ለሰባተኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ግንቦት 24 ድምጽ ይሰጣል
ማክሰኞ፣ ኅዳር 30 2018
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የጊዜ ሠሌዳ ለሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ድምጽ እንደሚሰጥ አስታውቋል። ቦርዱ ዛሬ ማክሰኞ ይፋ ባደረገው የምርጫ ሠሌዳ መሠረት ከጥር 01 እስከ የካቲት 01 ቀን 2018 ባሉት 30 ቀናት የዕጩዎች ምዝገባ ይከናወናል። የመራጮች ምዝገባ የሚካሔደው ከየካቲት 7 ቀን እስከ መጋቢት 7 ባለው አንድ ወር ውስጥ ነው።
የምረጡኝ ቅስቀሳ ወይም የምርጫ ዘመቻ የሚካሔደው ከጥር 01 ቀን እስከ ግንቦት 19 ቀን 2018 ይሆናል። ከግንቦት 20 እስከ ድምጽ መስጫ ቀን ዋዜማ ማለትም ግንቦት 23 ድረስ “የጥሞና ጊዜ” ሲሆን ቅስቀሳ ማድረግ የማይቻልባቸው ቀናት ናቸው።
ድምጽ በሚሰጥበት ሰኞ ግንቦት 24 እና በማግሥቱ ግንቦት 25 ቀን የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያዎች ይፋ ይደረጋል። የመጨረሻው ይፋዊ የምርጫ ውጤት በምርጫ ቦርድ የሚገለጸው ሰኔ 04 ቀን 2018 ነው።
“በተለያየ ምክንያት [ምርጫ] ‘ይደረጋል’ ‘አይደረግም’ የሚል ነገር” መኖሩን እንደሚያውቁ የገለጹት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ መሥሪያ ቤታቸው “ያለ ማቋረጥ፤ ያለ መታከት ምርጫው እንደሚደረግ” እየገለጸ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ቦርዱ “በተግባርም እያሳየ ያለው ይኸንን ነው” ያሉት ሜላተወርቅ “ፖለቲካ ፓርቲዎችም በሚኖረን ምክክር ላይ ያላቸው ጥያቄ ‘አስቻይ ሁኔታ አለ’ ‘የለም’ እንጂ ‘ምርጫ አይደረግም’ የሚል ጥቅል ነገር አላቸው” ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች እና በትግራይ ክልል የበረታው ፖለቲካዊ ውጥረት በተያዘው ዓመት ይካሔዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ ላይ ክፉኛ አጥልተዋል።
ድምጽ እስከሚሰጥበት ዕለት ድረስ ከክልል መንግሥታት፣ መከላከያ ሠራዊት እና ፌድራል ፖሊስን ከመሳሰሰሉ ተቋማት መረጃ በመቀበል ምርጫ ለማካሔድ የሚያስችል ሁኔታ መኖሩን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደሚገመግም ሰብሳቢዋ ሜላተወርቅ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአቶ ጌታቸው ረዳ ለሚመራው ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ “የክልላዊ ፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባ እና የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ” ዛሬ ኅዳር 29 ቀን 2018 ሰጥቷል። ከተሰረዘው ህወሓት ጋር በአንጻሩ ቦርዱ “ምንም ግንኙነት” እንደሌለው ሜላተወርቅ አስረድተዋል።
የኦሮሞ ፌድራላዊ ኮንግረስ በግንቦቱ ምርጫ በአዲስ አበባ እና “በአንዳንድ ጥቂት አካባቢዎች ብቻ” እንደሚሳተፍ ባለፈው ሣምንት አስታውቋል። ፓርቲው “በኦሮሚያ እና ጦርነት ውስጥ ባሉ ሌሎች ክልሎች አፋጣኝ እና ሊረጋገጥ የሚችል የግጭት ማቆም ሥምምነት ተግባራዊ እንዲደረግ” ጥሪ አቅርቦ ነበር።
ሜላተወርቅ ለምርጫ አስቻይ ሁኔታዎች ስለመኖራቸው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሚደረገው ግምገማ ኦፌኮ እንደሚሳተፍ አስታውሰው ውጤቱን “እያዩ ሲሔዱ የተሻለ በስፋት የመካፈል ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችሉ” ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከግጭት እና የጸጥታ መጓደል ባሻገር የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ለምርጫው እንቅፋት እንደሚሆን በተደጋጋሚ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በየዕለቱ እየተቀበለ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ሜላተወርቅ “የቢሮ መዘጋት ችግር አለ። የአባላቶች እስር አለ” ሲሉ ተደምጠዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ለሚያስሩ አካላት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ በመጻፍ ጥያቄ እንደሚያቀርብ የገለጹት ሰብሳቢዋ “መልስ የሚሰጥ መዋቅር አለ፤ መልስ የማይሰጥ መዋቅር አለ” ሲሉ ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች የትኛውም ተቋም ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት” ያሉት ሜላተወርቅ “አንድ ፓርቲ ‘አባሌ ታሰረብኝ ብሎ ሲጠይቅ፤ ‘ይኸ አባል ለምን ታሠረ?’ ‘ታሥሮስ ፍርድ ቤት ቀርቧል ወይ?’ የሚለውን የክትትል ሥራ” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ማሻሻያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 25 ቀን 2018 በሙሉ ድምጽ ሲጸድቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ የሚያስገድደው ድንጋጌ በሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ እንዲታገድ ተደርጓል።
እሸቴ በቀለ
አርታዒ ታምራት ዲንሳ