1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ለጦርነት በስፋት የዋሉት የሰው አልባ አውሮፕላኖች

ማክሰኞ፣ ሰኔ 28 2014

ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች በጦርነቶች በተለይም በአፍሪቃ አገሮች ውስጥ በሚካሂዱ ውጊያዎች አይነተኛ ለውጥ እየፈጠሩ መሆኑን በመስኩ ላይ የተደረገ ጥናት አመለከተ።

MQ-1C Gray Eagle Drohne
ምስል፦ Yonhap/picture alliance

ሰው አልባ አውሮፕላኖች

This browser does not support the audio element.

ፓክስ የተባለ የኔዘርላንድስ የሰላም ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ፤ ከዓመታት በፊት የተወሰኑ አገሮች ለቅኝትና ሌሎች ሰላማዊ አገልግሎቶች ያውሏቸው የነበሩት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለይ በአፍሪቃ ዋና የጦር መሣሪያዎች በመሆን የጦርነት ውሎዎችንና የዘመቻዎችን ውጤት እየለወጡት መሆኑን ገልጿል። በአሁኑ ወቅት ግብጽ ቱኒዚያ ሞሮኮና ናይጀሪያን ጨምሮ 30 በሚሆኑ የአፍሪካ አገሮች ወታደራዊ ድሮኖች በጥቅም ላይ ይውላሉ። ኢትዮጵያም ከቅርብ ግዜ ወዲህ የወታደራዊ ድሮኖች ባለቤት እንደሆነች ይታወቃል። ባለፉት ወራት በስሜን የአገሪቱ ከፍል ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀት ጋር በተካሂደው ጦርነትም ወሳኝ ሚና የነበራቸው መሆኑን ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖችና ሌሎች አካላትም ጭምር ገልጸዋዋል። 

ወታደራዊ ድሮኖች ከሌሎቹ የጦር መሣሪያዎች የሚለዩበትንና አውደ ውጊያዎችን የሚለውጡበትን ሁኔታ ሚስተር ዊም ዝዌኔንበርግ የኔዘርላድሱ የሰላም ድርጅት ፓክስ የድሮን ተመራማሪ ለዶቼ ቬለ (DW)ዲደብሊው ሲያስረዱ፤ «||ወታደራዊ ድሮኖች ከ24-26 ሰአታት በአየር ላይ ሊቆዩ የሚችሉ፤ ካሜራ የተገጠመላቸው፤ በሌሊት ጭምር ሊያጠቁና ኢላማቸውን በትክክክል የሚመቱ ናቸው» ብለዋል። አክለውም ወታደራዊ ድሮኖች በአንጻራዊነት እርካሽ መሆናቸውና ከየትኛውም ቦታ በቀላሉ ሊነሱና ሊያጠቁ መቻላቸው በተለይ በአፍሪካ ተመራጭ እንዳደርጋቸው፤ በአሁኑ ወቅትም በአብዛኛዎቹ የአፍሪቃ አገሮች በጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆነ አስረድተዋል። አሜሪካ በሶማሊያ አልሸባብን ለመምታት እንደምጠቀምበት ሁሉ ፈረንሳይም በማሊ አማጺያን የምትላቸውን ቡድኖች ስታጠቃበት ቆይታለች።  የመንግሥታቱ ድርጅትም በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ድሮንን እንደሚጠቀምና፤ ከሁሉም በላይ ግን በመንግሥት አልባዋ ሊቢያ የሚገኙ ልዩ ልዩ ተፋላሚ ወገኖች ድሮንን አብዝተው እንደሚጠቀሙና መሳሪያዎቹን የሚያገኙትም ከምዕራባውያንና የአረብ መንግሥታት ደጋፊዎቻቸው እንደሆነ ሚስተር ዊም አክለው ገልጸዋል። ስለመሣሪያዎቹ አጠቃቀምና የትና እንዴት በሥራ ላይ መዋል እንዳለባቸው የሚደንግጉ ሕጎች አለመኖራቸው፤ ድሮንን በሚመለክት በአሁኑ ወቅት የሚነሱ አሳሳቢ አጀንዳዎች ናቸው። ድሮኖች ቲክኖሎጂያቸው ቀላልና ዋጋቸውም እርካሽ መሆኑ፤ በሁሉም እጅ በቀላሉ እንዲገቡ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ስጋትም በሰፊው ይነገር ይዟል። የኔዘርላንድሱ ፓክስ የሰላም ድርጅትና ሌሎች የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎችም ይህንኑ ስጋት በሰፊው በማስተጋባ፤ መሣሪያዎቹ በስፋት እንዳይሰራጩና አጠቃቀማቸውም ሕግና ስርዓት እንዲኖረው እያሳሰቡ ነው። ሚስተር ዊም ወታደራዊ ድሮኖችን በሚመለክት በአሁኑ ወቅት አሳሳቢዎች ናቸው ያሉዋቸውን ሲያስረዱም፤«“ የሚያሳሥበው ጉዳይ ድሮኖች በቀላሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እጅ ውስጥም ሊገቡ የመቻላቸው ሁኔታና የደህንነት ስጋት መፍጠራቸው ነው። አጠቃቃማቸውን በሚመለክት የሕግ ማዕቀፍ፤ ግልጽነትና ተጠያቂነት አለመኖሩም ሌላው ችግር ነው።» በማለት የወታደራዊ ድሮኖች ባለቤትነትና ስምሪት ጉዳይ ሚስጢር ሆኖ መቆየቱንና ይህም ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል ። በአንጻሩ ኢትዮጵያ በቅርቡ ባሳየችው የአየር ኃይል ወታደራዊ ትዕይንት ላይ የድሮን አቅሟን ማሳየቷ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን ሊያግዝ ይችላል ሲሉም በመገናኛ ብዙሀን በአወንታዊ ጠቅሰውታል። ድሮኖች ወታደራዊ ኢላማቸውን በትክክክል የሚመቱ ናቸው ይባል እንጂ  በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚድርሱት ጥቃትና የሚያስከትሉት ጉዳትም ብዙ መሆኑን  የሚናገሩት ሚስተር ዊም፤ በማንኛውም የድሮን መሣሪያም ይሁን በሌላ፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና የሚደርሱ ጉዳቶች፤ ገለልተኛ ምርመራ ሊደረግባቸውና ጥቃቱን በፈጸሙ ቡድኖች ላይም እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ በመግለጽ መንግሥታት ሊያደርጓቸው ይገባል ያሉቸውን ዘርዝረዋል፤  

ምስል፦ Muhammed Enes Yildirim/AA/picture alliance
ምስል፦ IDF/AFP

«መንግሥታት መሣሪያዎቹን ሲጠቀሙ ዓለም አቀፍ ሕግን አክብረው መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። የመሣሪያዎቹን አጠቃቀምና ስምሪት በሚመለከት ዝርዝር ማብራሪያ በመስጠት ግልጽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ጥቃቶች ሲፈጸሙ ምርመራ ማካሄድና አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል፤  እንዲሁም መንግሥታት በድሮኖች ግብይትና ስርጭት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርባቸዋል።» በማለት የወታደራዊ ድሮኖችን አጠቃቀምና ወታደራዊ ስነምግባር በሚመለክት ወጥ የሆነና አስገዳጅ የሕግ ማዕቀፍ ሊዘጋጅ እንደሚገባው የኔዘርላንድሱ ፓክስ የሰላም ድርጅት ተመራማሪ ሚስተር ዊም ዝዌይኔንበርግ አሳስበዋል።  

ገበያው ንጉሤ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW