1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኢትዮጵያ ቀውስ መፍትሔ ሳይበጅ፣ ግጭት ሳይቆም የሽግግር ፍትሕ ተጎጂዎችን ይፈውስ ይሆን?

Eshete Bekele
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 14 2017

በኢትዮጵያ የቀውስ አዙሪት ግድያ፣ አስገድዶ መደፈር እና መፈናቀልን ጨምሮ የተለያዩ ግፎች የተፈጸሙባቸው ዜጎች ፍትሕ ይጠብቃሉ። ሀገሪቱም ለሽግግር ፍትሕ እየተዘጋጀች ነው። የአማራ እና የኦሮሚያ ግጭት ሳይቆሙ፤ ሀገሪቱን ለቀውስ ለዳረጉ ጉዳዮች መፍትሔ ሳይበጅ ተግባራዊ የሚደረግ የሽግግር ፍትሕ ተጎጂዎችን ለመፈወሱ በርካቶች ጥያቄ አላቸው።

ሰላም ለኢትዮጵያ የሚል ሐውልት በአዲስ አበባ
ኢትዮጵያ ለሽግግር ፍትሕ ስትዘጋጅ 17 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ከታኅሳስ 2016 እስከ ታኅሳስ 2017 ባለው አንድ ዓመት ውስጥ ለግጭት ተጋልጠዋል ተብሎ ይገመታል።ምስል Eshete Bekele/DW

ለኢትዮጵያ ቀውስ መፍትሔ ሳይበጅ፣ ግጭት ሳይቆም የሽግግር ፍትሕ ተጎጂዎችን ይፈውስ ይሆን?

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ 17 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ከታኅሳስ 2016 እስከ ታኅሳስ 2017 ባለው አንድ ዓመት ውስጥ ለግጭት ተጋልጠዋል ተብሎ ይገመታል። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚከሰቱ ግጭቶችን እየተከታተለ የሚሰንደው አክሌድ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ግምት “በሥርዓተ-አልበኝነት” ወይም “አለመረጋጋት” ውስጥ የሚኖሩትን የሚመለከት ነው።

ከኢትዮጵያ አስራ ሁለት ክልሎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች መካከል ከታኅሳስ 2016 እስከ ታኅሳስ 2017 ባለው ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለግጭት የተጋለጠባቸው የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ናቸው። በአክሌድ ግምት በአማራ ክልል 7.5 ሚሊዮን ሰዎች በኦሮሚያ ክልል 6.3 ሚሊዮን ሰዎች ለግጭት ተጋልጠዋል።

“…ዕድሌ ደክሞ ነው እንጂ…”

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለግጭት ከተጋለጡ መካከል በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን የደቡብ አቸፈር ወረዳ ነዋሪ የሆነ በግብርና የሚተዳደር ቤተሰብ ይገኝበታል። ዝብስት በተባለች ከተማ ጥቅምት 26 ቀን 2017 በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ከተገደሉ መካከል ለገበያ ወደ ከተማዋ ያቀናው የቤተሰቡ አባል አንዱ ነበር።

“ገበያ ሔዶ ቀርቶ ተጎዳሁኝ እንጂ” ይላሉ በሐዘን የተዘፈቁት የ20 ዓመቱ ወጣት እናት። የልጃቸውን አሟሟት ሲያስረዱ “አየር ወድቆባቸው ቀረ” የሚሉት እናት “ዕድሌ ነው እንጂ” ሲሉ ራሳቸውን ይወቅሳሉ።

ዶይቼ ቬለ የሟቹን ቤተሰቦች ሊደርስባቸው ከሚችል ጥቃት ለመጠበቅ ማንነታቸውን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

የ9ኛ ክፍል ተማሪ የነበረው ልጃቸው በአማራ ክልል በመንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ሲቀሰቀስ ትምህርቱ ተቋርጧል። ፊቱን ወደ አልባሳት ንግድ ያዞረው የቤተሰቦቹ ሸክም ከመሆን ለመዳን ነበር። “ሊበን ይሔዳል፣ ዝብስት ይሔዳል፤ ዱር ቤቴ ይውላል” ይላሉ አባት የልጃቸውን የንግድ እንቅስቃሴ መለስ ብለስ ሲያስታውሱ።

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሔዱ ግጭቶች እና የሲቪክ ምኅዳሩ መዘጋት “በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የሽግግር ፍትኅን ፈጽሞ የማይቻል እንኳ ባይሆን አስቸጋሪ ያደርገዋል” ሲሉ አምባሳደር ቤትዝ ቫን ስካክ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።ምስል Rod Lamkey/CNP/picture alliance

በዕለተ-ሰኞ ወጣቱ ለተመሳሳይ ዓላማ ወደ ዝብስት አቅንቷል። በትንሿ ከተማ ማክሰኞ የሚቆም ገበያ ነበር። በዕለቱ በከተማዋ በገበያ፣ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ ላይ ጉዳት ያደረሰ የድሮን ጥቃት ተፈጸመ። ጥቃቱ በአማራ ክልል በርካታ ሰዎች ከተገደሉባቸው የድሮን ጥቃቶ አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል። አባት ከዝብስት የስልክ ጥሪ ደረሳቸው።

ከሟቾቹ መካከል አንዱ ልጃቸው እንደሆነ የተለየው በመታወቂያው ነበር። “አብረውት የሔዱ ጓደኞቹ ወድቀው አገኘናቸው” ይላሉ አባት። “መንግሥት ገበያ በዋለበት እንዴት ይጥላል ብለን፤ የምናመለክተው አጥተን ልጆቻችንን አምጥተን በቤተ-ክርስቲያን ቀበርን” ሲሉ ተናግረዋል።

በዝብስት በተፈጸመው የድሮን ጥቃት የ20 ዓመት ልጃቸውን የተነጠቁት እናት እና አባት በግጭት አዙሪት በተዘፈቀችው ኢትዮጵያ ፍትሕ ከሚጠብቁ ዜጎች መካከል ሆነዋል።

መቋጫ ያልተበጀላቸው የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ግጭቶች 

ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በአማራ ክልል፤ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በኦሮሚያ ክልል በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች ኢትዮጵያ ላቀደችው የሽግግር ፍትሕ ፈተና የጋረጡ ናቸው።

ኢትዮጵያ ያቀደችውን የሽግግር ፍትሕ ሒደት በቅርብ ከሚከታተሉ የውጪ ዲፕሎማቶች አንዷ የሆኑት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍትሕ አምባሳደር ቤትዝ ቫን ስካክ “በኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሒደት ተበረታተናል” ቢሉም “የሲቪክ ምኅዳሩ መዘጋት” እና በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸሙ የሚገኙ ጥሰቶች አሳሳቢ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ስካክ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የጸጥታ ጥናት ተቋም በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ዝግጅት ላይ ባካሔዱት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ተሳትፈው ሲመለሱ “ይኸ በእርግጠኝነት በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የሽግግር ፍትሕን ፈጽሞ የማይቻል እንኳ ባይሆን አስቸጋሪ ያደርገዋል” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

“ሰዎች እውነቱን ለመናገር ነጻነት ከሌላቸው በፍትሕ ሒደት ውስጥ ሊሳተፉ እንደማይችሉ እናውቃለን” ያሉት አሜሪካዊቷ ዲፕሎማት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች በፖለቲካዊ ውይይት ሊፈቱ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በሁለቱ ክልሎች በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች ብርቱ ሰብአዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳት ቢያስከትሉም መንግሥት ከታጣቂዎቹ ጋር በመነጋገር መፍታት አልቻለም። በሰኚ ነጋሳ የሚመራው አንድ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አንጃ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር በቅርቡ የተፈራረመው ሥምምነት ለክልሉ ቀውስ የተሟላ መፍትሔ ለማበጀቱ በርካቶች ጥርጣሬ አላቸው።

ኩምሣ ድሪባ ከሚመሩት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር የተጀመሩ የድርድር ጥረቶች አልተሳኩም። በአማራ ክልል ከመንግሥት ከሚዋጉ የፋኖ ታጣቂዎች ጋር ድርድር እንዲካሔድ በተለያዩ ወገኖች ግፊት ቢደረግም የተጀመረ ነገር የለም።

ሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች “አንድ ሺሕ ዓመት ቢታገሉ ስለማያሸንፉ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ወደ ሰላም እንዲመጡ” ጥሪ አቅርበዋል።

በሰኚ ነጋሳ የሚመራው አንድ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አንጃ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር የተፈራረመው ሥምምነት ለቀውሱ ኹነኛ መፍትሔ ማበጀት ስለመቻሉ በርካቶች ጥርጣሬ አላቸው። ምስል Oromia communication

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ያጸደቀው ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ነበር። በጄኔቫ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ እና የሰብአዊ መብቶች አካዳሚ ተመራማሪው ዶክተር ውብሸት ቁምላቸው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው መጽደቅ እና ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ሕጎች ዝግጅት “መልካም” እንደሆነ ይስማማሉ።

ይሁንና በቆዳ ስፋት እና በሕዝብ ብዛት ቀዳሚውን ድርሻ በሚይዙት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሚካሔዱ ግጭቶች ሳይቆሙ የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር ተቀባይነት እንዳይኖረው ሊያደርግ እንደሚችል ሥጋት አላቸው።

በሽግግር ፍትሕ በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች በባለቤትነት ሊሳተፉ እንደሚገባ የሚናገሩት የሕግ ተመራማሪው አሁን ያለው አካሔድ ጉዳዩን “የፍትሕ ሚኒስቴር የሚሰጠው” ሊያስመስለው እንደሚችል ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዶክተር ውብሸት እንደሚሉት የሽግግር ፍትሕ አካል የሚሆኑ ምርመራ እና እውነት ማውጣትን የመሳሰሉ ሒደቶች ግጭቶች ባለባቸው አካባቢዎች ማካሔድ ፈታኝ ሊሆን ይችላል።

የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዋና ዓላማ “ዘላቂ ሰላም፣ ዕርቅ፣ የህግ የበላይነት፣ ፍትሕ እና ዲሞክራሲ የሚረጋገጥበትን መደላድል መፍጠር ነው።” በፖሊሲው መሠረት “በሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚከናወነው የወንጀል ምርመራ እና ክስ የመመስረት ተግባር አሁን ካለው የወንጀል ምርመራ እና ዐቃቤ ሕግ ተቋም ውጪ በሆነ፣ ነጻ እና ገለልተኛ” ተቋም ነው። አዲስ የሚቋቋመው ልዩ ዐቃቤ ሕግ መርማሪዎችን እና ዐቃብያነ ሕግን የመምራት ኃላፊነት ይሰጠዋል።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥር “በማህበረሰቡ፣ በተጎጂዎች እና በተከሳሶች አመኔታ እና ተቀባይነት የሚኖረው” ልዩ ችሎት የሚደራጅ ይሆናል። በልዩ ችሎቱ “የውጪ ሀገራት ባለሙያዎች በአማካሪነት እና አሰልጣኝነት እንዲሳተፉ” ለማድረግ ታቅዷል። ከዚህ በተጨማሪ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን እና የተቋማት ማሻሻያ ኮሚሽን ይቋቋማሉ። በኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ ያልተካተቱ ወንጀሎችን ለመዳኘት የዓለም አቀፍ ወንጀሎች ተጠያቂነት አዋጅም ይዘጋጃል።

የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርአያሥላሴ ሦስቱ ተቋማት፣ አንድ ልዩ ችሎት እና የዓለም አቀፍ ወንጀሎች ተጠያቂነት አዋጅ የሚዘጋጁት “በማሕበረሰቡ ዘንድ ተዓማኒነት ያላቸው አዳዲስ ተቋማት አስፈላጊ” በመሆናቸው እንደሆነ ከሁለት ሣምንታት በፊት በአዲስ አበባ በሕግ ረቂቆቹ ላይ ከተደረገ ውይይት በኋላ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የሚደረገው ውጊያ በፖለቲካዊ ውይይት እንዲፈታ ከተለያዩ ወገኖች ግፊት ቢደረግም እስካሁን በተጨባጭ የታየ ለውጥ የለም። ምስል Mariel Müller/DW

“ሁሉም ሰው ሊስማማባቸው የሚችል የሹመት ሒደታቸው ግልጽ የሆነ እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክትትል የሚደረግበት ሒደት በማድረግ ሁሉንም ያሳተፈ እንዲሁም ደግሞ ለተጎጂዎች ትኩረት የሰጠ አካታች ሒደት የተከተለ የተቋማት ምሥረታ አስፈላጊ ስለሆነ ነው” ሲሉ የፍትሕ ሚኒስትሯ ሐና አርአያሥላሴ አስረድተዋል።

ፖሊሲው እንደሚለው ለወንጀል ተጠያቂነት በሽግግር ፍትሕ የሚታዩት በሥራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ወዲህ የተፈጸሙ ጥሰቶች ናቸው። በሒደቱ ምርመራ የሚካሔድባቸው እና ክስ የሚመሠረትባቸው “በጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወይም አፈፃፀም ሒደት ከፍተኛ ደረጃ የወንጀል ተሳትፎ ያላቸው አጥፊዎች” ናቸው።

ዶክተር ውብሸት ቁምላቸው ግን “ዋና አጥፊ የተባሉ ሰዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለወይ?” የሚለው ጥያቄ አሳሳቢ እንደሚሆን ይናገራሉ። “ተጠያቂ ይሆናሉ የሚባሉ ሰዎች አንድም ሥልጣን ላይ ናቸው ወይንም ደግሞ ሒደቱን ለማደናቀፍ ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ አላቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

“ቧልት”?

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ “በመንግሥት አደራጅነት ከሚቋቋም የሽግግር ፍትሕ ተቋም ከዚህ በፊት ከተቋቋሙት እና ያለ ውጤትና ሪፖርት ከተበተኑት ኮሚሽኖች የተለየ ውጤት አይጠበቅም” በማለት ተችቷል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ እና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲን የሚያካትተው ኮከስ “በመደበኛ የመንግሥት አስተዳደር ወቅት ተግባራዊ ያልተደረገ የፍትህ ሥርዓት በሽግግር ፍትሕ አሰፍናለሁ ማለት ከቧልት ያለፈ ስሜት አይሰጥም” የሚል አቋም አለው።

በመንግሥት የሽግግር ፍትሕ ዝግጅት ላይ ብርቱ ትችት ከሰነዘሩ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ፌድራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፣ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የኦሮሞ ፌድራላዊ ኮንግረስ ጭምር ይገኙበታል። ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫቸው “አካታች፣ አሳታፊ እና ተዓማኒ የሽግግር ሂደትና ተቀባይነት ያለው ህጋዊ የፍትሕ ሥርዓት እንዲዘረጋ እና እንዲተገበር” ጥሪ አቅርበዋል።

የሽግግር ፍትሕ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና ፌድራል መንግሥት በተፈራረሙት የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት የተካተተ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ሥምምነቱ እንዲፈረም ከፍ ያለ ግፊት ያደረገችው የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለሁለት ዓመታት በተደረገው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተሳተፉ ኃይሎች ሁሉ “የጦር ወንጀል” ፈጽመዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

በብሊንከን ድምዳሜ መሠረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ጦር እና በወቅቱ ከፌድራል መንግሥቱ ጎን ተሰልፈው ይዋጉ የነበሩ የአማራ ኃይሎች “በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ፈጽመዋል።” ይኸ “ማሰቃየት፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች” የሚጨምር ነው።

በፕሪቶሪያው ግጭት የማቆም ሥምምነት ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት እና በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ መሠረት ተጠያቂነት እና ፍትሕን ለማረጋገጥ ግዴታ ገብተዋል። 

በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት አሰቃቂ ጦርነት በተደረገበት ወቅት በትግራይ ክልል ተገደው የተደፈሩ በርካታ እንስቶች ፍትሕ በመጠበቅ ላይ ናቸው። ምስል Ximena Borrazas

በተለይ በትግራይ ክልል ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሚወነጀለው የኢትዮጵያ መንግሥት ፍትሕ እና ተጠያቂነት ማረጋገጥ ይችል እንደሁ የተጠየቁት አምባሳደር ቤትዝ “መንግሥት ስለ ራሱ ያለፈ ታሪክ ሐቀኛ ሊሆን እና በራሱ የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙ አጥፊዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ትክክለኛ እርምጃ ሊወስድ ያስፈልጋል”  ሲሉ ተናግረዋል።

“በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የተወሰኑ ችሎቶች እና የሥነ ምግባር ዳኝነቶች” እንደነበሩ ያስታወሱት አምባሳደር ቤትዝ ቫን ስካክ “ግልጽ ባለመሆናቸው ማን ለየትኞቹ ወንጀሎች እንደተከሰሰ ምን አይነት ቅጣት እንደተላለፈ የምናውቀው ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ከግጭት አዙሪት ለመውጣት የመረጠቻቸው የሽግግር ፍትሕ እና የብሔራዊ ምክክር መንገዶች በሰላም እና በፍትሕ መካከል ውጥረት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይሰጋሉ። በሰብአዊ መብቶች ጥሰት የተጠረጠሩ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ይሁን የታጣቂዎች መሪዎችን ከሕግ ፊት ለማቆም መሞከር ከምክክር እና ድርድር ሊያሸሽ ይችላል። ፍትሕን ቸል ማለት በአንጻሩ ለአጥፊዎች የልብ ልብ የመስጠት አቅም አለው።

አምባሳደር ቤትዝ ቫን ስካክ ለሽግግር ፍትሕ የተደላደለ መሠረት ለመጣል “በጥሰት የተወነጀሉ ሰዎችን ከሥልጣን ማንሳት” ለመንግሥት “ትርጉም ያለው እርምጃ” እንደሚሆን ጠቁመዋል። “በተለይ በወንጀል የተከሰሱ የሠራዊት አባላትን ሙሉ ምርመራ እኪደረግ ድረስ አስተዳደራዊ ፈቃድ መስጠት” ዲፕሎማቷ ያቀረቡት ምክረ ሐሳብ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት ለተፈጸሙ ጥሰቶች “በይፋ እውቅና መስጠት” እንደሚኖርበት መክረዋል።

ፍትሕ የሚጠብቁ ተጎጂዎች የገጠሟቸው ግጭቶች እና ብርቱ ጥሰቶች ያገረሻሉ የሚል የማያቋርጥ ሥጋት አላቸው። “በአጭር ጊዜ ተፈጻሚ ቢሆን እና የተፈናቀለው፣ ወንጀል የተሠራበት፣ የተገደለው ፍትሕ ቢያገኝ መልካም ነው” የሚሉት ዶክተር ውብሸት ቁምላቸው የሽግግር ፍትሕ ከሚያካትታቸው ሒደቶች አኳያ ረዥም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል አስገንዝበዋል።  

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW