1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

ኒው ሚሊኒየም ውመን ኢምፓወርመንት

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ሰኔ 16 2015

ከከተማ ወደ ገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል በተሔደ ቁጥር ሴቶት የሚገጥማቸው ፈተና መጨመሩ አይቀሬ ነው። ስለሆነም ኒው ሚሊኒየም ውመን ኢምፓወርመንት የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በማስቆም ፣በጤና፣ በኢኮኖሚ እና ትምህርት ዘርፎች ላይ ይሳተፋል።

Logo New Millennium Women Empowerment

ኒው ሚሊኒየም ውመን ኢምፓወርመንት

This browser does not support the audio element.

ሀገር በቀሉ ድርጅት ከዋና ከተማ አዲስ አበባ በተጨማሪ ፣ በጋምቤላ ፣ በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ይንቀሳቀሳል። «ድርጅቱ ከተመሰረተ 16 ዓመት ሆኖቷል» ትላለች ከቅርብ ጊዜ አንስቶ የፆታ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆና የምታገለግለው እስከዳር ታጠቅ። ኒው ሚሊኒየም ከሚሳተፍባቸው ፕሮጀክቶች አንዱ በተለያዩ ሀገራትም የሚከናወነው የ «She Leads» ወይም «እሷ ትምራው» የተሰኘው ፕሮጀክት ነው። « ፕሮጀክቱ ሰባት ሀገራት ላይ ይተገበራል። ኢትዮጵያ ከእነዚህ አንዷ ናት። ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን በቡድን ነው የምንሰራው።» የምትለው እስከዳር የፕሮከክቱ አላማ የሴቶችን ተፅዕኖ ማሳደግ እና ሴቶችን እስከ አመራር ደረጃ ማብቃት እንደሆነ ለዶይቸ ቬለ ገልፃለች። የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ከ 14 እስከ 24 እድሜ ያላቸው ሴቶች ናቸው። ፕሮጀክቱ አዲስ አበባ የሚገኙ ሁለት ክፍለ ከተሞች ላይ ከሚገኙ ስድስት ትምህርት ቤቶች ጋር ይሰራል።
መቅደስ ሳሚ እና ዳናዊት እንደግ የዚህ ፕሮጀክት አካል ናቸው።  በድርጅቱ በኩል ያገኙትን ስልጠና ፣ የልምድ ልውውጥ እና የግል ተነሳሽነት ተጠቅመው በዋናነት በማህበረሱ ዘንድ ያለውን በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመቀየር ይሰራሉ። « ይሔ አጋጣሚ የተፈጠረው «She Leads» ወደ ትምህርት ቤታችን የመጣ ጊዜ ነው። »
ትላለች የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነችው መቅደስ። ምንም እንኳን ከተማ ቢሆንም የምትኖረው ፆታዊ ጥቃት በየቦታው በመታዘቧ ይህን እንዴት መከላከል እንደምትችል ከሌሎች ጋር ትወያያለች። የ 18 ዓመቷ ወጣት ከሰዎች ጋር በቀላሉ መግባባት መቻሏ ለምትሰራው ስራ ጠቅሟታል ።

ዳናዊት ደግሞ የ12 ክፍል ተማሪ እና የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ናት። እሷም ወጣት ሴት ልጆችን እንዴት ማጠንከር እና ማበረታታት እንደሚገባ ትገልፅላቸዋለች። ትምህርቱን የምትለግሰው ለሴቶች ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ እድሜ ላይ ለሚገኙ ወንድ ተማሪዎችም ነው።  « እነሱን በማስተማር ነው ልንለውጠው የምንችለው። ለዛም ነው ለተቃራኒ ፆታ ትምህርት የምንሰጠው።»

ዳናዊት በሚኒ ሚዲያ ፤ በተለያዩ ክበባት ፤ በየክፍሉ እየተዘዋወረች ወይም በተለያዩ መድረኮች ላይ እየተገኘች ይህንን ትምህርት እንደምታስተላልፍ ገልፃልናለች። ካደገችበት ማህበረሰብ እና ጓደኞቿ ተለይታ የምታስበውን በድፍረት ለመናገር እንዴት እንደቻለችም ገልፃለልናለች።  « 9ኛ ክፍል እያለሁ ጎረምሶች በጣም ነበር የሚያስቸግሩኝ። መውጣት መግባት አልችልም ነበር። እና እንዴት ሴት ልጅ የፈለገችውን ነገር አታደርግም የሚል ሀሳብ አደረብኝ እና መማር ስላለባቸው ይህንን ትምህርት መጀመር ፈለኩ።»

የ «She Leads» ወይም «እሷ ትምራው» የተሰኘው ፕሮጀክት ሰባት ሀገራት ላይ ይተገበራል። ምስል NMWEO

ከአዲስ አበባ የመጣችው መቅደስ የሚሰጡት ስልጠናዎች ብቻ በቂ አይደሉም ትላለች። ወጣቷ በተለይ ከወላጆች እና የህግ አስከባሪዎች ብዙ ትጠብቃለች።  « የሚሰጠው ስልጠና በተግባር ቢደገፍ ለምሳሌ እኔ ከእናቴ ጋር ስለተፈጠሩ ነገሮች እናወራለን። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር እንዴት መግባባት እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው። እንዲሁም ደግሞ አንዲት ሴት የመደፈር ጉዳት ከደረሰባት የፖሊሶች ነገርን አደባብሶ ማለፉ ቢቀር። ህግጋቶቹ ቢሻሻሉ። ሴት ልጅ ተደፍራ ትንሽ ቅጣት ሊሰጥ አይገባም። እንደ ቀላል ነገር መታየት የለበትም»
በቅርቡ ሀዋሳ ከተማ ላይ የተጠለፈችው ወጣት ጉዳይ ብዙዎችን አነጋግሯል። ዳናዊትም ጉዳዩን በደንብ ስትከታተለው ነበር ትላለች። ለእሷ የጠለፋው ችግር በጣም ቅርብ ነው። 
« የምማርበት ትምህርት ቤት ጋር ብዙ ሴቶች እየተጠለፉ ነው። በተለይ ባህር ዳር ላይ ሴቶችን በባጃጅ እየጠለፉ ህይወታቸውን እያበለሹ ነው። » ስለሆነም የሚመለከተው አካል ይበልጥ እንዲሰራበት ትመክራለች።
በባህር ዳር ከተማ ከ9 ክፍል አንስቶ እስካሁን የማህበረሰቡን አስተሳሰብ በመቀየር እና አዳጊ ሴቶችን በማነቃቃት ስራ ላይ የተሳተፈችው ዳናዊት እስካሁን ወደ አዲስ አበባ ሄዳ ከሌሎች በፕሮጀክቱ ከሚሳተፉ ሴት ልጆች ጋር የመገናኘት እድል አላገኘችም። የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉት በስልክ ነው። ከሚያደርጉት የልምድ ልውውጥ በገጠር አካባቢ ብዙ መሠራት አለበት ትላለት ዳናዊት። ለዚህ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላል። 
የኒው ሚሊኒየም ውመን ኢምፓወርመንት የፆታ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆነችው እስከዳር እንደምትለው በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ላይ በነበራቸው ተሳትፎ  በተለይ ያለ እድሜ ጋብቻ ፣ ፆታዊ ጥቃት፣ የሴት ልጅ ግርዛት እና  የሥነ ልቦና ጉዳቶች በገጠራማው ክፍል አሁንም ድረስ ተግዳሮት እንደሆኑ ገልፃልናለች። « የራሳቸው ሴቶቹ አመለካከት የማህበረሰቡ ተፅዕኖ ስላለ እችላለሁ የሚል እምነት ያጣሉ። የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ የማህበረሰቡ ተፅዕኖ አለ። » ስለሆነም  ኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶች በጤና ፣ በሥነ ልቦና፣ በኢኮኖሚ እና በመሳሰሉት እንዲጎለብቱ አሁንም ብዙ መሰራት እንዳለበት ነው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶቻችን ከተሞክሯቸው ያጋሩን። 

ልደት አበበ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW