1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለፀጥታ ችግር፤ ሙስና እና የኑሮ ውድነት መንግሥት መፍትሄ እንዲፈልግ መጠየቁ

ማክሰኞ፣ የካቲት 12 2016

እየተባባሰ ለመጣው የሙስና ፣ የኑሮ ውድነት እና የፀጥታ ችግር መንግሥት መፍትሄ እንዲፈልግ በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎች ጠየቁ ፡፡ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት በበኩላቸው መንግሥት ነዎሪዎቹ ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመሥጠት እንደሚሠራ ተናግረዋል ፡፡

በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎች መንግሥት መፍትሄ እንዲፈልግ ጠየቁ
በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎች መንግሥት መፍትሄ እንዲፈልግ ጠየቁምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎች መንግሥት ለፀጥታ ችግር መፍትሄ እንዲፈልግ ጠየቁ

This browser does not support the audio element.

እየተባባሰ ለመጣው የሙስና ፣ የኑሮ ውድነት እና የፀጥታ ችግር መንግሥት መፍትሄ እንዲፈልግ በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎች ጠየቁ ፡፡ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት በበኩላቸው መንግሥት ነዎሪዎቹ ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመሥጠት እንደሚሠራ ተናግረዋል ፡፡

የመንግሥት ባለሥልጣናት በህዝቡ የሚነሱ ጉዳዮችን ማዳመጣቸው በጎ ጅምር መሆኑን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት አንድ የፌዴራሊዝምና የህዝብ አስተደዳር መምህርና ተመራማሪ “ ነገር ግን ለጥቄዎቹ ተገቢውን ምላሽ ሊሠጥ ይገባል “ ብለዋል ፡፡

ህዝቡ በመድረኮቹ ምን ጠየቀ ?

የፌዴራል መንግሥት ከቀናት በፊት በአማራ ክልል የጀመረውን ሕዝባዊ የውይይት መድረክ  አሁን ላይ በሌሎች ክልሎችም እያካሄደ ይገኛል ፡፡ በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በተካሄዱ የውይይት መድረኮች ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች አሉብን ያሏቸውን ችግሮች ለባለሥልጣናቱ ነግረዋቸዋል  ፡፡ በተለይም እየተባባሰ መጥተዋል ያሏቸውን ሙስና ፣ የኑሮ ውድነት እና የፀጥታ ችግሮች መንግሥት መፍትሄ ሊፈልግ እንደሚገባ  በሀዋሳ እና በሚዛን ቴፒ  ከተሞች የሚገኙ ተሳታፊ ነዋሪዎች ጠቅሰዋል  ፡፡

አሳሳቢ የተባሉት ችግሮች  

በሀዋሳ እና በሚዛን ቴፒ በተካሄዱት የውይይት መድረኮች ነዋሪዎች መንግሥት ሊፈታቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች አንሰተዋል ፡፡ “ ሌብነት ፣ ሙስና እና ሀብትን አለአግባብ መጠቀም እየተባባሰ መጥቷል “ ያሉት አንድ የሚዛን ቴፒ ተሳታፊ “ እነዚህ ነገሮች እንደ ሥረዓት የበላይነት አሊያዙም ወይ ?  ይህን አንዴት ነው ያያችሁት ?  “ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

“ አሁን ያለውየኑሮ ውድነት  በጣም ከብዷል “ ያሉት ሌላው ተሳታፊ “ መንግሥት ቢያንስ በልተን የምናድርበትን ሁኔታ ያመቻችልን “ ሲሉ ጠይቀዋል ፡፡ በሀዋሳው መድረክ ተሳታፊ የሆኑ አንድ እናት ደግሞ የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ጠቅሰው መንግሥት በመላው ኢትዮጵያ ሠላም እንዲያሰፍን በእናቶች ሥም አደራ እላለሁ ብለዋል ፡፡

በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎች መንግሥት መፍትሄ እንዲፈልግ ጠየቁምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ጉቦ

የሚዛን ቴፒን የውይይት መድረክ የመሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተሳታፊዎቹ በሙስና ዙሪያያነሱትን ጥያቄ “ አስከፊ “ በማለት ነው የገለጹት ፡፡ በየአካባቢው የመልካም አስተዳደር እጦት እና ሌብነት ይስተዋላል ያሉት አቶ ጥላሁን “ አመራሩ የራሱን ህዝብ የእጅ መንሻ ጉቦ እየጠየቀ ህዝብን እያጉላላ ያለበት ሁኔታ “ በጣም አስከፊ ነው “ ፡፡ ድርጊቱን መንግሥታችንም ሆነ ፓርቲያችን ብልፅግና ቀይ መስመር ብሎ ነው ያስቀመጠው ፡፡ ይህን በጋራ ታግለን ልናስተካክል  ይገባል “ ብለዋል ፡፡  

የሰላም ጉዳይ

በሀዋሳው የውይይት መድረክ ላይ ለተነሱት የኑሮ ውድነት ጥያቄዎች የገንዝብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ የምርት መጠን መጨመርና ከውጭ የሚገቡ የምግብ ሸቀጦችን ከቀረጥ ነጻ ማድረግን ጨምሮ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ የጠቀሱት ሚንስትሩ “ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮችን በተመለከተም የፌዴራል መንግሥት በአንዳንድ ክልሎች የሚታየውን የፀጥታ ችግር በውይይት ለመፍታት ዝግጁ ነው ፡፡ ነገር ግን አንደ መንግሥት የህግ የበላይነት የማስከበር ሃላፊነት አለብን ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ችግሮችን በሰላማዊ መልኩ የመፍታት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ፡፡ መንግሥት ለዚህ ዝግጁ መሆኑን የሲዳማ ህዝብ እንዲረዳን እንፈልጋልን “ ብለዋል ፡፡

የውይይት መድረኮቹ  ፋይዳ

በኢትዮጵያ የተካሄደውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ መንግሥት በበርካታ ተግዳሮቶች የተሞላ ነው ፡፡ ግጭት ፣ መፈናቀል ፣ ረሀብ እና የኑሮ ውድነት ዜጎች ከሚማረሩባቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ፡፡ ዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና የአካባቢ አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ አቶ አንዱዓለም ግርማ  “ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከህዝብ የሚነሱ ጉዳዮችን ማዳመጣቸው  በጎ ጅምር ነው “ ይላሉ ፡፡

አቶ አህመድ ሺዴ፤ የገንዝብ ሚኒስትርምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

መድረኩ የህዝብ ማስተንፈሻ አይነት ሳይሆን ከልብ መፍትሄ ለመፈለግ ከሆነ የሚደገፍ መሆኑን የተናገሩት አቶ አንዱዓለም “ ዋናው ነገር የችግሩን ምንጭ መለየት ነው ፡፡ አሁን ላይ ተጠያቂነት አይስተዋልም ፤ የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ አይታይም ፤ ያጠፉ የመንግሥት አመራሮች ሲጠየቁ አይታይም ፡፡ እርምት አይወሰድም ፡፡ በመሆኑም መንግሥት በሥሩ ያሉ ባለሥልጣናትን እና ተቋማትን መፈተሸ ይኖርበታል ፡፡ ህዝቡ ላነሳቸው ጥያቄዎችም ተገቢውን ምላሽ በጊዜ መስጠት ይጠበቅበታል “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW