1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሊቢያ የተመድ ማዕቀብና ጋዳፊ

ሰኞ፣ የካቲት 21 2003

በሊቢያ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ ዓመፅ ዛሬም አልበረደም። የጋዳፊን መሰናበት የሚጠይቁት ተቃዋሚዎች ከዋና ከተማ ትሪፓሊ 50ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚትገኘዉን አል ዛዉያ ከተማን በሳምንቱ ማለቂያ ይዘዋል።

ተቃዋሚዉ በተቃጠ ታንክ ላይምስል AP

የተመድ ላለፉት 41ዓመታት ሊቢያን በገዙት ሙአመር ኤል ጋዳፊና የቅርብ አጋሮቻቸዉ ላይ ማዕቀብ ጥሏል። መንግስታቸዉ በሊቢያ ሕዝብ ላይ ሰሞኑን የፈፀመዉ ጥቃትና ያስከተለዉ ጉዳትም በዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት እንዲታይ መርቷል። ጋዳፊ ግን ዛሬም እሳቸዉ ጥቂት የሚሏቸዉን ተቃዋሚዎቻቸዉን ደምስሰዉ በስልጣን ለመክረም ጥረት ቀጥለዋል።

ሊቢያ በሕዝባዊዉ አብዮት መናጥ ከጀመረች ነገ ሁለተኛ ሳምንቷን ትደፍናለች። ባለፉት ቀናት በጋዳፊ ትዕዛዝ ደጋፊዎቻቸዉ በገዛ ሕዝባቸዉ ላይ የሰነዘሩት ጥቃት እንደዓለም ዓቀፍ ተቋማት ግምት ወደአንድ ሺ ህይወትን ቀጥፏል። የሌሎች አገራት ዜጎችን ጨምሮም ወደአንድ መቶ ሺዎችን ከሊቢያ አሰድዷል። ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ በተደጋጋሚ የጋዳፊ ደጋፊዎች ከጥቃት ርምጃቸዉ እንዲታቀቡ ቢያሳስብም ለ41ዓመታት ሊቢያን የገዙትና አብዮታዊ መሪ መሆናቸዉን የሚያዉጁት ጋዳፊም ሆኑ አጋሮቻቸዉ ከድርጊታቸዉ አልታገሱም። እንደዉም የጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል ኢስላም ከአባቱ መንግስት ቁጥጥር ቁጭ በሆነዉ በሌላዉ አካባቢ የሚኖረዉን ዜጋ ቁጥር ከትሪፖሊ ጋ በማነፃፀር ብዙሃኑ የጋዳፊ ደጋፊ እንደሆነ ለማስረዳት እየሞከረ ነዉ፤

«ኃይል አልተጠቀምንም። አሁንም በዙሪያችን ሰዎች አሉ። ያለነዉ ትሪፖሊ ነዉ፤ እዚህ ደግሞ ከሊቢያ ሕዝብ ግማሽ የሚሆነዉ ይኖራል፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ፤ የከተማዋ ኗሪ 2,5 ሚሊዮን ይሆናል። ለመሆኑ አስር ሺ ወይም አምስት ሺ ሕዝብ፤ ያዉም ከሞላ ማለት ነዉ፤ አባቴን ቢቃወም ወይም የፈለገዉን ቢል መላዉ የሊቢያ ሕዝብ ሚስተር ጋዳፊን ተቃወመ ማለት ነዉ?»

የጋዳፊ ልጅ ይህን ቢልም በመንግስት ዳጋፊዎችና በተቃዋሚዎች መካከል በተለያዩ ከተሞች ዉጊያ እየተካሄደ እንደሚገኝ ዘገባዎች ያመለክታሉ። ሮይተርስ እንደሚለዉ ከትሪፖሊ በስተምስራቅ 200ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኝ ሚስራታ በተባለች ከተማ የጋዳፊ ታማኞች በአዉሮፕላን ጥቃት ለማድረስ ሲሞክሩ አዉሮፕላኗ ተመትታ ወድቃለች።

ሳይፍ አል ኢስላም ጋዳፊምስል AP

በምዕራብ በኩል በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለችዉ አል ዛዊያ ከተማ ትናንት በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር ስትገባ፤ በአዉሮፕላን ጥቃት ቢሞከር መተላለቅ ይከተላል ሲሉ የከተማዋ ኗሪዎች አሳስበዋል። እንደዜና ዘገባዎች ከሆነም የጦር መሣሪያ በከተማዋ ኗሪዎች እጅም ገብቷል። ሕዝባዊዉ አመፅ ከተቀጣጠለበት ዕለት አንስቶ ሁኔታዉ መባባሱን ያስተዋለዉ ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ የጋዳፊ አገዛዝ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያከትም ጠይቋል። ከሊቢያ ጋ የቅርብ ግንኙነት ያላት ጣሊያን፤ የትብብርና አጋርነት ዉሏ ለጊዜዉ መቋረጡን አመልክታለች። ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ በምስራቅ ሊቢያ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ቡድኖችን ለመርዳት ዝግጁ መሆኗን አሳዉቃለች። የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት በጋዳፊና ተባባሪዎቻቸዉ ላይ ማዕቀብ ጥሏል። 15 አባላት ያሉት ምክር ቤት ቅዳሜ ዕለት ባካሄደዉ ልዩ ጉባኤ በሊቢያ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፤ በከፍተኛ ባለስልጣኖች ላይ የጉዞ እገዳ፤ እንዲሁም በዉጭ አገር የሚገኘዉ የጋዳፊ ቤተሰቦች ሃብት እንዳይንቀሳቀስ ወስኗል። ብሪታንያ በበኩሏ የጋዳፊና የቅርብ ተባባሪዎቻቸዉን ሃብት ማገዷን አስታዉቃለች። በተጨማሪም የፀጥታዉ ምክር ቤት በሊቢያ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመዉን ጥቃት ዓለም ዓቀፍ የወንጀል ችሎት እንዲመረምር አስተላልፏል። በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካን አምባሰደር ሱዛን ራይስ ዉሳኔዉ የጋዳፊ መንግስት መግደል እንዲያቆም ግልፅ ማስጠንቀቂያ እንደሆነ አመልክተዋል፤

«የፀጥታዉ ምክር ቤት በጋራ ጥቃቱን አዉግዟል፤ ተጠያቂነት እንዲኖር ግፊት አድርጓል፤ እንዲሁም በሰራዉ መጥፎ ድርጊት የማይፀፀተዉ የሊቢያ አመራር ቡድን ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ አሳልፏል። ይህ የሊቢያ መንግስት መግደል ማቆም እንደሚኖርበት ግልፅ ማስጠንቀቂያ ነዉ።»

በሊቢያዉ ሙአመር ጋዳፊና ተባባሪዎቻቸዉ ላይ ጫና እንዲደረግ አበክራ ስትወተዉት የቆየችዉ የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬለ ማዕቀቡ የገዛ ሕዝቡ ላይ ጥቃት የከፈተዉን አምባገነን ቡድን እንጂ የሊቢያን ሕዝብ እንደማይጎዳ በመጠቆም የአዉሮፓ ኅብረትም ተመሳሳይ ጠንካራ ዉሳኔ እንዲያሳልፍ እየጠየቁ ነዉ።

«የአዉሮፓ ኅብረት የበላይ አካልም ሳይዘገይ በሳምንቱ መጀመሪያ፤ ተመሳሳይ ማዕቀብ ይፋ ዉሳኔ ማለት ነዉ ያሳልፋል ብለን እንጠብቃለን።»

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትም ዛሬ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የሊቢያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ይነጋገራል። ለአራት ሳምንታት በሚቆየዉ የምክር ቤቱ ጉባኤ የአዉሮፓ ኅብረት፤ ጀርመን፤ ጣሊያን፤ ፈረንሳይ፤ ብሪታንያ፤ የአሜሪካንና የሩሲያ እንዲሁም የሌሎች አገራት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ይገኛሉ።

አብዮታዊዉ መሪ ጋዳፊምስል dapd

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ኃላፊ ናቪ ፒሌይ የሊቢያን ጨምሮ በርካታ የመካከለኛዉ ምስራቅ አገራት መሪዎች ሕዝባቸዉን በጠንካራ ኃይል እንደሚጫኑ በመጠቆም፤ የሊቢያ የተቃዉሞ ወገን ከለላ እንደሚያስፈልገዉ አመልክተዋል። በአገር ዉስጥ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ያየለባቸዉና ዓለም ዓቀፍ ዉግዘት የሚወርድባቸዉ ጋዳፊ ግን የተመድ የጣለባቸዉን ማዕቀብ በማጣጣል ጥቂት ያሏቸዉን ተቃዋሚዎቻቸዉን ደምስሰዉ በመንበራቸዉ የመክረም ተስፋቸዉ ገና አልተሟጠጠም።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW