ለኢትዮጵያ ከዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ምን አለ?
ረቡዕ፣ መጋቢት 10 2017
ለዓለም ንግድ ድርጅት ላቀረበችው የአባልነት ማመልከቻ “ማነቆ” በነበሩ የማክሮ-ኢኮኖሚ እና የንግድ ሥርዓቶች ላይ ማሻሻያ እያደረገች የምትገኘው ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ጄኔቫ ተመልሳለች። የድርጅቱ አባል ሀገራት በቡድን ከኢትዮጵያ ልዑካን ጋር የተደራደሩበት አምስተኛ ስብሰባ ዛሬ ተካሒዷል።
በዋና ተደራዳሪነት የኢትዮጵያን ልዑክ የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ይመራሉ። የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ፣ የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እና የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን በልዑካን ቡድኑ ውስጥ ተካተዋል።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና ማመልከቻዋን የሚመረምረው የዓለም ንግድ ድርጅት ኮሚቴ አራተኛ ስብሰባ የተካሔደው ማሞ ምኅረቱ ዋና ተደራዳሪ ሣሉ ነበር። የሚንፏቀቀውን ሒደት ለማስቀጠል የቀድሞው የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በሐምሌ 2015 ወደ ድርጅቱ ብቅ ብለው የነበረ ቢሆንም ድርድሩን “ያለ ማቋረጥ ለመቀጠል” የነበራቸው ተስፋ 20 ወራት ገደማ ዘግይቷል።
የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ወደ ጄኔቫ ያቀኑት መንግሥታቸው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ሊብራል ሥርዓት የሚመሩ በርካታ ማሻሻያዎች ተግባራዊ እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ነው። ማሻሻያዎቹ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተፈቀዱ የሥራ ዘርፎችን ለውጪ ባለወረቶች እና ኩባንያዎች ከፍተዋል።
“የውጪ የንግድ ሸሪኮች ሊያነሷቸው የሚችሉ አብዛኞቹ ችግር ተብለው ከዚህ በፊት በነበረው ሒደት ውስጥ የሚወሰዱ ነገሮች አሁን መንግሥት በራሱ ፈቃደኝነት እያነሳቸው ነው” የሚሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም “ከከዚህ በፊቱ በተሻለ ሁኔታ መደላድል አለ” የሚል ዕምነት አላቸው።
አራተኛው የኮሚቴው ስብሰባ ከተካሔደ ወዲህ ለውጪ ኩባንያዎች ተዘግቶ የቆየው የቴሌኮም ገበያ ተከፍቶ የአምስት ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው ሳፋሪኮም ከመንግሥታዊው ኢትዮ-ቴሌኮም እየተፎካከረ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በገቢ፣ ወጪ፣ የጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ የውጭ ባለወረቶች እንዲሰማሩ ፈቅዷል።
በጥር 2017 ሥራ የጀመረው የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር ከተከናወኑ ተጠቃሽ ሥራዎች አንዱ ነው። የባንክ ሥራ አዋጅ ተሻሽሎ ገበያው የውጪ ሀገር የፋይናንስ ተቋማትን እየጠበቀ ነው። ይሁና አሁንም በአባል ሀገራት የሚነሱ እና ሒደቱ “በፍጥነት እንዳይከናወን” ሊያደርጉ የሚችሉ ቀሪ ጉዳዮች ይኖራሉ።
“ኢትዮጵያ ማቅረብ የማትችላቸው የተወሰኑ በሕግ ማዕቀፍ እና በማስተማመኛ ረገድ የሚነሱ አሁንም አጨቃጫቂ የሆኑ ነገሮች አሉ” የሚሉት አቶ ጌታቸው በተለይ የውጪ ባለሀብቶች ወደ ሀገሪቱ ገብተው በሚሠሩበት ወቅት “ከእነሱ ወይንም ከንግድ ሥርዓቱ ውጪ ለሆነ ለምሳሌ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚደርሱ አይነት ችግሮች የሚሰጡ ዓለም አቀፍ መተማመኛዎች በኢትዮጵያ አሁንም የሉም” በማለት አስረድተዋል።
አቶ ጌታቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ “ተገማች የሆነ የንግድ ፖሊሲ ሥርዓት” መፍጠር ይገባታል። “ግልጽ የሆነ የንግድ ፖሊሲ ሥርዓት አለመኖር” ሌላው በኢትዮጵያ ላይ የሚነሳ ጥያቄ ነው። በንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ ረቂቅ ገና ውይይት እየተደረገበት ይገኛል። ፖሊሲው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ የሚተገበር ከሆነ አቶ ጌታቸው “የተወሰነ ግልጽነት ማምጣት ይችል ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ “በሸሪኮች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የሀገር ውስጥ ሥርዓቱ ምን ያህል ጠንካራ ነው?” የሚለው ጉዳይ በድርድሩ ሊነሳ የሚችል ነው። “ግልጽ የሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት፤ ከፖለቲካ ነጻ የሆነ፤ መገመት የሚችል የችግር መፍቺያ ሥርዓት” በኢትዮጵያ ስለመኖሩ ጥያቄ እንደሚቀርብ የሚያስረዱት አቶ ጌታቸው የሕግ ማዕቀፎች፣ የዳኝነት ሥርዓት እና ተያያዥ ነገሮች መነጋገሪያ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
ሀገሪቱ ከአእምሯዊ ንብረት (intellectual property) አንጻር “ጠንካራ የሚባል የመብት ጥበቃ ሥርዓት” እንደሌላት የሚያስታውሱት አቶ ጌታቸው ጉዳዩ በንግድ ሸሪኮች የሚነሳ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ውይይት እየተደረገበት የሚገኘው የንግድ ፖሊሲ ረቂቅ ኢትዮጵያ 166 አባላት ያሉትን ድርጅት ብትቀላቀል በዓለም ገበያ ለምትሸጣቸው ሸቀጦች (export) “ከሌሎች የዓለም ንግድ ድርጅት አባል አገራት ዕኩል የገበያ ዕድል እንዲያገኙ ያስችላል” የሚል ተስፋ የሰነቀ ነው። የምጣኔ ሐብት ተመራማሪው ዶክተር በሪሁ አሰፋ “ለምሳሌ የአውሮፓ ገበያ ውስጥ ለመግባት ብዙ ከታሪፍ ውጪ የሆኑ ግዴታዎች አሉ። እነዚያን ግዴታዎች ማሟላት ለብዙ የአፍሪካ ኢንተርፕራይዞች ከባድ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።
“ታሪፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ የሚከለክል አይደለም። የኢትዮጵያም ታሪፍ ዝቅተኛ ነው። ኢትዮጵያም ወደ ሌላ ሀገር በምትልክበት ጊዜ ታሪፍ ብዙ ከባድ አይሆንም” የሚሉት የምጣኔ ሐብት ተመራማሪው “ታሪፍ ያልሆኑ እንቅፋቶች በሥምምነት” እንደሚነሱ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ “የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ስትሆን ሥርዓቱ አድሏዊ ስለማይሆን ይነሳሉ” የሚሉት ዶክተር በሪሁ “ይህ ትልቅ የገበያ ዕድል ይሰጣል” በማለት ፋይዳውን አብራርተዋል።
በእርግጥም የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ኢትዮጵያ በይበልጥ ለምትታወቅባቸው የግብርና ምርቶች አዲስም ባይሆን የወጪ ንግድ ቀረጥን (export tax) በመቀነስ “ሰፋ ያለ የገበያ ዕድል” ሊፈጥር እንደሚችል አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ብትሆን ለዓለም ገበያ የምታቀርበው እንደ ከዚህ ቀደሙ በዋናነት እንደ ቡና ያሉ የግብርና ምርቶችን ነው። የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሀገሪቱ የገበሬዎች እና የአምራቾችን ተወዳዳሪነት ለማጠናከር የምታደርጋቸውን ድጎማዎች በግልጽ የማሳወቅ ብቻ ሳይሆን የመቀነስ ግዴታ ውስጥ ይከታታል። ሌሎች የድርጅቱ አባል ሀገሮች “ድጎማን የውድድር መድረኩን እንደ ማዛነፍ ስለሚቆጥሩት” አቶ ጌታቸው እንደሚሉት “ለገበሬዎች ድጎማ እና የተለያዩ ድጋፎች እንዳታደርግ የሚከላከሉበት አሠራር ይኖራቸዋል።”
የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ኢትዮጵያ የምትሻውን የውጪ መዋዕለ-ንዋይ (FDI) ለመሳብ ጭምር ዕድል እንደሚፈጥር ዶክተር በሪሁ ዕምነታቸው ነው። ለዚህ ደግሞ የውጪ ባለሀብቶች ለሥራቸው የሚያስፈልጓቸው የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የሠራተኛ ወጪ እና መሬት “ርካሽ” መሆናቸው አስተዋጽዖ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለውጪ ባለወረቶች “እነዚህን ነገሮች ተጠቅማችሁ፤ አምርታችሁ ዕቃዎቻችሁን ወይም ምርቶቻችሁን ሰፊ ገበያ ላይ መሸጥ ትችላላችሁ” የሚል ማሳመኛ ታገኛለች። “ምክንያቱ ‘እኛ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ነን’ ሲባሉ የሚፈልጉት ነገር ነው የሚሆነው” ሲሉ ዶክተር በሪሁ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ብትሆን ገበያዋን ለአባል ሀገራት አሁን ካለው በተሻለ መጠን መክፈት ይጠበቅባታል። በገበያ ረገድ የፈረጠመ አቅም ካላቸው አባል ሀገራት የሚነሱ ተቃውሞዎችን በራሱ በዓለም ንግድ ድርጅት መድረክ መከራከር ከፍተኛ ወጪ እና ትልቅ የመሟገት አቅም የሚጠይቅ ነው።
ዶክተር በሪሁ ግን “ማንም ሀገር የዓለም ንግድ ድርጅት የሚገባው ሁሉንም ጨርሶ ኢንዱስትሪውን አሳድጎ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ አይደለም” የሚል አቋም አላቸው። “የዓለም የንግድ ድርጅት እንደ መማሪያም ነው” የሚሉት የምጣኔ ሐብት ተመራማሪው በአባልነት ከሚገኙት “የተወሰኑ ጥቅሞች” ባሻገር ኢትዮጵያ ውድድር ውስጥ ስትገባ ተገዳ ተግባራዊ የምታደርጋቸው ጉዳዮች ፋይዳ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።
ከ30 ዓመታት በፊት የተመሠረተው ድርጅት በዓለም ንግድ ውስጥ የሚፈጠሩ ውዝግቦችን ለመፍታት እንደ ዳኛ ይቆጠራል። ካናዳ እና ሜክሲኮ ወደ አሜሪካ በሚልኳቸው ሸቀጦች ላይ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የጣለባቸውን ቀረጥ በመቃወም አቤቱታ ያቀረቡት ለዓለም ንግድ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ንግድ ድርድር የሚደረግበት ብቻ ሳይሆን ሕግጋት የሚበጁበትም ሆኖ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አቅሙን እያጣ አባላቱም ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ እና ተገዳዳሪዎቻቸውን ለመቅጣት ሕግጋቱን እየጣሱ መሔዳቸውን ባለሙያዎች ታዝበዋል።
ኢትዮጵያ ከ22 ዓመታት በፊት አባል ለመሆን የጀመረችውን ሒደት በዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ቆርጣ የተነሳችው የዓለም የንግድ ሥርዓት ጫና ውስጥ በሚገኝበት ወቅት ነው። የተባበሩት መንግሥታት በማደግ ላይ የሚባሉ ሀገራትን ጥቅም ለመደገፍ ያቋቋመው የንግድ እና ልማት ሴክሬታሪያት ባልደረባ የሆኑ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን “እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገሮች የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆናቸው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምንም ጥቅም አያመጣም” የሚል ዕምነታቸውን ለዶይቼ ቬለ አጋርተዋል።
የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸውም ተክለማርያም “በዚህ ሰዓት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚደረግ እንቅስቃሴ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል” የሚል ዕምነት አላቸው። የዓለም የንግድ ድርጅት በአባላቱ “የሚታመን፤ በአባል ሀገራት መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ጠንካራ ሥርዓት፣ የማስገደድ አቅም እና ተደማጭነት ያለው ተቋም ቢሆን” ኢትዮጵያ የምታገኘው ጥቅም እንደሚኖር አላጡትም።
“ጊዜው ግን በተቋሙ እና ተቋሙ በሠራቸው ሥርዓቶች ላይ ከፍተኛ ጥያቄ የሚነሳበት፤ የተቋሙም መኖር በራሱ ጥያቄ ውስጥ የገባበት ጊዜ ነው” ሲሉ አቶ ጌታቸው ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። የዓለም የንግድ ሥርዓት “ሀገራት የንግድ ፍላጎቶቻቸውን እና በንግድ ረገድ ያላቸውን ምኞት በራሳቸው እጅ ውስጥ ለማስገባት የሚፎካከሩበት ጊዜ ነው” ሲሉ አቶ ጌታቸው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ከመሆኗ በላይ በድርድሩ የምታልፍባቸው ሒደቶች ለኢኮኖሚዋ “የተሻለ ጥቅም” እንደሚኖራቸው አቶ ጌታቸው ያምናሉ። በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ “ምን አልባት ውድድር ወደ ተሻለ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ይመራል የሚል ዕሳቤ” ሳይኖር እንዳልቀረ ተገንዝበዋል። ይህ በማምረት ሒደት ውስጥ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ ድርጅቶች እና ተቋማት የተሻለ እሴት የመጨመር አቅም እንዲያጎለብቱ ማጠናከርን ይጨምራል።
ከዚህ በፊት የኢትዮጵያን ገበያ ከሌሎች ሀገራት ከሚመጣ ውድድር ጠብቆ ያቆየው አሠራር አዋጪ አለመሆን መንግሥትን ወደ ነጻ ገበያ እንዲያመራ ገፊ ምክንያት የሚሆን ነው። ውድድር የታቀደውን ለማሳካት ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሚያምኑት አቶ ጌታቸው “የኢትዮጵያ ድርጅቶች፣ ተቋማት፣ አምራቾች እና ገበሬዎች በዚህ ውድድር ውስጥ ህልውናቸውን አስጠብቀው መቆየት ይችላሉ የሚለውን ነገር እርግጠኛ መሆን” እንደማይቻል ግን አስረድተዋል።
እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ