንግስት የ2017 አመት ረቂቅ በጀት ላይ በዝርዝር ለመወያየት፣  የኢሚግሬሽን አዋጅን ለማሻሻል የወጣ ረቂቅ አዋጅን ለማጽደቅ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመወያየት  አጀንዳ መያዙ ተነግሮ ነበር።ከመንግስት መገናኛ ዘዴዎች ጋዜጠኞች ዉጪ የሌሎች መገናኛ ዘዴዎች ጉባኤዉን በአካል እንዳይከታተሉ ምክር ቤቱ ያገደበትን ምክንያት አላስታወቀም።አንድ የምክር ቤት አባል ግን ከበጀቱ ጋር በተያያዘ "የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለምን አይካሄድም" የሚል ጥያቄ መቅረቡን ጠቅሰው ከተለመደው ውጭ የግል መገናኛ ብዙኃን እንዳይገቡ የሚያደርግ ጉዳይ ነበር ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።

ለውይይት የተያዙት አጀንዳዎች ምን ምን ነበሩ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ዛሬ ያካሄደው ስብሰባው የፌዴራል መንግስት የ2017 በጀት አመት ረቂቅበጀት ላይ በዝርዝር ለመወያየት፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንደገና ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን  እንዲሁም የኢሚግሬሽን አዋጅን ለማሻሻል የወጣ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን ዘገባ እና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን ለማጽደቅ እንደሚወያይ ትናንት በማሕበራዊ መገናኛ ዐውታር አስታውቆ ነበር። ምክር ቤቱ እንደ ሌላው ጊዜ ለቋሚ የምክር ቤቱ የግል እና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ዘጋቢዎች መልእክቱን በኢሜይል አልላከም። 
ዶቼ ቬለን ጨምሮ ሌሎች የውጭ መገናኛ ብዙኃን ቋሚ የምክር ቤቱ ዘጋቢዎች በጥዋቱ ለዘገባ ቢሄዱም "ለዛሬ አልተፈቀደም" የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸው ተመልሰዋል።

ምክር ቤቱ ከዚህ በፊት ያደርግ እንደነበረው ጉባኤውን በቀጥታ በማህበራዊ መገናኛ ዐውታሮች የማሰራጨት ተግባሩንም በዛሬው ጉባኤ አላደረገም።

የጉባኤውን መጠናቀቅ ተከትሎ ምክር ቤቱ ባወጣው ዘገባ በጀቱ "ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ እና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ስለማረጋገጡ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ" ማሳሰቡን ተገልጿል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤትምስል DW/Y. Gebreegiziabher


በውይይቱ የወጪ ንግድን ከማሳደግ፣ የእዳ ጫናን ከመቀነስ፣ የፕሮጀክቶች አስተዳደርን ከማሻሻል፣ የዋጋ ንረትን ከማረጋጋት፣ የሃብት ብክነትን ከመቆጣጠርና ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ፣ በጀትን በእውቀትና በፋይናንስ አሰራር ከመምራት አንፃር የገንዘብ ሚኒስቴር ምን ያህል ዝግጁ ነው?  የሚሉ ጥያቄዎች በምክር ቤት አባላት ተነስተው እንደነበርና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ "በጀቱ ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞችን ታሳቢ ስለማድረጉና የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል ስለመታቀዱ" እናንዲሁም "አጠቃላይ የደመወዝ ማስተካከያ የሚደረገው ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ መሆኑን እና የኑሮ ውድነቱን ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግ" መናገራቸውን ገልጿል።

ውይይቱን የተከታተሉት አቶ አብርሃም በርታ የተባሉ አንድ የምክር ቤቱ አባል መገናኛ ብዙኃንን ሊያስከለክል የሚችል ምንም አዲስ ነገር የለም ብለዋል። 

ሌላው ምክር ቤቱ ዛሬ ተወያይቶ ያፀደቀው ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ ሥልጣንን ለኢሚግሬሽን [አገልግሎት] የበላይ ኃላፊ የሚሰጥ ድንጋጌ የያዘውና ከሳምንት በፊት የቀረበው ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ነው። የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት "ዜግነት የማጣራት ሥራውን በልምድ የሚያከናውን፣ ውሳኔው ዜግነትን በሚያጣራው ግለሰብ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ እና ወጥ የሆነ አሠራር የማይከተል" ነው ሲል በቅርቡ አመታዊ የፋይናንስ እና የክዋኔ ኦዲት ዘገባውን ለምክር ቤቱ ያቀረበው የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስተያየት የሰጠበት የተቋሙ ማሻሻያ አዋጅ መጽደቁን ሌላ የምክር ቤት አባል ተናግረዋል።

በሌላ በኩል መደበኛ ጉባኤውን ማድረግ ከጀመረ ሁለት ቀናት የሆኑት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በልዩ ልዩ ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ቢሆንም የግል እና የውጭ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ገብተው እንዲዘግቡ እድል አልተሰጠም። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መገናኛ ብዙኃንን ለዘገባ እንዳይገቡ ሲከለክል ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ሰሎሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW