ለሶስት ቀናት የሚቆየው የብሄራዊ የውይይት ኮሚሽን አጀንዳ ማሰባሰቢያ ውይይት
ዓርብ፣ ግንቦት 22 2017
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የትግራይ ክልል በአገራዊ ምክክር ሂደት ተሳታፊ እንዲሆን ኮሚሽኑ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ባለድርሻ አካላት ጥሪ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ ዛሬ መልእክቱን ያስተላለፉት ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት አዲስ አበባ ውስጥ በሚደረገው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ተቋማት እና ማህበራት አጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
ኮሚሽናቸው የአገራዊ ምክክር ጉባኤ መዳረሻ ላይ መሆኑን ያስገነዘቡት ኮሚሽነሩ በተለይም በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ለሚገኙ ለታጣቂ ኃይሎች እና እስካሁን በምክክር ሂደቱ መሳተፍ ላልጀመሩ የፖለቲካ ድርጅቶችም የተሳትፎ ጥሪ አቅርበውላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት በፖለቲከኞች እና ሊዕቃን መካከል የሚስተዋሉ ልዩነቶች ጦር አማዘው ደም አፋሰው እስከዛሬም ድረስ የዘለቀ መሆኑን ያስረዳው የኢትዮጵያ አአገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ ዛሬም ድረስ ያልተቀረፈ ያለውን አዙሪት ለማስወገድ ችግሮችን በውይይት ለይቶ ማስቀመጥ ይሻል ብሏል፡፡
ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በተጀመረው የፌዴራል ተቋማት እና ማህበራት አጀንዳ የማሰባሰብየምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ ችግሮቹን ለመፍታት እስከመጨረሻው እንደምጥር አስታውቀዋል፡፡ “ኮሚሽኑ ይህንን የኢትዮጵያውያንን ህልም ቋጠሮ ለመፍታት ህዝቡን ቀኝ እጁ አድርጎ ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው” በማለትም የዛሬው የፌዴራል ባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ መድረክ 14ኛው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ከዚሁ ለምክክሩ አጀንዳ ከማሰባሰብ አኳያ የትግራይ ክልልን በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፍ ማድረግ እና ውጪ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎችን ማሰባሰብ የሚቀሩት አበይት ስራዎች መሆኑን ያስረዳው ኮሚሽኑ፤ መሳሪያ አንግበው ዱር የገቡ ታጣቂዎች በሂደቱ አለመሳተፋቸው በእጅጉ እንዳሳሰበውም በመግለጽ የትግራይ ክልልም በሂደቱ እንዲሳተፍ ጥሪ አሰምቷል፡፡ ኮሚሽነሩ አቶ መስፍን ዓርዓያ፤ “የትግራይ ክልል በሂደቱ ተካቶ በክልሉ የሚገኙ ውድ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ላይ ከሌሎች ወድሞቻቸው ጋር እንዲመክሩ ሄኔታዎችን እንዲያመቻቹ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌዴራል መንግስት እና በጉዳዩ ላይ አዎንታዊ ሚና ያላቸው ሁሉ ተገቢውን ጥረት እንዲያደርጉ” ሲሉ በመጠየቅ፤ ኮሚሽናቸው “መሳሪያ አንግበው ዱር የገቡ እህት ወንድሞቻችን በዚህ ሂደት አለመሳተፋቸው ኮሚሽናችንን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኖ አግኝቷል” ነው ያሉት፡፡
ኮሚሽነር መስፍን በተለይም የታጠቁ ወገኖችን በማስመልከት ባቀረቡት ጥሪ፤ “በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ወገኖች በተለይም የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት እና የፋኖ ኃይሎች እንዲሁም መንግስት ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት ብቸኛው መንገድ አገራዊ ምክክር መሆኑን በመረዳት የተቻለውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርጉ” ሲሉ
ጠይቀዋል፡፡ በዚህም በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ ወገኖች በብርቱ እንዲያስቡበትና መንግስትም ለምክክር ሂደቱ የሚቻለውን አስቻይ ሁኔታ ሁሉ እንዲፈጥር ተጠይቆ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በህግ በተሰጠው ሃላፊነት ልክ የሚቻለውን ጥረት ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋልም፡፡
በፍርድ ሂደት ላይ ያሉና በስደትም ላይ የሚገኙ ዜጎች በምክክር ሂደቱ ብሳተፉ የሚስገኙት አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነ እንገነዘባለን ያሉት ኮሚሽነር መስፍን፤ በሂደቱ ተሳታፊ ላልሆኑ ውስን ላሏቸው የፖለቲካ ድርጅቶችም የተሳተፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ “ሂደቱን አገባዶ ወደ ዋና ምክክር ጉባኤ ጫፍ ላይ እየደረሰ ያለው የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ምክክር ይበልጥ አካታችና አሳታፊ እንዲሆንና ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ እንዲያስገኝ በተለያዩ ምክንያቶች በሂደቱ ያልተሳተፋችሁ እንዲሁም ተሳትፎአችሁን ያቋረጣችሁ ከኮሚሽኑ አኳያ ለሚነሱት ምክንያቶች ለቀራርበን ለመመካከር ዝግጁ ነን” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የሶስት ዓመታት የስራ ጊዜውን በማጠናቀቁ በቅርቡ በኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ ዓመት የስራ ጊዜ የተጨመረለት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሁን በሚቀሩት የ10 ወራት ብቻ እድሜ የአገራዊ ምክክ ጉባኤ መዳረሻ ላይ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ኮሚሽኑ በዚህን ወቅት ትግራይ ክልል እና ውጪ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አጀንዳ ማሰባሰብ ብሎም የጉባኤው ተወካዮችን የማስመረጥ በቀጣይ ጢቂት ወራት ለማጠናቀቅ ማቀዱን ይገልጻል፡፡ ያንን ተከትሎም የአወያዮች መረጣና ስልጠና፣ የአጀንዳ ቀረጻ፣ የምክክር ሂደት ስርዓትና ድንጋጌዎች ይሰራሉም ተብሏል፡፡
ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የተጀመረው የሃማኖትና ሲቪክ ተቋማት፣ የመንግስት ተወካዮች፣ ሚዲያ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት እንዲሁም ማህበራት እና ታዋቂ ሰዎችን ያካተተው የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ በአጠቃላይ 879 ተወካዮች በኩል እንደ አገር ለገጠሙ ችግሮች መንስኤ ናቸው የተባሉ ጉዳዮች በምክክል ተለይተው እስከ የፊታችን እሁድ እንዲቀርቡ ይጠበቃልም ተብሏል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
ፀሀይ ጫኔ