ለአሳሳቢው የጥላቻ ንግግር በኢትዮጵያ መፍትሔ ተጠየቀ
ማክሰኞ፣ መስከረም 20 2018
አሳሳቢው የጥላቻ ንግግር በኢትዮጵያ
እልኸኝነት ፣ ብሽሽቅና ከመጥፎ አዕምሮ የሚመነጭ የጥላቻ ንግግር በኢትዮጵያ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አውድ ላይ መስማት እየተለመደ መጥቷል ፡፡ "ማህበራዊ ሚዲያና የጥላቻ ንግግር በኢትዮጵያ በዲጂታል ሚዲያ ዘመን የሰላም አማራጮችን ፍለጋ" በሚል ርዕስ በሀዋሳ የተካሄደው የፓናል ውይይትም አትኩሮቱን በዚሁ አሳሳቢ ጉዳይ ላይ ያደረገ ነው ፡፡ በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የሚሠራጩ የጥላቻ ንግግሮች የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት እያወሳሰቡት መምጣታቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች አመልክተዋል ፡፡
የጥላቻ ንግግር ጦሶች
በፓናል ውይይቱ ላይ ምልከታቸውን ካቀረቡት መካከል አንዱ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና የሥነ ተግባቦት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መልሰው ደጀኔ ናቸው ፡፡ የጥላቻ ንግግርን አቅልለን ልናየው አይገባም ያሉት ዶክተር መልሰው አሁን ላይ እያስከተለ ይገኛል ያሉትን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች አንስተዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የኑሮ ውድነትን ጨምሮ በብዙ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዶክተር መልሰው “ ለምሳሌ የጥላቻ ንግግር አንዱ የኑሮ ውድነት አባባሽ እየሆነ ነው ፡፡ በጥላቻ ንግግር ምክንያት አርሶአደሩን ጨምሮ ሰዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ተቸግረዋል ፡፡ ሰው በጥላቻ ምክንያት በሠፈር ተከፋፍሎ እየተቆራቆዘ አርሶአደሩ ማረስ ያልቻለበት ሁኔታ አለ ፡፡ ይህም የምርት መቀነስና ለኑሮ መባባሳ ምክንያት እየሆነ ይገኛል ፡፡ ይህ ማለት ግን ፖሊሲው ችግር የለበትም እያልኩ አይደለም ፡፡ እሱ ሌላ ጉዳይ ነው “ ብለዋል ፡፡
ያልተጣጣመው የመረጃ ፍጆታ እና የሚዲያው ፍጥነት
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የተሠራጩ መረጃዎችንበሙሉ ትክክል አድርጎ የማመን እና የመቀበል ችግሮች በብዛት ይስተዋላሉ ያሉት ደግሞ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰላምና የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ናቸው ፡፡ አምባሳደሩ ለዚህ ምክንያት ነው ያሉት ደግሞ የተጠቃሚው የመረጃ ፍጆታው ከሚዲያው ፍጥነት ጋር የተጣጣመ ሆኖ አለመገኘት ነው ፡፡
ሰዎች ትክክለኛ የሆኑ መረጃዎችን ትክክል ካልሆኑት መለየት እንዳለባቸው የጠቆሙት አምባሳደሩ “ ምክንያቱም ብዝሀ ማንነትን ባቀፈች ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች መቻቻልና መከባበር አለባቸው ፡፡ ለሰላም መደፍረስ ማንኛውም ሰው አስተዋጽኦ እንዳለው ሁሉ ሰላምን ለመገንባት ከግለሰብ ጀምሮ ሁሉም ጥረት ሊያደርግ ይገባል ፡፡ በተለይ በጽሁፍም ሆነ በንግግር የሚገለጹ ድርጊቶቻችንን ከማረቅ አንስቶ የሰላምን ትሩፋት በማስተዋወቅ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል ፤ ብለዋል ፡፡
መፍትሄው ምን ይሆን ?
በውይይቱ ላይ የጥላቻ ንግግርን እንዴት መከላከል ይቻላል በሚለው ላይ ከተወያዮችና ከሀሳብ አቅራቢዎች የተለያዩ የመፍትሄ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል ፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የጥላቻ ንግግርንበህግ መቆጣጠር ይኖርብናል ብለዋል ፡፡ በተለይም ህዝብን የሚያጋጩና ሰላምን የሚያደፈርሱ መልዕክቶችን በሚያሰራጩት ላይ የጥላቻ ንግግር አዋጅን ተፈጻሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና የሥነ ተግባቦት መምህርና ተመራማሪው ዶክተር መልሰው ደጀኔ በበኩላቸው ከትምህር ቤቶች ጀምሮ የህብተሰቡን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ክህሎት / Media literacy / ማሳደግ የችግሩ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል ፡፡ የተወሰኑ ግለሰብ አንቂዎችን ማሠር እና የሚዲያ ተቋማትን ማዕቀብ ለችግሩዘላቂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም የሚል እምንት እንዳላቸው የተናገሩት ዶክተር መልሰው “ ህግ የሚያሥፈልገው ለወንጀሎች ነው ፡፡ የእሳት ማጥፋት / fire brigade approach / ከመከተል ይልቅ ከማዋለ ህጻናት ጀምሮ ከታች መሥራት ይገባል ፡፡ ምክንያቱም ያወቀ ማህበረሰብ ህግ አይጥስም ተብሎ ይታመናል “ ብለዋል ፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና የግሎባል ፒስ ባንክ በጋራ ባዘጋጁት የፓናል ውይይት ላይ ከፍተኛ የመንግስት ተወካዮች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችና አንቂዎች ተሳትፈዋል።
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ