1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ተመራማሪዎች ለኤችአይቪ/ኤድስ አዲስ መድሃኒት አገኙ

ረቡዕ፣ ኅዳር 25 2017

ሌናካፓቪር፤ የተባለ አዲስ የኤችአይቪ/ኤድስ መድሃኒት ስኬታማ በሆነ መንገድ መሞከሩን ተመራማሪዎች ይፋ አድርገዋል። ጊሊድ በተባለ የአሜሪካ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ የተሰራው ይህ መድሃኒት በመርፌ መልክ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን፤100 ፐርሰንት ውጤታማ ነው ተብሏል።

South Africa HIV Shot Lenacapavir Impfung
ምስል Nardus Engelbrecht/AP/picture alliance

ተመራማሪዎች ለኤችአይቪ/ኤድስ አዲስ መድሃኒት አገኙ

This browser does not support the audio element.

ከ40 ዓመታት በፊት በዓለም ላይ ለተከሰተው የኤችአይቪ/ኤድስ ወረርሽኝ ህክምና እና የመከላከያ መድሃኒት ለማግኘት የሳይንስ ሊቃውንት በበሽታው ላይ በርካታ ምርምሮችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ምንም እንኳ እነዚህ ምርምሮች በሽታውን ለማዳን እና ለመከላከል የሚያስችል ሁነኛ መፍትሄ ባያመጡም። ART የተባለውን  የፀረ-ኤችአይቪ ሕክምና ጨምሮ የተለያዩ አማራጮችን ለማግኘት ረድተዋል።
ከአርባ አመታት ያለሰለሰ ምርምር  በኋላ ደግሞ  በበቅርቡ ሌናካፓቪር፤ የተባለ አዲስ የኤችአይቪ/ኤድስ መድሃኒት ስኬታማ በሆነ መንገድ መሞከሩን ተመራማሪዎች ይፋ አድርገዋል።
የዚህ መዳህኒት የምርምር ውጤት በጎርጎሪያኑ ሀምሌ  2024 ዓ/ም በተካሄደው የዓለም ኤድስ ጉባኤ ላይ የቀረበ ሲሆን፤ እንደ ባለሙያዎቹ  አዲሱ መድሃኒት ኤች አይቬ ኤድስን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ በመሆኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። በጀርመን የኮሎኝ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የተላላፊ በሽታዎች መከላከያ ማዕከል ኃላፊ የሆኑት  ፕሮፌሰር ክላራ ሌህማን በግኝቱ መደሰታቸውን ይገልፃሉ።
«በጣም በአዎንታዊ መልኩ ነው የማየው።ሙሉ በሙሉ  ተደስቻለሁ። መናገር የምችለው በአለም የኤድስ ጉባኤ ላይ ይህ መረጃ ሲቀርብ እኔ እምብዛም ያላጋጠመኝ አስደሳች ድባብ ነበረ። ያ ደግሞ በጣም ድንቅ ነው። [...] እንደዚህ አይነት እድገቶች መኖራቸው በጣም ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። እንዲሁም በኤችአይቪ ምርምር፣ ህክምና እና ፈውስ ላይ  የበለጠ  እየተንቀሳቀስን እና  የበለጠ  እየተገነዘብን ነው ብዬ አምናለሁ። »ብለዋል። 

መድሃኒቱን ልዩ የሚያደርገው ምንድነው?

ጊሊድ በተባለ የአሜሪካ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ የተሰራው ይህ መድሃኒት በኤችአይቪ ዘረመል ላይ የሚገኘውን ሾጣጣ ቅርጽ ያለው የፕሮቲን ሽፋን በማጥቃት እና ተዋህሲው እንዳይራባ በማድረግ፤100  ፐርሰንት ውጤታማ ነው ተብሏል።
በአሁኑ ጊዜ  በተህዋሲው የተያዙ ሰዎች እንደ ካቦቴግራቪር /cabotegravir/ (CAB) ያሉ ሌሎች የፀረ ኤችአይቪ መድሃኒቶች በየወሩ እና በየ  ሁለት ወሩ የሚወስዱ ሲሆን፤ ትሩቫዳ/Truvada/  የተባለውን መድሃኒት ደግሞ በየቀኑ መወሰድ ይጠበቅባቸዋል።
የጊሊድ አዲሱ የፀረ ኤችአይቪ መድሃኒት ግን፤ በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ በመርፌ መልክ የሚሰጥ ነው። ይህም  አጠቃቀሙን በጣም ቀላል ያደርገዋል።ይላሉ በሃይደልበርግ የአለም ጤና ተቋም ረዳት ተመራማሪ ዶክተር አስትሪድ በርነር-ሮዶሬዳ።

«ሌናካፓቪር ለብዙ ሰዎች ጨዋታ ቀያሪ መሆኑን ማየት በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ መወሰድ የለበትም። በዓመት ሁለት ጊዜ በመርፌ መልክ የሚሰጥ ነው።  ይህ በእርግጥ  በየቀኑ መድሃኒት ከመውሰድ የበለጠ ምቹ ነው።»ብለዋል።ተመራማሪዋ እንደሚሉት አዲሱ መድሃኒት የበለጠ ምቹ ብቻ ሳይሆን፤ መድሃኒት እጥረትን ለመቅረፍ እንዲሁም እለታዊ መድሃኒቶችን በመውሰድ ከቤተሰብ እና ከአካባቢ ማኅበረሰብ የሚደርስን መድሎ እና መገለሎችን ለማስወገድም እፎይታ ሊሆን ይችላል ያላሉ። «ይህንን መርፌ ለመውሰድ በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ወደ ክሊኒኩ መሄድ ካለብኝ፤ በጣም ምቹ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ ማለት ትንሽ በሚስጥር ልይዘው እችላለሁ።, እና መድሃኒት እየወሰድኩ እንደሆነ ለሁሉም ሰው መንገር የለብኝም።ያም መድሃኒቱን ለሚወስዱት ሰዎች ብዙ ጥቅሞች አሉት።»ብለዋል። ይህም በኤችአይቪ እጅግ በከፍተኛ  ደረጃ ለሚጠቁት በተለይ ለሴቶች እና ወጣት ልጃገረዶች የበለጠ እንደሚጠቅም ተመራማሪዋ ገልፀዋል። 

በ2023 ዓ/ም ወደ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በተዋህሲው ​​መያዛቸውን  አዲሱ የተባበሩት መንግስታት የኤድስ ማስተባበሪያ /የዩ ኤን ኤድስ/ ሪፖርት አመልክቷል። ምስል Peter Kovalev/TASS/dpa/picture alliance

ሌናካፓቪር መቼ በገበያ ላይ ይውላል?

ተስፋ ሰጪ የተባለው ይህ መድኃኒት በአውሮፓ ኅብረት  የኤችአይቪ ህሙማንን ለማከም  ፈቃድ አግኝቷል። ሆኖም አምራቹ ኩባንያ ማረጋገጫ እየጠበቀ በመሆኑ፤መድሃኒቱን ገና ገበያ ላይ አልዋለም።  በቅርብ ግን ማረጋገጫ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ያም ሆኖ ሌናካፓቪር ኤድስን ለመከላከል በሚደረገው ትግል ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን ውጤት በእርግጥ ያመጣ እንደሁ ገና ግልጽ አይደለም። ያን ለማለት መድሃኒቱ በሰፊው ጥቅም መዋል አለበት። ለዚህ ደግሞ መድሃኒቱ በተመጣጣኝ ዋጋ መገኘት አለበት።.

አዲሱ መድሃኒት ምን ያህል ውድ ነው?

ይሁን እንጂ ሌናካፓቪር በዋጋ ደረጃ በጣም ውድ ነው።የዩኤስ አሜሪካው  የመድኃኒት ኩባንያ ጊልያድ፤ ለህክምናው በዓመት ከ40,000 ዶላር በላይ ያስከፍላል። ለማነጻጸር፡- ሌሎች የኤችአይቪ መከላከያ ዘዴዎች በወር በአማካይ ከ50-60 ዩሮ ያስከፍላሉ፣ ማለትም ዋጋው በዓመት ከ600-700 ዩሮ አካባቢ ነው። የጤና መብት ተሟጋቾች እና  እንደ ዶክተር አስትሪድ ያሉ ባለሙያዎች እና ይህንን ይተቻሉ። 
«ነገር ግን እንደ ህክምና በጣም ውድ ነው. ለእነዚህ ሁለት መርፌዎች በዓመት 42,000 ዶላር አካባቢ የሚያስወጣ ይመስለኛል። እና አሁን ጥያቄው መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገሮች እንዴት ነው [ይህንን ገንዘብ] የሚያገኙት? በጣም ጥሩ ነው፣ በተለይ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገሮች። ይህ መርፌ መወሰድ ያለበት  በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ በመሆኑ፤ እንዳልኩት፣ ይህ በእርግጥ በየቀኑ መድሃኒት ከመውሰድ የተሻለ ቀላል ነው። ነገር ግን በዓመት ለአንድ ሰው 42,000  ዶላር  የማይቻል ዋጋ ነው።» በማለት ገልፀዋል።

አዲሱ የኤች አይቪ መድሃኒት በዓመት 42,000 ዶላር ያስወጣል።ምስል Irfan Aftab/DW

ሌናካፓቪር የት ይገኛል?

የመዳህኒት አምራች ኩባንያው ጊሊድ፤ መድሀኒቱን በቀጣይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ለማምረት እና ለመሸጥ ከበርካታ  መድሃኒት አምራቾች ጋር በመደራደር ላይ ነው። ይህም ከሰሃራ በታች ያሉ አንዳንድ ሀገራትን ጨምሮ 120 ሀገራትን ያካትታል ተብሏል።
«እና ጊሊድ እስካሁን  ከስድስት ኩባንያዎች ጋር  የፈቃደኝነት ስምምነቶችን መፈራረሙን እና በ120 ሀገሮች የፈቃድ መስጫ ቦታዎችን ይፋ አድርጓል።  ያ በርካታ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን ያጠቃልላል።» ብለዋል ዶክተር  አስትሪድ በርነር  ሮዶሬዳ ። 
በተመሳሳይ ጊዜ አንዳንድ መካከለኛ ገቢ ያላቸው እንደ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ እና ፔሩ በተፈቀደው ክልል ውስጥ ላይሆኑ ይችላሉ። ምንም እንኳን ጊሊድ እዚያ መድሃኒቱን ቢሞክርም ። ይህም የስነምግባር እና የህግ ጥያቄዎችን ያስነሳል ብለዋል በርነር-ሮዶሬዳ።
የዩኤንኤድስ ምክትል ዳይሬክተር ክሪስቲን ስቴግሊንግ  ሁኔታውን በተመሳሳይ መንገድ ያዩታል።እሳቸው እንዳሉት እንዲህ ያሉት «ጨዋታ ቀያሪ» ፈጠራዎች ለሁሉም ሰው ተደራሽ  ከሆኑ ብቻ ነው በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ የሚቻለው።

በአለም አቀፍ ደረጃ የኤችአይቪ አደጋ ምን ያህል ነው?

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኤችአይቪን ወረርሽኝ በ2030 ማቆም ይፈልጋል። ነገር ግን እውነታው ከዚያ በጣም ሩቅ ነው።፡ በዓለም ዙሪያ ከ ከ42 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አሁንም በተዋህሲው ተይዘዋል። ወደ 30 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑት ህክምና እየተደረገላቸው ነው። ሲሶ ያህሉ ግን በደም ውስጥ ያለውን የተዋህሲ መጠን የሚቀንስውን የፀረ-ኤችአይቪ ሕክምናን አያገኙም።
በጎርጎሪያኑ  2010 እና 2021 መካከል በዓለም ዙሪያ  በኤችአይቪ የመያዝ ዕድል በ22 በመቶ ቀንሷል። ሆኖም በ2023 ዓ/ም ወደ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በተዋህሲው ​​መያዛቸውን  አዲሱ የተባበሩት መንግስታት የኤድስ ማስተባበሪያ /የዩ ኤን ኤድስ/ ሪፖርት አመልክቷል።
630,000 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ የኤድስ ታማሚዎችን ይበልጥ በሚያጠቁ በሽታዎች ሞተዋል። በሽታው ከተከሰተ ጀምሮ  ደግሞ በአጠቃላይ በበሽታው እስካሁን በዓለም ላይ ከ43 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
አስትሪድ በርነር  ሮዶሬዳ በሽታውን በመከላከል ረገድ ብዙ አልተሰራም ይላሉ። «በመከላከል ረገድ ብዙ መሻሻል አላደረግንም። ይህ በትክክል መነገር አለበት። በ2030 የኤድስን ወረርሽኝ ማቆም ከፈለግን በሚቀጥለው ዓመት አዳዲስ በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ወደ 370,000 መቀነስ አለብን። አሁንም 1.3 ሚሊዮን አዳዲስ በበሽታው የሚያዙ ነበሩ።»ብለዋል።
በሽታው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ እና በደቡብ እስያ ሀገራት የቀነሰ ሲሆን፤  በአንፃሩ በመካከለኛው እና በምስራቅ አውሮፓ፣ በመካከለኛው እስያ፣ በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ቁጥር እየጨመረ ነው።

እንደ ተባበሩት መንግስታት የኤድስ ማስተባበሪያ በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም መድሃኒቱ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች መካከል 15 በመቶው ብቻ አግኝተዋል።ምስል AP

አማራጮች አሉ?

ላለፉት አርባ አመታት በበሽታው ላይ ጥልቅ ምርምር ቢደረግም አሁንም በኤች አይ ቪ ላይ ምንም የመከላከያ ክትባት አልተገኜም። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ የኤችአይቪን  የሚከላከሉ አንዳንድ ውጤታማ የቅድመ-መጋለጥ መድሃኒቶች አሉ። ምንም እንኳን ለአጠቃቀም ምቹ ባይሆኑም ፣እነዚህ የአስቀድሞ ተጋላጭነት መድሃኒቶች /ፕሮፊላክሲስ/ በአንዳንድ ሀገሮች የኤችአይቪን መጠን በእጅጉ መቀነስ ችለዋል።
እስካሁን ድረስ እነዚህ ርካሽ መንገዶች በተለይ በበለጸጉ አገሮች ውስጥ ውጤታማ ሆነዋል። ከፍተኛ የኤችአይቪ መጠን ባለባቸው ድሃ አገሮች ግን እነዚህ የመከላከያ እርምጃዎች ብዙውን ጊዜ በጣም ውድ ናቸው። እንደ ተባበሩት መንግስታት የኤድስ ማስተባበሪያ /UNAIDS/ ዘገባ  በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም መድሃኒቱ /PREP/ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች መካከል 15 በመቶው ብቻ አግኝተዋል።
ከሰሃራ በታች ባሉ  የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ በኤችአይቪ ተዋህሲ ከተያዙት ውስጥ ART የተባለውን መድሃኒት የሚያገኑት 75 በመቶ  የሚሆኑት ናቸው።
ስለሆነም  በተለያዩ መንገዶች ራስን ከበሽታው መጠበቅ ገንዘብ የማይወጣበት ቀላል፣ አስተማማኙ እና ተመራጩ መፍትሄ መሆኑን በባለሙያዎች ይመከራል።

 

ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW