ልሳነ ግፉዓን ድርጅት ስለወልቃይት ጉዳይ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 27 2015
የወልቃይት እና አካባቢውን ጉዳይ በህዝበ ውሳኔ ለመፍታት የቀረበው የውሳኔ ዐሳብ ተቀባይነት የለውም ሲል ልሳነ ግፉዓን ድርጅት አስታወቀ። የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ዐቢዩ በለው ለዶቼቬለ እንደተናገሩት፣ለወልቃይትና አካባቢው ችግር፣በመፍትሔነት እየቀረቡ ያሉት ህዝበ-ውሳኔ በፌዴራሊዝም እንዲተዳደር አሊያም የራስ ገዝ አስተዳደር ዐሳቦች ተቀባይነት የላቸውም።
የወልቃይት ጉዳይ በህገ መንግስቱ መሰረት እንደሚፈታ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው መናገራቸው ይታወሳል። ከሰሞኑም የብሔራዊ ደህንነት አማካሪያቸው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ለፖለቲካ ፓርቲዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ የወልቃይት አካባቢን ማካለል ጉዳይ፣የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚዘረጋው ስርዓት መሰረት እንደሚፈታ መናገራቸው ተዘግቧል። ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው፣ልሳነ ግፉዓን ድርጅት፣የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ሕዝብን የሰብዓዊ መብትና የፍትሕ ጥያቄ ይዞ በመታገል ረጅም ጊዜ ማሳለፉን የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ዐቢዮ ይገልጻሉ። ልሳነ ግፉዓን ድርጅት፣ በመንግስት ለቀረቡ የውሳኔ ዐሳቦች ምላሽ በሰጠበትና ይፋ ባደረገው ሰነድ ላይ፣ ደመፍትሔ ዐሳቦችን ውድቅ አድርጓቸዋል ይላሉ አቶ ዐቢዩ በለው።
"ሰሞኑን መንግስት በተለያዩ መድረኮች፣ በተለይም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ሰብስቦ ባወያየበት መድረክ፣አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ የተባለዉ ጉዳይ፣ የወልቃይት ጉዳይ በፌደሬሽን ምክር ቤት ይፈታል ያሉበት፣አቀራረብ አለ።በመንግስት በኩል እነዚህ እንደመፍትሔ ሀሣብ ተደርገው ሲቀርቡ ህዝባችን የማይቀበላቸው መሆኑን በዚህ ሰነድ ላይ ገልጸናል።በፍጹም ህዝበ ውሳኔና ራስ ገዝ ወይም በፌዴራል ይኹን ማለት የህወሓት ፕላን ቢ ነው፤አንቀበለውም የሚል መልዕክት አስተላልፈናል።"
የፌደራል መንግስቱ፣ የወልቃይትን ህዝብ ዐማራዊ ማንነት በይፋ እውቅና መስጠትና ማክበር ይገባዋል ያሉት ሊቀመንበሩ፣ወልቃይት፣ጠገዴና ጠለምት ከ1983 በፊት በነበሩት ሁኔታ በይፋ እንዲካለሉ ጠይቀዋል።
"መፍትሔው፣ በጉልበት የተወሰደን መሬት ወይም በጉልበት የተደፈፈጠን ማንነት፣ወደነበረበት መመለስ ነው።ያም ከ1983 ዓ.ም በፊት ወደነበረበት ሁኔታ መመለስ ነው።የወልቃይት፣ጠገዴ ጠለምት ሕዝብ ዐማራ ነው። ወደ ዐማራነቱ መመለስ። የወልቃይት፣ጠገዴ ጠለምት መሬቱ የጎንደር ነው፤ወደ ጎንደር መመለስ። ድንበሩ ደግሞ ተከዜ ነው፣ያንን የተከዜ ወሠንነት ዕውቅና ሰጥቶ፣ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምትን ወደዐማራ ማካለል ነው መፍትሔው።" ወልቃይት በዐማራና በትግራይ ክልሎች ማኸከል ያለ ጸብ ነው፣ ለተባለውም፣ አቶ ዐብዩ ምላሽ ሲሰጡ የሚከተለውን ብለዋል።
"ይህ የዐማራና የትግራይ ጸብ አይደለም።ይኼ የወልቃይት ሕዝብ ያነሳው ጥያቄ ነው።የወልቃይት ሕዝብ፣በህወሓት አፈናና ጭቆና ውስጥ እየማቀቀ፣የወልቃይት ሕዝብ የዐማራ ማንነቱን ተነጥቆ ትግራይ ትሆናለኽ በተባለና ያ ሰቆቃ በበዛበት ጊዜ ከመጀመሪያው ጀምሮ የታገለ ነው፤የተቃወመ ነው።"
የወልቃይት ሕዝብ የዐማራ ማንነት ጥያቄ ምላሽ በመነፈግ ምክንያት፣ የዐማራ ህዝብ አንድነትና የክልሉ መንግስት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ሲሉ ሊቀመንበሩ አሳስበዋል።
አቶ ዐቢዩ፣ እንዳሉት በዚሁ ሰነዳቸው ላይ፣ የዐማራ ክልል ወሰን ወልቃይት ጠገዴና ጠለምትን ባካተተ ሁኔታ እንዲሻሻል፣ በዚህም መሠረት የክልሉን ህገ መንግስት ማሻሻያ በማድረግ እንዲያጸና አጥብቀው ጠይቀዋል።
በወልቃይት ሕዝብ ላይ ተፈጸመ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ወንጀሎች የሚመረመር ልዩ ዐቃቤ ሕግ እንዲቋቋምም ጥሪ አቅርበዋል። ለመላው ዐማራ ሕዝብ ባቀረቡት ጥሪም፣የዐማራ ታሪካዊ መሬቶች ያሏቸውን ሕጋዊ ለማድረግና ለማጽናት በቀጣይነት ለሚያደርጉት ትግል ከጎናቸው እንዲሰለፍ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ