1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«ለታሸለ ነገ ታስፋን የሰነቁት» የማርጎት ፍሪድሌንደር - ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ

ሐሙስ፣ ግንቦት 7 2017

«የምለዉ ሰዉ እንሁን።ይህ ነዉ ዋናዉ።የሰዉን ሃይማኖትና የቆዳ ቀለም ሳያዩ ሰዉ ስለሆነ ብቻ ማክበር። ሁሌም እንደምለዉ የክርስቲያን ደም የሚባል የለም፤ የሙስሊም የሚባል ደም የለም፤ የአይሁድ የሚባል ደም የለም፣ ያለዉ የሰዉ ልጅ ደም ብቻ ነው።ሁላችን አንድ ነን።ወደ ዓለምም በተመሳሳይ መንገድ ነዉ የመጣነዉ፤ሰዉን እናከብር።» ማርጎት ፍሪድሌንደር

ማርጎት ፍሪድሌንደር - ከናዚ ጭፍጨፋ «ሆሎኮስት» የተረፉት 
ማርጎት ፍሪድሌንደር - ከናዚ ጭፍጨፋ «ሆሎኮስት» የተረፉት ምስል፦ Bernd von Jutrczenka/dpa/picture alliance

«ለታሸለ ነገ ታስፋን የሰነቁት» የማርጎት ፍሪድሌንደር - ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ

This browser does not support the audio element.

«ለታሸለ ነገ ታስፋን የሰነቁት» ማርጎት ፍሪድሌንደር  

« ብዙ መናገር አልፈልግም። ብዙ ቃላቶችም አያስፈልጉኝም። እኔ የምለዉ ሰዉ እንሁን ነዉ። ይህ ነዉ ዋናዉ እና አስፈላጊዉ ነገር። የሰዎችን  ሃይማኖት ፤ የቆዳ ቀለማቸዉን ሳያዩ በሰዉነታቸዉ ብቻ ማክበር። ሁልጊዜ እንደምለዉ የክርስቲያን ደም የሚባል የለም፤  የሙስሊም የሚባል ደም የለም፣ የአይሁድ የሚባል ደም የለም፣ ያለዉ የሰዉ ልጅ ደም ብቻ ነው። ሁላችንም አንድ ነን። ወደዚህ ዓለምም የመጣነው በተመሳሳይ መንገድ ነው።  ሰዎች ነን እና፣ ሰዎችን እናከብር።»አይሁዶች በጅምላ የተጨፈጨፉበት መታሰቢያ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሔደ

«ለታሸለ ነገ ታስፋን የሰነቁት» ማርጎት ፍሪድሌንደር - ሥርዓተ ቀብራቸዉ ተፈፀመ ምስል፦ Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

ግንቦት 1፤ ቀን 2017 ዓ.ም በ103 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩት ጀርመናዊ አይሁዳዊት ማርጎት ፍሪድሌንደር ከተናገሩት የተወሰደ ነዉ። ማርጎት ፍሬድሌንደር በዚህ ንግግራቸዉ በጀርመናዉያን ልብ ተቀርፀዋል፤ በዓለም ዙርያም በዚህ ሰላም ጥሪያቸዉ እዉቅና እና አድናቆትን አግኝተዋል። ማርጎት ፍሪድሌንደር በ 103 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ባለፈዉ ሳምንት አርብ ነበር። በጀርመን ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት የተጠናቀቀበት 80ኛ ዓመት በታሰበ ማግስት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ሜይ 9 ቀን 2025 ዓ.ም መሆኑ ነዉ። ማርጎት ከናዚ ጀርመን የግፉ ጥቃት የተረፉ ፤ በዓይናቸዉ ያዩትንም ሲናገሩ የይቅርባይነት እና የፍቅር እጃቸዉን  ሲዘረጉ የቆዩ በጀርመን ከፍተኛ ክብር ያገኙ ሰዉ ነበሩ። ማርጎት ከዚህ ከናዚ ጀርመን ግፍ አምልጠዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1946 ዓ.ም ከባለቤታቸዉ ጋር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተሰደዋል። በዩናይትድ ስቴትስም ለበርካታ አስርተ ዓመታ ኖረዉ፤ ባለቤታቸዉ በሞት ሲለዩዋቸዉ፤ ወደ ትዉልድ አገራቸዉ ወደ ጀርመን በጎርጎረሳዉያኑ 2010 ዓ.ም ወደ ተወለዱበት ከተማ በርሊን ጠቅልለዉ ተመልሰዋል። ማርጎት ከተመለሱ በኋላ የሁለተኛዉን ዓለም ጦርነት ግፍና በደል ሲነግሩ ፤ ይህ ታሪክ አይደገም በማለት ሲያስተምሩ የይቅር ባይነትን ልብ አስፈላጊነት ሲያሳዩ ዘልቀዋል።መራሒተ መንግሥቷ አዉስሽቪትስን ጎበኙ

«ለታሸለ ነገ ታስፋን የሰነቁት» ማርጎት ፍሪድሌንደር - ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ ምስል፦ Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

የጀርመኑ ርዕሰ ብሔር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ፤ ለማርጎት ፍሪድሌንደር፤ እስከዛሬ ያልታየ የጀርመንን ከፍተኛ ኒሻን ዳግም ለመስጠት በተዘጋጁበት እለት የ 103 ዓመትዋ ማርጎት ፍሪድሌንደር ከዚህ ዓለም በድካም አሸልበዋል። ማርጎት ከቀናቶች በፊት በታዋቂ የቴሌቭዥን እና ራድዮ ጣብያዎች ቀርበዉ ቃለ-ምልልስ ሲሰጡ ላያቸዉ ጠንካራ ሙሉ ጤነኛ የሰማንያ ዓመት አዛዉን አቋም ነበራቸዉ አይነት ነበሩ። በዚህም የማርጎት በድንገት የማሸለባቸዉ ዜና በርካታ ጀርመናዉያንን አስደንግጧል፤ አሳዝኗልም።ዓለም አቀፍ የሆሎኮስት መታሰቢያ ምንድን ነው?

ማርጎት ፍሪድሌንደር - የቀብር ሥነ-ስርዓት ምስል፦ Christophe Gateau/dpa/picture alliance

በርሊን ላይ ነዋሪ የሆኑት የአስተዳደር እና የምጣኔ ሃብት ባለሞያዉ ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ በጀርመን ሃገር ሲኖሩ ወደ ሰላሣ ሰባት ዓመት ሆንዋቸዋል። በቅርቡ የመዲና በበርሊን አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለቀጣዩ አምስት ዓመታት የክብር ዳኛ እንዲሆኑ መርጧቸዉ በማገልገል ላይ ይገኛሉም።  ዶክተር ፀጋዬ ጀርመናዊ አይሁዳዊት ማርጎት ፍሪድሌንደር እንቀራረብ ሲሉ የይቅርታ እጃቸዉን የዘረጉ ታላቅ ሰዉ ሲሉ ይገልጿቸዋል።

ከናዚ ጭፍጨፋ «ሆሎኮስት» የተረፉት ማርጎት ፍሪድሌንደር 

ማርጎት ፍሪድሌንደር የ 21 ዓመት ወጣት ሳሉ በበርሊን ከርሰ ምድር ዋሻዎች ዉስጥ ለ 15 እና 16 ወራቶች  ተደብቀዉ ከናዚ ጥቃት አምልጠዉ ህይወታቸዉን አትርፈዋል። በጎርጎረሳዉያኑ በ1944 ዓ.ም ማርጎት በናዚ ጦር ተይዘዉ ጦሩ የጉልበት ብዝበዛ በሚያካሂድበት በዝያን ጊዜዉ ቼኮስሎቫክያ ዉስጥ በያዘዉ እና ትሪዝንሽታት በሚባል ማጎርያ ስፍራ ታስረዉ ሳለ፤ ቆየት ብለዉ ለትዳር የበቁበትን  ጀርመናዊ ባለቤታቸዉን የተዋወቁት። ሁለቱ ጀርመናዊ አይሁድ ጥንዶች ከናዚ ጭፍጨፋ ተርፈው ተጋብተዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1946 ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተሰደዉ በኒዮርክ ኑሯቸዉን ጀመሩ።  ማርጎት ፍሪድሌንደር "Try to Make Your Life" «ህይወትህን ለማነፅ ሞክር » የሚል ስለራሳቸዉ የህይወት ታሪክ ጽፈዋል። ከአስርተ ዓመታቶች በኋላ ማርጎት ይዘዉት የነበረዉን የአሜሪካ ዜግነትን መልሰዉ ጀርመናዊ ዜግነታቸዉን ዳግም ተቀብለዉ በርሊን መኖር ጀምረዋል።   

ከናዚ ጭፍጨፋ «ሆሎኮስት» የተረፉት ማርጎት ፍሪድሌንደርምስል፦ VOGUE Germany/dpa/picture-alliance

ማርጎት ፍሪድሌንደር ወደ ጀርመን ከተመለሱ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ቀጠሮዎችን በመያዝ የህይወት ታሪካቸዉን የጦርነት እና የብሔርተኝነትን አስከፊነትን ደጋግመዉ ተናግረዋል። ለምን ይህን እንደሚያደርጉ ሲጠየቁ ደግሞ እኔ ከናዚ ጭፍጨፋ ተርፊያለሁ፤ ለተገደሉት እና መናገር ላልቻሉት እኔ ልናገርላቸዉ ስለምፈልግ ነዉ፤ ይህ ደግሞ ለስድስት ሚሊዮን አይሁዳዉያን ብቻ ሳይሆን በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ለተገደሉ ሁሉ ድምፅ መሆን ስለምፈልግ ነዉ ብለዉ ተናግረዋል።  የጀርመን ፕሬዚደንት በሆሎኮስት መታሰቢያ ንግግር አሰሙ

የማርጎት ፍሪድሌንደር ይቅርባይነት 

ማርጎት ፍሪድሌንደር በቀብር ሥነ-ሰርርዓት ላይ የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተርሽታይን ማየር፤ የጀርመኑ ቻንስለር ፍርድሪሽ ሜርስ፤ የቀድሞዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል ምስል፦ Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

ማርጎት ፍሪድሌንደር ለወጣቱ ትዉልድ በተለያዩ ዝግጅቶች፤ በትምህርት ቤቶች፤ የጦርነትን አስከፊነት የብሔርተኝነትን አስከፊነት ብሎም የናዚን ጭፍጨፋ ታሪክን  ከተረኩ በኋላ በርካታ የእናመሰግናለን ደብዳቤዎች እንደሚደርሷቸዉ ይናገሩም ነበር። ወጣቶቹ በደብዳቤያቸዉ ማርጎት በኛ እንዲተማመኑ እንፈልጋለን ሲሉ ቃል እንደገቡላቸዉ ፤ ይህ የታሪክ ጠባሳ እንደማይደገም ቃል በመግባት በርካታ የጽሑፍ ማስታወሻ እንደሚደርሳቸዉ ማርጎት ደጋግመዉ ተናግረዋል።

ማርጎት ፍሪድሌንደር ከሁለት ዓመት በፊት የተከበሩ የበርሊን ነዋሪ ተብለዉ በብር የተቀረፀ ምስላቸዉ ተበርክቶላቸዉ ን መርቀዋል። ከጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በጀርመን አንደኛ ደረጃ የተባለ የክብር ኒሻን ተሸልመዋል። በዚህ ሥነ-ስርዓት ላይ ማርጎት የሚገርም ህይወት ሲሉ እንዲህ ተናግረዉ ነበር።

ማርጎት ፍሪድሌንደር ከጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተርሽታይን ጋርምስል፦ Federico Gambarini/dpa/picture alliance

«እዚህ ተወለድኩ፣ እዚህ እሞታለሁ፣ እዚሁ ደግሞ ቀብሪ ይፈፀማል። ምን አይነት የሚገርም ህይወት ነዉ።»

የበርሊን ነዋሪ የነበሩት ማርጎት ፍሪድሌንደር ማረፍን ተከትሎ የበርሊን መዘጋጃ ቤት ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ተዉለብልቧልምስል፦ Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

ከናዚ ጭፍጨፋ «ሆሎኮስት» የተረፉት እና ባለፈዉ ሳምንት በ103 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት  በጀርመን ታላቅዋ ሰዉ ማርጎት ፍሪድሌንደር ዛሬ ከቀትር በፊት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተርሽታይን ማየር፤ አዲስ የተመረጡት የጀርመኑ ቻንስለር ፍርድሪሽ ሜርስ፤ ብሎም የቀድሞዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት ከበርሊን በዲና ወጣ ብሎ በሚገኘዉ በበርሊን ቫንዜ፤ የአይሁድ መቃብር ስፍራ ዛሬ ሃሙስ ግንቦት 7 ቀን 2027 ዓ.ም ወይም በፈረንጆቹ  ሜይ 2025 ሥርዓተ ቀብራቸዉ ተፈፅሟል።

ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን!

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW