1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩንቨርስቲ መምህራን ጥያቄ

ዓርብ፣ ኅዳር 30 2015

ከሰኞ ህዳር 26 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ዓርብ ኅዳር 30 ቀን ድረስ የሥራ ማቆም አድማ መተዉ የነበሩት መምህራን የፊታችን ሰኞ ወደ ሥራ እንደሚመለሱ ገለፁ።

የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ ለማካተት ወደ ለሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ስልክ ደውለን ስብሰባ ላይ እንደሆኑ እና ማናገር እንደማይችሉ ነግረውናል።ምስል Solomon Muchie/DW

የዩንቨርስቲ መምህራን ጉዳይ

This browser does not support the audio element.

ከሰኞ ኅዳር 26 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ዓርብ  ኅዳር 30 ቀን ድረስ  የሥራ ማቆም አድማ አድገው የነበሩት የዩንቨርስቲ መምህራን የፊታችን ሰኞ ወደ ሥራ እንደሚመለሱ ገለፁ። ዶቼ ቬሌ ያነጋገራቸው ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ አንድ የዩንቨርስቲ መምህር እንደተናገሩት፤ አድማዉን በተለያዩ ዩንቨርስቲ የሚያስተምሩ በርካታ መምህራን ትግላችንን ተቀላቅለው ነበር ብለዋል። «አድማው ዛሬ  አምስተኛ ቀኑ ነው ዛሬ የመጨረሻም ቀኑ ነው » ብለዋል ከ36 ዩንቨርስቲች በላይ የሚገኙ መምህራን በተለያዩ መልኩ አድማውን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል ።

 መምህራኑ አድማቸዉን ያቋረጡት፤ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ ይሆን ብለን ላቀረብንላቸዉ ጥያቄ  ሲመልሱ « እንኳን ጥያቄውን ለመመለስ ቀርቶ የሚመለከታቸው አከሎች መምህራንን   አላወያዩም በመግለጫም ይሁን በምንም መልክ መግለጫ አልሰጡም ባልሰማ ዝም ብለው ነው ያሉት » ብለዋል መምህራን ለተማሪው ለአገርም ስለምናስብ ወደስራ እንገባለን ነገር ግን ለ5 ቀን ያደረግነውን አድማ መንግሥት እንደማስጠንቀዊያ ወስዶት በሦስት ሳምንት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ የማይሰጥ ከሆነ ግን ከሦስት ሳምንት በኋላ ከዚህ ከፍ ባለ ትግል ስልት መርጠን ደግመን እንደምንጀምር ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠን ነው ያጠናቀቅነው ብለዋል።

 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን እና ቴክኒካል ረዳቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር በፍቃዱ ዘለቀ፤ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም የሥራ ማቆም አድማ የጠራው  የመምህራን ቡድን ኢንፎርማል ወይም እውቅና የሌለው ቡድን ነው ሲሉ ለዶቼ ቬሌ ተናግረው ነበር ። ዶክተር በፈቃዱ ለሚመለከተው  አካል ጥያቄያችንን አስገብተናል ሲሉ ተናግረዉም ነበር። ማህበሩ ላቀረበው ጥያቄ ምን ምላሽ አገኛችሁ ለማለት ለኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን እና ቴክኒካል ረዳቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ለዶክተር በፍቃዱ ዘለቀ በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልክ ባለማንሳታቸው ሀሳባቸውን ማካተት አልቻልንም።

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን እና ቴክኒካል ረዳቶች ማኅበር ኅዳር አጋማሽ ላይ ለትምህርት ሚኒስቴር ያስገባው 14 የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች፤ መካከል የደመወዝ ጭማሪ፣ የደረጃ ዕድገት፣ የቤት አበል  ክፍያ ፣በተጨማሪ ሥራዎች የሚገኝ ገቢ ላይ የግብር ቅነሳ የሚሉ ጥያቄዎችን ያካተተ ነው። አርባ ምንጭ ዩንቨርስቲ፤ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ፤ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ፤ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፤ ወልድያ ዩኒቨርሲቲ፤ እንዲሁም ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ትላንትና እና ዛሬ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ባሰራጩት መልዕክት ከዛሬ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም መምህራን ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲገቡ አሳስበዋል ።

የመምህራኑን አድማና ጥቃቄን ይዘን ወደ ሚመለከተው የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ ለማካተት ወደ ለሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ስልክ ደውለን ስብሰባ ላይ እንደሆኑ እና ማናገር እንደማይችሉ በመግለጻቸው ሃሳባቸውን ልናካትት አልቻልንም።

ማኅሌት ፋሲል 

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW