1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኦሮሚያው ግጭት ዘላቂ እልባት ከየት ይምጣ?

ሰኞ፣ ሰኔ 26 2015

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በሚያዝያ የጀመሩት የሰላም ንግግር ለኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ችግር መፍትሔ ያበጃል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር። የሁለቱ ወገኖች የሰላም ንግግር እንደቆመ ሲሆን እስካሁን በተጨባጭ የታየ ለውጥ የለም። የክልሉ ነዋሪዎች እሮሮም እንደቀጠለ ነው።

Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Deutsch

ለኦሮሚያው ግጭት ዘላቂ እልባት ከየት ይምጣ?

This browser does not support the audio element.

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ በምዕራብ ኦሮሚያ የቀለም ወለጋ ዞን ነዋሪ በአካባቢያቸው "እንደ ከዚህ ቀደሙ የከፋ አለመረጋጋት ባይኖርም ፍጹም ሰላምም ሰፍኗል የሚያስብል ሁኔታ አይስተዋልም" ባይ ናቸው፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው፤ አሁን ላይ ቤተሰቦቻቸው በሚገኙበት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አባይ ጮመን እና ጉዱሩ ወረዳዎች ግን ምንም የተረጋጋ ሁኔታ የለም፡፡ “አሁን እዚህ በምኖርበት ቀለም ወለጋ የተሻለ ሰላም ይስተዋላል፡፡ ግን ይህ ምን ያህል ዘላቂ ነው ብትለኝ ምንም ዋስትና የለም፡፡ በተለይም ደግሞ ቤተሰቦቼ በሙሉ በምገኙበት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጮመን እና ጉዱሩ አከባቢ ጦርነት በመኖሩ ኔትዎርክም ተቋርጧል ሰላም የለም፡፡” ነዋሪነታቸውን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ያደረጉት ሌላው አስተያየት ሰጪ እንደሚሉትም፤ በነዚህ አከባቢም ማህበረሰቡ የተረጋጋ አከባቢ ውስጥ ሆኖ ኑሮውን መግፋት ተስኖታል ይላሉ፡፡

“በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በቅርቡ ኔትዎርክ ተለቆልን ደስ ብሎን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እሱም ተቋርጧል፡፡፡ ወጣ ብዬ ነው እያናገርኩህ ያለውት፡፡ መንግስት አሁን በተለያዩ አቅጣጫዎች ወታደራዊ ኃይሉን እያሰማራ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ይህ ሁሉ አለመረጋጋት ከመንግስት እይታ ውጪ ነው የሚል እምነትም የለንም፡፡ ሰው በሰላም እጦት ተጎሳቁለው ተሰቃይቷልም፡፡ አሁን እኮ እኛ ጋር በወረዳችን ሰው ተፈናቅለው ከሚኖርባቸው ኦቦራ እና አገምሳ ከተሞች 300ሜትር እንኳ ወጣ ማለት አዳጋች ሆኗል፡፡ እዚሁ ጎረቤታችን ወረዳ ጃርደጋ ጃርቴም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሰው እኮ በከተማ ተጨናንቆ በርሃብ ስቃይ እየተሰቃየ ነው፡፡” 

ከሳምንታ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሚያ በስፋት ይንቀሳቀሳል በሚባለው መንግስት ‘ሸነ’ ባለውና እራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል በታንዛኒያ ለቀናት ተካሂዶ የነበረው የሰላም ምክክር በውል የሚታወቅ ስምምነት ላይ ሳይደርስ መጠናቀቁን ተከትሎ ተስፋ ታይቶበት የነበረው የክልሉ ፀጥታ ዳግም መክፋቱ ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ሁለቱ ተደራዳሪ ቡድኖች ግን በወቅቱ በተደረገው ምክክር የተቆረጠ የሰላም ስምምነት ላይ ባይደረስም በቀጣይነት ስምምነቱ ሊቀጥል በሚችልበት ሁኔታ ላይ መስማማታቸውን ገልጸው ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ ግን በመንግስት በኩልም ስለዚህ ስምምነት መቀጠል አለመቀጠል ብያንስ እስካሁን በግልጽ የተባለ ነገር የለም፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ዓለማቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢም ሰሞኑን በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት መልእክት አሁን ላይ እየተካሄደ ያለ ሰላምምነትም ሆነ በቀጣይነት እቅድ የተያዘለት የምክክር መርሃ ግብር የለም ብለዋል፡፡ ይሁንና ጦራቸው አሁንም ለሰላማዊ ውይይት ቁርጠኛ መሆኑን በዚሁ ጽሁፋቸው ጠቁመዋል፡፡ በመንግስት በኩል በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት እንደ እልባት ስለተቀመጠ አቅጣጫ ለመጠየቅ ለክልሉ ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ለሰላም ሚኒስቴር ባለስልጣናት ደውለን ምላሻቸውን ማግኘት አልሰመረልንም፡፡

የኦሮሚያውን የፖለቲካ ሁናቴ በቅርበት የሚከታተሉት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ባለሙያ እና የሶስተኛ ድግሪ ተማሪ አቶ መብራቱ ገርጅሶ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ግን የታንዛኒያው ድርድር እንደተጣለበት ተስፋ ሳይሆን ያለስምምነት ብጠናቀቅም አሁንም ብሆን ያንን መንገድ መከተል የተሻለ እልባት ይሆናል ባይ ናቸው፡፡ 

“በተለያየ ደረጃ በተደራዳሪ ቡድኖቹ ይቀጥላል የተባልነው የሰላም ስምምነት አሁን ላይ ከምን እንደደረሰ አናውቅም፡፡ ምን ላይ እንደተግብቡና ምን ነጥብ ልዩነት እንደፈጠረባቸውም እንደህዝብ አናቅም፡፡ በታሪካችን እንደምንረዳው ጦርነት ቀውስ እንጂ መፍትሄ አላመጣምና አሁንም ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታ ብሰራ መልካም ይመስለኛል፡፡ አሁን የትኛውም አካል በጦርነት አሸናፊ ብሆን እንኳ ነገ መልሰን ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ ላለመግባታችን ዋስትና የለም፡፡”

የኦሮሚያው አለመረጋጋት ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሰላማዊ እልባትን እንደሚያሻው በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ይሰማል፡፡ ባለፈው ሳምንት 50ኛውን የምስረታ በዓል ያከበረው አንጋፋዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እንኳ በኦሮሚያ ህዝብን የሚያሳርፈው ሰላማዊ የፖለቲካ መፍትሄ ይምጣ ሲል በአጽእኖት መጠየቁ ይታወሳል፡፡

የሰላምና ደህንነት ባለሙያው አቶ መብራቱም የህዝብ ፍላጎት በሰላም ወጣቶ መግባት ነው ሲሉ የሰላምን አስፈላጊነት አጉልተው አንስተዋል፡፡ “ሰላም በተጓተተ ቁጥር የሰውና ቁሳዊ ጉዳቱ ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ማህበረሰብ ሲባል በግጭቱ ውስጥ የሚገኙ አካላት ወደሚያግባባቸው ነጥብ ብመጡ የተሸለ ይሆናል፡፡ አሁን ከኦሮሚያም ባሻገር ለተስፋፋው ጦርነት የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ሰላምን ያመጣ እንደሆነ ለዚያ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡” ኦሮሚያ ውስጥ በተለይም በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ ቢያንስ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው አለመረጋጋት በዜጎች ደህንነት እና ተረጋግቶ ህይወታቸውን መምራት ላይ የጎላ ጥላ ማጥላት ተደጋግሞ መዘገቡ ይታወሳል።

ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW