ለግዕዝ ቋንቋ ፍቅር ያደረባቸው ወጣቶች
ዓርብ፣ ኅዳር 25 2013
የግዕዝ ቋንቋ ከቤተ ክርስትያናት ኃይማኖታዊ አገልግሎት ዉጪ በሌላዉ ኢትዮጵያዊ ዘንድ ብዙም አይታወቅም። ይሁንና ይህ ቋንቋ ከዛም በላይ እንደሆነ የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶቻችን ይናገራሉ።ራሄል ሰለሞን እና አቤል መኮንን ስራዬ ብለው እና ጊዜ ወስደው ከሌሎች የግዕዝ ቋንቋ መማር ከሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ጋር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ተሰባስበው ይማራሉ። አዲስ አበባ የሚኖረው አቤል ለቋንቋው ብዙም እንግዳ አይደለም።«ቤተክርስትያን ውስጥ ነው ያደኩት። ዲያቆን ነኝ፤ ስለዚህ ትምህርቱን የጀመርኩት ከታች ነው።ሰንበት ትምህርት ቤት ስንማር ግዕዝ እንደ አንድ ሳብጀክት ይሰጠናል። ከዛ ቲዮሎጂ ስማር ተምሬያለሁ።የበለጠ ግን ግዕዝን እንዳውቅ የረዳኝ ቅኔ ነው።» ይላል።
አቤል ቀድሞውንም መሠረት ያለውን እውቀቱን አሁን ይበልጥ ለማዳበር የተነሳሳበት ዋናው ምክንያት ግን ሌላ ነው።«በተለያዩ የውጭ ስመ ጥር ዩንቨርስቲዎች ግዕዝ እስከ PHD ደረጃ ይሰጣል እና ባለቤቷ ኢትዮጵያ ሆና ሳለ የውጪዎቹ እንደዚህ እስከ PHD ደረጃ ሲያስተምሩ እንዴት የራሳችንን ቋንቋ በሥነ ሥርዓት ማወቅ ያቅተናል የሚል ቁጭት አደረብኝ»
ወጣት ራሄልንም ቢሆን ግዕዝ ለመማር ያበረታታት ነገር የሀገር ሀብት የሆነውን ቋንቋ በሯሷ መረዳት መፈለጓ ነው። የ25 ዓመቷ ወጣት ኖርዌይ ሀገር ስትኖር 10 ዓመት አልፏታል። ከኖርቬጂኛ ባሻገር የምልዕክት ቋንቋም ተምራለች።« ግዕዝ የቤተክርስትያናችንም የሀገራችንም ቋንቋ ነው።እና በግዕዝ ስታነቢው የበለጠ ትርጉም ይሰጥሻል።ለሌሎች ባልተርፍ እንኳን ለራሴ ልወቀው ብዬ ነው የምማረው»
በቱሪዝም ዘርፍ አስጎብኚ ሆኖ የሚሰራው አቤል ይህንን ቋንቋም ለመማር በርካታ አማራጮች እንዳሉ ያስረዳል። ከዚህም መካከል ሁለቱም ወጣቶች አባል የሆኑበት የግዕዝ ፋሚሊ ወይም የግዕዝ ቤተሰብ የቴሌግራም ግሩፕ አንዱ አማራጩ ነው።« የሚያስተምሩን መምህር ደቡብ ኮርያ ነው ያሉት። እሳቸው ቴሌግራም ላይ ይህን ግሩፕ ከፍተው እዛ ላይ በየቀኑ ለአንድ ሰዓት ያህል ቻት እንድናደርግ ያደርጉናል። በሳምንት አንድ ጊዜ ደግሞ የግዕዝ ሰዋ ሰው ያስተምሩናል።» ከዚህም ሌላ ቋንቋውን መማር ለሚፈልጉ ሰዎች በቴሌቪዥን እና በአካል ተገኝተው የሚማሩበት በርካታ አማራጮች አሉ ይላል አቤል። ዋናው ነገር እሱ እንደሚለው ፍላጎቱ ነው። በዚህ ራሄልም ትስማማለች፤« አብረውን ከሚማሩ ልጆች የተረዳሁት ነገር አብዛኛው ሰው ፍላጎቱ እንዳለው ነው።» በተለይ ደግሞ ሴቶች ከፍተኛ ፍላጎት እንደሚያሳዩ ገልፃልናለች።
ግዕዝ መማር ከጀመረች ሁለት ዓመት የሆናት ራሄል እድሉን ካገኘች ከፍተኛ እስከተባለው የግዕዝ ደረጃ ድረስ የመማር ፍላጎት አላት። አሁን ግዕዝ የምትማርበት ግሩፕ ላይ 400 የሚጠጉ አባላት አሉ።አባላቱ የሚገኙትም የተለያዩ ሀገራት ነው። ስለሆነም የኦንላይ ትምህርቱ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረላቸው ይመስላል፤ ትምህርቱ የአብነት እና የቋንቋ ተብሎ ለሁለት የተከፈለ ነው።
እዛም ላይ « ርዕስ ተመርጦ በዛ ርዕስ ላይ ሙሉ በሙሉ እንወያያለን። ግድፈት ሊኖር ይችላል። ግን መምህራችን መኃላችን ስላሉ ያርሙናል።»ትላለች ራሄል።
ቴሌግራም ላይ ወጣቶቹን የሚያስተምሩት መምህር ነጋሲ ግደይ ይባላሉ። ደቡብ ኮርያ ውስጥ የቤተክርስትያን አገልጋይ ሲሆኑ በግዕዝ ቋንቋ አንድ ልብ ወለድ መጽሀፍ ፅፈዋል። ይህም መፅሐፍ አንዱ የተማሪዎቹ የግዕዝ መለማመጃ ነው። መምህራቸው እንደሚሉት ተማሪዎቹ ከፍተኛ መሻሻል አድርገዋል።« ከጀመርኩ ጀምሬ እስካሁን ድረስ ያለው ነገር ከጠበኩት በላይ ነው። ልጆቹ አሁን እስከ ማውራት ደርሰዋል። ትረካም ይሰራሩ፣ የተለያዩ ፁሁፎችም ይፅፋሉ። እና አራቱን የቋንቋ መሠረቶች ማለትም መናገር፣ ማዳመጥ ፣መፃፍ እና ማንበብ የሚባሉት ላይ በደብን በሚባል መልኩ ከፍተኛ ለውጥ አድርገዋል። » ይላሉ መምህራቸው።
ከልጅነቱ አንስቶ ግዕዝ የተማረው አቤል ምንም እንኳን የግዕዝ ፋሚሊ የቴሌግራም ግሩፕ ላይ ተማሪ ቢሆንም ያለውንም እውቀት ለሌሎች ለታናናሾቹ የሚያካፍልበት አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበር አጫውቶናል። « ያስተማርኩት አሜሪካን ሀገር ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፤ ከ 1 እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ናቸው። ለእነሱ የሁለት ወራት ያህል የግዕዝን ትምህርት አስተምሬያለሁ፤ ...ስለ ግዕዝ ታሪክ፤ ፊደላት፣ የግዕዝ ቁጥሮች በአጠቃላይ መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮችን አስተምራለሁ።»
የግዕዝ ቋንቋ ከአፍሪቃ ሀገራት የመጀመሪያው እና ብቸኛ የራሱን ፊደላት የያዘ ቋንቋ እንደሆነ ይነገርለታል። አቤል ቋንቋው ዘርፈ ብዙ እንደሆነ እና ሌሎች ወጣቶችም ሊማሩት የሚበረታታ እንደሆነ ያስረዳል። « የብዙዎች ችግር ግዕዝን የሀይማኖች ቋንቋ ብቻ አድርጎ የማየት ችግር ይመስለኛል። ነገር ግን መጠነ ሰፊ የሆነ ጥቅም አለው። ለምሳሌ ሥለ መልከዓ ምድር፣ ስለ መድኃኒት ቅመማ ፣ ስለ ሥነ ጥበብ፣ ስለ ታሪክ እና ብዙ ነገሮች ነው በውስጡ የያዘው። ይህንን ቋንቋ ሰው በሚገባ ባወቀው ቁጥር እነዚህን ሀገር በቀል እውቀቶች የሚመረምር ትውልድ ይመጣል።» ሲል ወጣቱን ያበረታታል።
ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ