1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኦሮሚያ ግጭት የሰላም አማራጭ ጥሪ

ረቡዕ፣ የካቲት 8 2015

«የዚህ ደብዳቤ ዓላማ ታጥቀው መንግስትን የሚገዳደረውን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ወይም መንግስትን ለመጥቀም ወይም ለመጥቀም ሳይሆን በዚህም በዚያም አንዱ ሌላውን ደገፍክ እያለ የሚያሰቃየው የኦሮሞን ህዝብ ችግር እንዲያባራ ነው፡፡ እናም በዚያም ሆነ በዘያ ግፊት ተፈጥሮ ሰላም እንዲወርድ ነው፡፡ ህብረተሰቡም በእርቁ ሃሳብ አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው»

Karte Äthiopien AM

ለኦሮሚያ ግጭት የሰላም አማራጭ ጥሪ

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በስፋት የሚታየው አለመረጋጋትና ግጭት ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ የሚጠይቅ ደብዳቤ በውጭ አገራት በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጅ ማህበረሰብና ሲቪል ማህበራት ለመንግስት ተላከ፡፡ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና መንግሥት ሸኔ ሲል ለሚጠራው ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ዋና አዛዥ ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) በሚል የተላከው ይህ ግልጽ ደብዳቤው፤ ኦሮሚያ ውስጥ ለሚስተዋለው አለመረጋጋትና ሰብኣዊ ቀውስ እልባት እንዲሰጥ የሚጠይቅ ነው ፡፡ መቀመጫውን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው “ኦሮሞ ሌጋሲ፣ ሊደርሺፕ እና አድቮከሲ” የተባለው ድርጅት ከአውሮጳ እስከ አሜሪካ በምእራቡ ዓለም ያሉትን የኦሮሞ ማህበረሰብ የሚያሰባስብ ገለልተኛ ተቋም እንደሆነ ይገለጻል፡፡ በጎርጎራውያኑ 2016 ተጠርቶ በነበረው ታላቁ ሰላማዊ ሰልፍ መመስረቱ የተነገረው ይህ ድርጅት የኦሮሞ ማህበረሰብን በማሰባሰብ ከተለያዩ ሀገራትና የዓለማቀፍ ማህበረሰብ ጋርም በመስራት የኦሮሞ መብት ተጥሷል ተብሎ ሲታመን የሚሟገትም ነው ይባልለታል፡፡

ሰሞኑን ታዲያ ይህ ድርጅት ከሌሎች ሲቪል ማህበራት ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ መንግስት እና ኦሮሚያ ውስጥ ታጥቆ መንግስትን እየተዋጋ ላለው መንግስት “ሸነ” በሚል ለሚጠራው “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” በላከው ደብዳቤ፤ የሁከት አዙሪት ተጋርጦበታል ያለው የኦሮሞ ህዝብ እረፍት እንዲያገኝ መንግስት ከታጣቂዎች ጋር ለእርቅ እንዲቀመጥና ሰላማዊ እልባት እንዲሰጥ ይጠይቃል፡፡ ሴና ጅንጅሞ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ስለደብዳቤው በተለይም ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያም፤ “ትግራይ ውስጥ የሰላም ችግር ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ዓለም የሰጠችውን ትልቅ ትኩረት እንደው ግማሹን እንኳ ተቀብላ በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ችግር ማስጮህ አልቻለችም፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ህዝብ እየሞተ በብዙ መልኩ እየተቸገረ እንደሆነ እየታወቀ በቂ ምላሽ በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ሊሰጥ አልተቻለም፡፡ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል የሚሰራው የአፍሪካ ህብረትም ቢሆንም፤ በተለይም አሜሪካን ጨምሮ ሌላው ዓለምም ሄንኑን መርህ ስለሚቀበሉ ያ ድርጅት ለኦሮሚያው ችግር በቂ ትኩረት አልሰጠም፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም አማራጮች እድል ሰጥቶ በይፋ በሚናገርበት ባሁን ወቅት እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በግልጽ በሁሉም ማዕከሎቹ ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ከተናገረ ወዲህ አሁን ለመነጋገር ጥሩ አጋጣሚ ነው በሚል እኛ እና 20 የኦሮሞ ማህበረሰብ ሲቪል ድርጅቶች በጋራ ሆነን ነው ይህነ ደብዳቤ የጻፍነው፡፡ የዚህ ደብዳቤ ዋናው ትኩረት ሰላም እንዲወርድ ጥሪ ማቅረብ ነው፡፡ ይህ ለመንግስት የተጻፈው የመጀመሪያው ደብዳቤ ይሁን እንጂ አስቀድሞም ላለፉት ሶስት ዓመታት ግጭቱ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እልባት እንዲያገኝ ስንወተውት ነበር” ብለዋል፡፡

ፎt ከማኅደር፦ ጎጆ ቤቶች በኦሮሚያ ክልልምስል Fischer/Bildagentur-online/picture alliance

ደብዳቤው ሁሉም ወገን ጋ መድረሱን አረጋግጣችኋል ወይ፤ ምን ያህልስ ተደማጭነት እናገኛለን ብላችሁ ትገምታላችሁ የተባሉት ሴና ጅንጅሞ፤ “ደብዳቤው ደርሷል፡፡ በርግጥ ሁሉም ቢሮ ደርሷል ወይ የሚለውን አናውቅም፡፡ ኤምባሲ እና የተለያዩ የመንግስት አካላት ጋ እንደደረሰ ግን እናውቃለን፡፡ ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትም በከፍተኛው አማካሪው በኩል ደብዳቤው እንደደረሰው ሰምተናል፡፡ ሌላው የዚህ ደብዳቤ ዓላማ ታጥቀው መንግስትን የሚገዳደር የኦሮሞ ነጻነት ጦር ወይም መንግስትን ለመጥቀም አሊያም ለመወገን ሳይሆን በዚህም በዚያም አንዱ ሌላውን ደገፍክ እያለ የሚያሰቃየው ያው የኦሮሞን ህዝብ ችግር እንዲያባራ ነው፡፡ እናም ይህ ደብዳቤ በዚያም ሆነ በዘያ ግፊት ተፈጥሮ ሰላም እንዲወርድ ነው፡፡ በዚህ ላይ ህብረተሰቡም ጊዜው አሁን ነው በማለት በእርቁ ሃሳብ አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው” ብለዋል፡፡

ደብዳቤውን የጻፉት የማህበረሰብ አካላት ለድርድሩ ሀሳብ ከማቅረብ በዘለለ የማደራደርና የማቀራረብ ውጥኑ ምንያህል ነው፤ በሁሉም ወገንስ በኩል ምን ያህል ተቀባነት ይኖረኛል ብሎ ያምናል የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው፡ “አሁን ባለው ሁኔታ የተሻለው መፍትሄ የምንለው የአፍሪካ ህብረትም ጭምር ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ብሎ በሚሄድበት የትግራይ ችግርንም እልባት በሰጠበት አኳኋን ለዚህም እድል ቢሰጥ ጥሩ አጋጣሚ ነው እንላለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በተለይም ከአሜሪካ መንግስት በኩል ጫና እንዲኖር ግንኙነት አለን፡፡ ይህ እርቅ የሚወርድበት ጊዜ መሆኑንም ከደብዳቤውም በፊት ሆነ በኋላ አሳውቀናቸዋል፡፡ ካልሆነ እንኳ በመላው ዓለም ያለው የኦሮሞ ማህበረሰብ ለሰላም ግፊት እንዲያሳድሩ ነው የምንፈልገው፡፡ እኛ እንደተቋም የምንወግንለት አካል የለም፡፡ የወገንተኝነት አቋምም ኖሮን አያውቅም፡፡ ወገንተኝነታቸውን አንዱ ሌላውን ደገፍክ እያለው ለሚሰቃየው ለኦሮሞ ህዝብ ነው፡፡ በግጭትና በድርቅ እኮ 15 ሚሊየን ህዝብ ሰቆቃ ውስጥ ነው ያለው፡፡ በቦረና፣ ጉጂ፣ የባሌ ቆላማ አከባቢዎች፣ በምዕራብ እና መካከለኛ ኦሮሚያ ጭምር እየሆነ ያለውን አብረን የምናውቀው ነው፡፡ በድርቅና ግጭቱ በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ እኮ ተፈናቅሏል፡፡ በቅርቡ እንኳ በወጣው የተመድ ሪፖርት በጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ ካሉ ከ5 ሚሊየን በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛው ኦሮሚያ ውስጥ መሆኑን አንጠራጠርም፡፡ እናም መንግስትም ሆነ ሌላው አካል ገለልተኝነታችንን ስለሚረዱ የጻፍነው ደብዳቤ ለሰላም ግፊት ለማሳደር ሚና ይኖረዋል የሚል ተስፋ አለን፡፡”

ተጻፈ ስለተባለው የሰላም ድርድር ስለሚያጠይቀው ደብዳቤ በመንግስት በኩል የተባለ ነገር የለም፡፡ ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እና ለፌዴራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገለግሎት ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ስለዚህ የሚያውቁት ካለ ለመጠየቅ የኃላፊዎቹ የእጅ ስልክ ላይ ብንደውልም አልተሳልንም፡፡

ከዚህ በፊት ግን መንግስት ሸኔ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው በኦሮሚያ በስፋት የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሰላም ለመደራደር ዝግጁነቱን ቢገልጽም፤ በመንግስት በኩል ማዕከላዊ አመራር ከሌለው ቡድን ጋር ለድርድር መቀመጥ አስቸጋሪ ይሆናል የሚል አቋሙን በተደጋጋሚ አሳውቆ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW