1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ለአሽከርካሪዎች ፈተና እየሆነ መጥቷል የተባለው የጊቤ መንገድ የፀጥታ ይዞታ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ መስከረም 29 2018

ጅማ ዞንን ጨምሮ ደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ አከባቢዎችን ከማዕከላዊ የአገሪቱ አከባቢዎች በሚያገናኘው የጊቤ መንገድ ላይ ተጋርጧል የተባለው የፀጥታ ችግር ፈተና እየደቀነ መምጣቱን አሽከርካሪዎች አመለከቱ ። በዚህ ሳምንት ብቻ በደረሰ የታጣቂዎች ጥቃት አንድ ሾፌር ሕይወቱ አልፎ አንዱ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶበት ሐኪም ቤት መግባቱ ተገልጧል ።

በሹፉርና ሕይወት የሚተዳደሩ አስተያየት ሰጪ ሾፌር እንዳሉት፤ "ከ12 ሰዓት በኋላ ጊቤን ማለፍ አይቻልም ወልቂጤ እደሩ እንባላለን፤ ሌሊት አልፈን ስንሄድ ሾፌር ይገድላሉ ብለዋል
በጅማ እና አዲስ አበባ መካከል ተመላልሰው በሹፉርና ሕይወት የሚተዳደሩ አስተያየት ሰጪ ሾፌር እንዳሉት፤ "ከ12 ሰዓት በኋላ ጊቤን ማለፍ አይቻልም ወልቂጤ እደሩ እንባላለን፤ ሌሊት አልፈን ስንሄድ ሾፌር ይገድላሉ ብለዋልምስል፦ Seyoum Getu Hailu/DW

በዚህ ሳምንት በደረሰ ጥቃት አንድ ሾፌር ሕይወቱ አልፎ አንዱ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶበታል

This browser does not support the audio element.

ጅማ ዞንን ጨምሮ ደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ አከባቢዎችን ከማዕከላዊ የአገሪቱ አከባቢዎች በሚያገናኘው የጊቤ መንገድ ላይ ተጋርጧል የተባለው የፀጥታ ችግር ፈተና እየደቀነ መምጣቱን አሽከርካሪዎች አመለከቱ ። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ በመስመሩ ላይ በመመላለስ የሚሠሩ አሽከርካሪዎች በዚህ ሳምንት ብቻ ሁለት አሽከርካሪዎች ላይ በደረሰው የታጣቂዎች ጥቃት አንድ ሾፌር ሕይወቱ አልፎ አንዱ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶበት ሐኪም ቤት መግባቱን ገልጸዋል ። በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች የፀጥታ ችግሮች ሲከሰቱ በአንጻራዊነት የተሸለ የፀጥታ ይዞታ ሲስተዋልበት በነበረው በዚህ መስመር መንገደኞችም መታገታቸው ተሰምቷል ።

የሾፌሮች ግድያ

በዚሁ ሳምንት መስከረም 27 ቀን፣ በታጣቂዎች ተመቶ ሕይወቱ ያለፈው ሳዳም አባኦሊ የተባለ አሽከርካሪ በበርካታው የአከባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል፡፡ በጅማ ዞን የሶኮሩ ወረዳ ቁምቢ ከተማ ነዋሪ የሆነው አሽከርካሪው አመሻሹን 11 ሰዓት አከባቢ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ወልቂጤን አልፎ ወደ ጅማ አቅጣጫ ጊቤ ወንዝ «ዶልፊን» በተባለ ሚኒባስ ተሽከርካሪ መንገደኞችን ጭኖ በመጓዝ ላይ ሳለ ሰሪቲ በምትባል ስፍራ በጥይት ተመትቶ ማለፉን የቅርቡ ጓደኛው ሀፊዝ አስተያየቱን ለዶቼ ቬለ ሰጥቷል፡፡ "ሳሪቲ በሚባል ስፍራ ነው ተኩሰውበት ህይወቱ ያለፈው” ያሉት የዐይን እማኝ አስተያየት ሰጪው የሟች ጓደኛ ከዚህ በፊትም ሁለት ሾፌሮች በተመሳሳይ መልኩ በዚሁ ስፍራ አከባቢ ከተገደሉ ገና ሁለቱ ወሩ ነው ብለዋል፡፡ ከሟቹ ሾፌር በተጨማሪ አንድ ሌላኛው ሾፌርም በዚሁ ሳምንት ተመቶ ሆስፒታል መግባቱን አስተያየት ሰጪው አክለዋል፡፡

ሌላም አስተያየት ሰጪ አሽከርካሪ አስተያየታቸውን አከሉ፡፡ "ዓመት ሆኖናል፤ መኪና እየተመታብን የጉሮሮ ነገር ስለሆነብን ነው የምንታገለው እንጂ በተደጋጋመሚ የፀጥታ ችግር እያጋጠመን ነው” በማለት ለዚህ ደግሞ አቤት የሚባልበትና እልባት የሚሰት አካል እንደጠፋባቸው በምሬት ተናግረዋልም፡፡

እልባት የሚሻው የመንገደኞች ደህንነት ስጋት

በጅማ እና አዲስ አበባ መካከል ተመላልሰው በሽፉርና ሕይወት የሚተዳደሩ ሌላው አስተያየት ሰጪ ሾፌር እንዳሉት፤ "ከ12 ሰዓት በኋላ ጊቤን ማለፍ አይቻልም ወልቂጤ እደሩ እንባላለን፤ ሌሊት አልፈን ስንሄድ ሾፌር ይገድላሉ፤ አሁን በ27 ሁለት ሾፌሮች ሕዝብ ጭነው ተከታትለው እየተጓዙ አንዱን ሾፌር ገድለው ሌላኛው ቆስሎ ነው ያመለጠው” በማለት በመንገዱ እየተከሰተ ያለውን ስጋት አስረድተዋል፡፡

በራሳቸውም ላይ በመንገዱ የደረሰ አደጋ ተከስቶ እንደሆነ የተጠየቁት እኚህ አሽከርካሪ፤ "ነሐሴ 14 ማለዳውን ከወልቂጤ ወረዳ እንደወጣን በቅርብ ርቀት ላይ ከፊት ለፊቴ የነበረ የአይሱዙ አሽከርካሪ እየዘረፉ ደርሼባቸው አዙሬ ወደ  ወልቂጤ ከተማ  በመመለሴ ልተርፍ ችያለሁ” በማለት መንገዱ ላይ እየተስተዋለ ያለው የደህንነት ስጋት አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዶይቼ ቬለ አሽከርካሪዎቹ ስላቀረቡት የደህንነት ስጋትና እየደረሰ ነው ስላሉት ጥቃት አስተያየታቸውን ለመጠየቅ አደጋው በተፈጠረበት ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ተመስጌን ካሳ የእጅ ስልክ ላይ በመደወልና አጭር መልእክት በመላክ ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልተሳካምምስል፦ Seyoum Getu Hailu/DW

የኃላፊዎች አስተያየት

ዶይቼ ቬለ አሽከርካሪዎቹ ስላቀረቡት የደህንነት ስጋትና እየደረሰ ነው ስላሉት ጥቃት አስተያየታቸውን ለመጠየቅ አደጋው በተፈጠረበት ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ተመስጌን ካሳ የእጅ ስልክ ላይ በመደወልና አጭር መልእክት በመላክ ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጉራጌ ዞን አሸንጌ ወረዳ እያጋጠመ ባለው የፀጥታ ችግር ላይ ዛሬ በወልቂጤ ከተማ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ክልሎች ባለስልጣናት የጋራ ውይይት ስለ መቀመጣቸው ግን ተሰምቷል፡፡ የጅማ ዞን ይፋዊ ኮሚዩኒኬሽን ገጽ እንደዘገበው፤ የሁለቱ ክልሎች እና የፌዴራል የፀጥታ አካል ባለስልጣናት ባደረጉት ውይይት በዚህ በጊቤ መንገድ ላይ እያጋጠመ ያለውን የፀጥታ ችግር እልባት መስጠት በሚያስችል መንገድ ላይ አቅጣጫ ተቀምጧልም፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሓይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW