ሊጠፋ የተቃረበዉ የጊኒ ትል
ማክሰኞ፣ ጥር 9 2009የሰሞኑ ሰናይ ዜና የጊኒ ትል ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ከማሳየቱ በተጨማሪ ማሊ ዉስጥ ከብዙ ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በትሉ የተያዘ ሰዉ አለመኖሩ መታየቱ ነዉ። አሁን ጊኒ ትል ይገኝባቸዋል ከተባሉት 25 ሰዎች ሦስቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ፣ 16ቱ ቻድ እንዲሁም ቀሪ ስድስቶቹ ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ነዉ የሚገኙት። ጊኒ ዎርምን ለማጥፋት ዘመቻዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሲጀመር ችግሩ የታየዉ በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደነበር የካርተር ማዕከል ድረ ገጽ መረጃ ይዘረዝራል። ዶክተር ዘሪሁንም ይህንኑ ያጠናክራሉ። ይህ በጣም ረዥም ትል ከታማሚዉ ሰዉነት የሚወጣዉ በዉኃ ዉስጥ መሆኑን ነዉ ዶክተር ዘሪሁን የሚናገሩት። ከታማሚዉ መዉጣቱ አንድ ነገር ቢሆንም መዘዝ ግን አለዉ።
አንድ ሰዉ በጊኒ ትል የተበከለ ዉኃ ጠጥቶ በበሽታዉ ቢያዝም በአጭር ጊዜ ዉስጥ ምልክት አያሳያም። ይህንንም ዶክተር ዘሪሁን የሚገርም የበሽታዉ ባህሪ ነዉ ይሉታል። በነገራችን ላይ ጊኒ ዎርም ቀደም ሲል ጊኒ ዉስጥ በብዛት በመገኘቱ ስያሜዉ በዚያዉ ይቅር እንጂ ጊኒ ከዚህ ችግር ከተላቀቀች ዓመታት ተቆጥረዋል። ጊኒ ዎርም ወይም ጊኒ ትል በህክምናዉ ድራንኮንኮላይስስ ትባላለች። ለረዥም ዓመታት የጊኒ ትልን ለማጥፋት የተካሄደዉ ዘመቻ ዉጤት ማሳየት መጀመሩ እና የታማሚዎቹ ቁጥርም በአጠቃላይ 25 ብቻ መሆኑ ተነግሯል። ታማሚዎቹም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሦስት የአፍሪቃ ሃገራት ብቻ ነዉ ይገኛሉ የተባለዉ። ዶክተር ዘሪሁን፤ የታማሚዎቹ ቁጥር መቀነሱ እዉነት ቢሆንም ከበሽታዉ ባህሪ በመነሳት ሙሉ ለሙሉ ጠፋ ብሎ መናገር አዳጋች ይሆናል ይላሉ።
በበጎ ፈቃድ ሠራተኞች የቤት ለቤት አሰሳዉ በየሁለት ቀኑ እንዲካሄድ የተደረገበት ዋናዉ ምክንያት ዶክተር ዘሪሁን እንደገለጹልን ትሉ የሚያሳብጠዉ ቦታ ሲቆስል በባህላዊ መንገድ ሰዎችን ዉኃ ዉስጥ መክተቱ ፋታ ስለሚሰጥ ያ ተደርጎ ዉኃ እንዳይበከል እና በሽታዉ ወደ ሌሎች እንዳይተላለፍ ለመከላከል ነዉ።
በሽታዉ ጋምቤላ ዉስጥ ጎግ እና አቦቦ የሚባሉትን ሁለት ወረዳዎች በተደጋጋሚ እንደሚያጠቃ ነዉ ዶክተር ዘሪሁን የገለፁልን። በሁለት ወረዳዎች ደግሞ ከአራት እስከ አምስት መቶ የሚሆኑ የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች ኅብረተሰቡን በማንቃትና በመከታተል ይሳተፋሉ። አንድ ሰዉ በዚህ በሽታ ሲለከፍ ከአንድ በላይ ትል ከሰዉነቱ ሊወጣ ይችላል። ዶክተር ዘሪሁን እንደገለጹልን በአንድ ዓመት ዉስጥ ከአንድ ሰዉ እስከ 15 ትል ሊወጣ ይችላል። በአሁኑ ጊዜ ግን ከሦስት እና ሁለት የበለጠ የወጣለት አልታየም። ትሉ በህክምና ባለሙያዎች ቁጥጥር ከወጣ ለግለሰቡም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ምንም ዓይነት ችግር እንደማያመጣም አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁን ቀሩ የተባሉት ሁለት ታማሚዎች በተገቢዉ ክትትል ስር የቆዩ መሆናቸዉን የጠቆሙት ዶክተር ዘሪሁን ከደቡብ ሱዳን የመጣዉ ሦስተኛዉ ታማሚ ያለፈባቸዉ ስፍራዎችን የመከታተል እና ዉኃዎቹን የማከሙ ትልቅ ሥራ እንዳለ ሳይገልፁ አላለፉም።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ