1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ለፍልስጤም የመንግስትነት እውቅና የሰጡ ሀገራት የመበራከታቸው ፋይዳና የአውሮጳ ሀገራት አቋም

ኂሩት መለሰ
ማክሰኞ፣ መስከረም 13 2018

የአውሮጳ ኅብረትና የቡድን ሰባት አባላት ጀርመንና ጣልያን በፍልስጤም ጉዳይ በሁለት መንግሥታት መፍትሔ ይስማማሉ። ሆኖም ሁለቱ ሀገራት ለፍልስጤም የመንግሥትነት እውቅና የምንሰጠው ከእሥራኤል ጋር ከሚደረስ አጠቃላይ የሰላም ስምምነት በኋላ ነው በሚለው አቋማቸው እንደጸኑ ነው። ጀርመን በቅርብ ጊዜ ውስጥ እውቅና የመስጠት እቅድ የላትም።

በጎርጎሮሳዊው መስከረም 22 ቀን 2025 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተካሄደው በእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ ላይ የተነጋገረው ጉባኤ
በጎርጎሮሳዊው መስከረም 22 ቀን 2025 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተካሄደው በእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ ላይ የተነጋገረው ጉባኤምስል፦ BPMI Setpres/Laily Rachev

ለፍልስጤም የመንግስትነት እውቅና የሰጡ ሀገራት የመበራከታቸው ፋይዳና የአውሮጳ ሀገራት የተለያየ አቋም

This browser does not support the audio element.

እሥራኤል የጋዛ ከተማን ከምድር የማጥቃቱን ዘመቻ አጠናክራ በቀጠለችበት በአሁኑ ጊዜ ለፍልስጤም የመንግሥትነት  እውቅና የሰጡ ሀገራትቁጥር ከፍ ብሏል። በተመድ 80ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ዋዜማ ከ193ቱ የተመድ አባል ሀገራት ለፍልስጤም እውቅና የሰጡት ቁጥር 157 ደርሷል። ከመካከላቸው ከ27ቱ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት 15ቱ ይገኙበታል።

የአውሮፓ ኅብረት እና የፍልስጤም ነጻ አውጭ ድርጅት በምህጻሩ PLO ግንኙነት የዩሮ -አረብ ውይይት አንድ አካል ሆኖ 50 ዓመታት አስቆጥሯል። የአውሮጳ ኅብረት ለፍልስጤማውያን አስተዳደር ከፍተኛ የውጭ እርዳታ ለጋሽ ነው።

ከኅብረቱ አባላት ለፍልስጤም እውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገር ስዊድን ናት፤ ይኽውም በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓም ነበር። ቆጵሮስ እና ሌሎች የማዕከላዊ አውሮጳ ሀገራት የኅብረቱ አባል ከመሆናቸው በፊት በምስራቁ ጎራ የያኔዋ ሶቭየት ኅብረት አጋር በነበሩበት ጊዜ ነው ለፍልስጤም እውቅና የሰጡት። ይሁንና ከመካከላቸው በተለይ ቼክ ሪፐብሊክና ሀንጋሪ አሁን የእሥራኤል የቅርብ አጋሮች ሆነዋል።  

ኖርዌይ አየርላንድ እና ስፔይን በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 2024 ዓም ስሎቬንያ ፣ በሰኔ 2024  ፣  ከ80ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ አስቀድሞ ትናንት በኒውዮርክ፣ ፈረንሳይና ሳዑዲ አረብያ በሊቀመንበርነት በመሩት ለፍልስጤም ድጋፍ በተካሄደ ጉባኤ ፍጻሜ ላይም ፈረንሳይ ፣ቤልጅየም፣ ሉክስምበርግ ማልታ እና ሞናኮ ለፍልስጤም የመንግስትነት እውቅና መስጠታቸውን አረጋግጠዋል። ብሪታንያ ካናዳ አውስትሬሊያና ፖርቱጋል ደግሞ ባለፈው እሁድ  እውቅና የሰጡ ሀገራት ናቸው።

የፍልስጤም መንግሥት ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ በፍልስጤም ጉዳይ ለተነጋገገረው ዓለም አቀፍ ጉባኤ በቪድዮ ንግግር ሲያደርጉ ምስል፦ Celal Gunes/Anadolu/picture alliance

ይሁንና የቡድን ሰባትም አባል የሆኑትጀርመንና ኢጣልያ ግን እስካሁን እውቅና አልሰጡም። በእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይበሁለት መንግሥታት መፍትሔ የሚስማሙት ጀርመንና ጣሊያን ለፍልስጤም መንግሥት እውቅና የምንሰጠው ከእሥራኤል ጋር ከሚደረስ አጠቃላይ የሰላም ስምምነት በኋላ ነው በሚለው አቋማቸው እንደጸኑ ነው ።ጀርመን በይፋ እንደተናገረችው በቅርብ ጊዜ ውስጥ እውቅና የመስጠት እቅድ የላትም። በዚህ ጉዳይ ላይ ስለ ጀርመን አቋም የተጠየቁት የጀርመን መራኄ መንግስት ፍሪድሪሽ ሜርስ ፣ በአሁኑ ጊዜ  እውቅና ለመስጠት የሚያስፈልጉት ቅድመ ሁኔታዎች አልተሟሉም ሲሉ  በቅርቡ ተናግረዋል።

«በአሁኑ ጊዜ ለጀርመን መንግስት፣ ለፍልስጤም እንደ መንግሥት እውቅና መስጠት ለውይይት የቀረበ ጉዳይ አይደለም። ይህን ዓይነቱን እውቅና ወደ ሁለት መንግሥታት መፍትሔ በሚወስደው መንገድ ከመጨረሻዎቹ እርምጃዎች አንዱ  እንጂ የመጀመሪያው አድርገን አናየውም። »

ተችዎች ፣ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ያሉትን ይህን ቅድመ ሁኔታ ብቻ የጀርመን ፌደራል መንግሥት እውቅና የመስጠት ውሳኔ ላይ ላለመድረስ እየተጠቀመበት ነው ብለው እንደሚያምኑ የዶቼቬለው ክርስቶፍ ሀስልባህ ዘግቧል።

የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ የሙኒኩ የአይሁዶች ሙክራብ እድሳት ከተጠናቀቀ በኋላ በመስከረም ወር በተዘጋጀው ክብረ በዓል ላይ ንግግር ሲያደርጉምስል፦ Angelika Warmuth/REUTERS

በ80ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ጀርመንን ወክለው የሚሳተፉት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርዮሃን ቫደፉልም እንደ ሜርስ ሁሉ ጀርመን አሁን ለፍልስጤም እውቅና እንደማትሰጥ ጠቁመዋል። ሆኖም መንግስታቸው የማይቀበላቸው የእስራኤል እርምጃዎች እንዳሉ ከመናገር አልተቆጠቡም።

«መፍትሄ የሚሹ ሁለት አስቸኳይ ጉዳዮችን እየተወያየን ነው። በመጀመሪያ ደረጃ በጋዛ ሰርጥ ላይ ስላለው አስከፊ የሰብአዊ ሁኔታ። በጀርመን መንግስት ስም የእስራኤል መንግስት የጋዛ ከተማን ለመያዝ የወሰደው ውሳኔ ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ መንገድ መሆኑን ደግሜ መናገር እችላለሁ። ለጋዛ ሰርጥ ህዝብ አንድ ነገር ወደ ሚደረግበት እና ሰብአዊ ሁኔታዎች እንደገና ወደ ሚሻሻሉበት ሁኔታ እንዲመለሱ የድርድር እድል እንደገና እንዲኖር አስቸኳይ ጥሪ እናቀርባለን። በሌላ በኩል የጋዛን ግጭት ለመፍታት ፣ በአጠቃላይ ይህንን ግጭት ለመፍታት ድርድር ላይ ማተኮር አለብን። የጀርመን አቋም በጣም ግልጽ ነው፤ ግባችን የፍልስጤም መንግሥት ነው። የሁለት መንግሥታት መፍትሄን እንደግፋለን ሌላ መንገድ የለም። »

የዶቼቬለ የብራሰልስ ዘጋቢ ገበያው ንጉሴ ጀርመን በእስራኤልና በፍልስጤማውያን ጉዳይ ላይ የያዘችውን አቋም ቁጥብነት ሲል ገልጾታል። ለዚህም ምክንያት አላት ብሏል።  ገበያው እንደሚለው የጀርመን ቁጥብነት  የአውሮጳ ኅብረት በእስራኤል ለመውሰድ ባሰባቸው እርምጃዎች ላይ ተጽእኖ አሳድሯል ፤ ወይም እርምጃዎቹን እያጓተተ ነው።

ጀርመን አሁን በፍልስጤምና እስራኤል ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች። በናዚ ጀርመን አገዛዝ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አይሁዶች በመጨፍጨፋቸው ምክንያት ጀርመን ለእሥራኤል ደኅንነት ልዩ ሃላፊነት ወስዳለች። ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ከቀሩት የሀማስ ጥቃት በኋላ ፀረ-ሴማዊነት በጀርመን መስፋፋቱ እንደሚያሳፍራቸው በቅርቡ የተናገሩት ሜርስ በጀርመን የሚካሄደውን ማንኛውንም ፀረ- ሴማዊነት ለመዋጋት ቃል ገብተዋል። ሆኖም ሜርስ በፀረ ሴማዊነት ላይ የሚካሄደውን ትግልና የእስራኤልን ፖሊሲ በተለይም በጋዛ ሰርጥ የእስራኤል ጦር የሚወስዳቸውን ወታደራዊ እርምጃዎች የሚገመግሙበት መንገድ የተለያየ ነው።

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሀን ቫደፉል ስለፍልስጤም ጉዳይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉምስል፦ Yuki Iwamura/AP Photo/picture alliance

እሥራኤል በጋዛ የምትወስዳቸውን እርምጃዎች የተቹት ሜርስ በሰበቡም በጋዛው ጦርነት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ የተባሉ የጦር መሣሪያዎችን ሀገራቸው ለእስራኤል እንዳትሸጥ አስቁመዋል። ይሁንና  የፌደራል መንግስቱ በእስራኤል ላይ ጠንከር ያለ አቋም እዲይዝ ጫናው እየበረታባቸው ነው።

በዚህ ረገድ የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ካያ ካላስ  የአውሮፓ ኅብረት በእስራኤል ላይ በሚጥለው ማዕቀብ ጀርመን እንድትሳተፍ ጠይቀዋል። የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ደግሞ የአውሮፓ ህብረት ከእስራኤል ጋር የነበረው ልዩ የንግድ እድል እንዲታገድ ሀሳብ አቅርበዋል ።በሀገር ውስጥም ፖለቲካዊ ጫናዎች እየበረቱ ነው። ተቃዋሚው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ የሜርስ መንግስት ለእሥራኤልና ለፍልስጤማውያን ሰላም ከሚቆሙት ጋር አብሮ ይሆናል ? ወይስ በጋዛ ጥቃቱን አጠናክሮ ከቀጠለው ከቀኝ አክራሪው የእስራኤል መንግስት ጋር? ሲል ጠይቆ  በጉዳዩ ላይ ሜርስ ቁርጥ ያለ አቋም እንዲይዙ ግፊት እያደረገ ነው።በርካታ የሲቪል ማኅበራትም ሜርስ በእስራኤል ላይ የሚያቀርቡትን ትችት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተምጽነዋል።

መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. እስራኤል አሜሪካን ጀርመንና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት አሸባሪ የሚሉት ሀማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመና ሰዎችን ካገተ በኋላ ፣ እሥራኤል ጦርም በጋዛ ሰርጥ በአጸፋው እስካሁንም የቀጠለ ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተ ወዲህ እሥራኤልና ፍልስጤም የየራሳቸው መንግሥት እንዲኖራቸው የቀረበው የሁለት መንግሥታት መፍትሔ እንደተዳፈነ ነው።  

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁምስል፦ Abir Sultan/AP Photo/picture alliance

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አብዛኛዎቹ ምዕራባውያን ሀገራት ፍልስጤም በተመለከተ የሚወስዷቸው እርምጃዎች የፖሊሲ ለውጥ የማድረጋቸው ምልክት ተድርጎ እየተወሰደ ነው። ይህ ደግሞ የእሥራኤል ባለሥልጣናትን አስቆጥቷል ። ለፍልስጤም የመንግሥት እውቅና መሰጠቱ ሀማስን መሸለም ነው የሚሉት አሜሪካንና እሥራኤል እርምጃዎቹን አጥበቀው እየተቃሙ ነው። በነርሱ አስተያየት እውቅናው የጋዛውን ጦርነት የማስቆምና ታጋቾችን የማስለቀቅን ስምምነት ላይ መድረስን ከባድ ያደርጋል።

ትናንት ፈረንሳይና ሳዑዲ አረብያ የመሩት ጉባኤና ለፍልስጤም የተሰጠው እውቅና መስፋፋት በፍልስጤም ፣በመሬት ላይ ባለው ሁኔታ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ያን ያህል እንዳልሆነ ነው የሚነገረው። እስራኤል የጋዛውን ጥቃትና በኃይል በያዘችው በዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ የምታካሂደውን ሰፈራም አጠናክራ ቀጥላለች። የጉባኤው ውጤት በብዙዎች ዘንድ የፍልስጤማውያንን ሞራል ከፍ ቢያደርግ እንጂ በመሬት ላይ ግን ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም። ከሀማስ ሚሊሽያዎች ጋር ውጊያ ላይ ያለው እጅግ ቀኝ አክራሪ የሚባለውየእሥራኤል መንግስት በእስራኤል ታሪክ የፍልስጤማውያን መንግስት አይኖርም ሲል አስታውቋል። ይሁንና በገበያው አስተያየት ለፍልስጤም መንግሥትነት እውቅና የሰጡት አገራት ቁጥር መጨመር ለፍልስጤም ትልቅ ፋይዳ አለው። ይኽውም በእስራኤልና በአሜሪካን ላይ ጫናውን በማጠናከር እስራኤል የፍልስጤምን መንግሥትንነት እንድተቀበል የሚያስገድድና ማዕቀብ የሚጣልባት እርምጃ እንዲወሰድ ሊያደርግ ይችላል ብሏል።

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW