1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ልጄን በገንዘብ ገዛሁት» የቀድሞ ታጋች አባት

ሐሙስ፣ ሰኔ 22 2015

ከአድካሚና አሰልቺ የእግር ጉዞ በኋላ ልጃቸውና ሌሎች ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁ 4 ታጋቾች አንድ ቦታ ከደረሱ በኋላ የመከላከያ አባላት መታወቂያ እንደጠየቋቸው ወታዶሮቹ ልጆቹ ከእነሱ ጋር እንዲያድሩ ካደረጉ በኋላ ጠዋት ወደሚፈልጉበት እንዲሄዱ በማድረጋቸው ሰኔ 18/2015 ዓ ም “ልጄን በገንዘብ ገዝቼ መጣሁ” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

Äthiopien Sululuta | "Land Grabbing"
ምስል Seyoum Getu/DW

የአጋች-ታጋቾች ድራማ

This browser does not support the audio element.


መንግስት በአጋችቾ ላይ የማያዳግም እርማጃ ካልወሰደ ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች እየተናገሩ ነው። ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን “አሊ ዶሮ” በተባለ ቦታ ልጃቸው ታግቶ የነበር አንድ አባት” ልጄን በገንዘቤ ገዛሁት” በማለት ልጃቸውን ከፍተኛ ገንዘብ ለአጋቾች ከፍለው ማስለቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡ዓለምነዉ መኮንን ከባሕርዳር
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሰዎች እገታና እንግልት ህብረተሰቡን ወደ ከፍተኛ ጭንቅና ስጋት እየዳረገው እንደሆነ አንዳንድ የህብረተሰቡ ክፍሎች  እየተናገሩ ነው፡፡
ሰኔ 10/2015 ዓ ም ልጃቸው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አሊ ዶሮ በተባለ አካባቢ ታግቶባቸው የነበሩ አንድ አባት ልጃቸውን ለማስለቀቅ ያደረጉትን ሂደት ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፣ አስፈሪ፣ ለስጋት የሚዳርግና ለመኖር የሚያስጠላ ብለውታል፡፡
ድርጊቱ በቅብብሎሽ እንደሚሰራ የገለፁት እኚህ አባት የያዙትን ገንዘብ መጀመሪያ ለአንድ ግለሰብ፣ እንደገና ደግሞ ለሌላ ሰው መጠኑን ጭምር ገልፀው አውላላ ሜዳ ላይ ማስረከባቸውንና እርሳቸው ወደ ገብረ ጉራቻ መመለሳቸውን ይዘረዝራሉ፡፡
ገንዘቡ፣ በእርሳቸው አገላለፅ “ለዋናዎቹ አጋቾች” ከደረሰ በኋላ ተደውሎ ልጃቸው እንደተለቀቀ ያስረዳሉ፡፡
ከአድካሚና አሰልቺ የእግር ጉዞ በኋላ ልጃቸውና ሌሎች ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁ 4 ታጋቾች  አንድ ቦታ ከደረሱ በኋላ የመከላከያ አባላት መታወቂያ እንደጠየቋቸው የሚናገሩት እኚህ አባት፣ ወታዶሮቹ ልጆቹ ከእነሱ ጋር እንዲያድሩ ካደረጉ በኋላ ጠዋት ወደሚፈልጉበት እንዲሄዱ በማድረጋቸው ሰኔ 18/2015 ዓ ም “ልጄን በገንዘብ ገዝቼ መጣሁ” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
መንግስት አፋጣኝ መፍትሔና እርምጃ ካልወሰደ፣ የተወሳሰበ ማሕበራዊ ቀውስ ይፈጠራል የሚሉት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፣ የአካባቢው አርሶ አደሮች በድርጊቱ እንደሚያዝኑ፣ እንደተማረሩና ተረጋግተው መደበኛ ስራቸውን ለመስራት መቸገራቸውን ነው ያስረዱን፣ በአዩት አካባቢ የህክምናና የትምህርት ተ ቋማትን ማየት እዳልቻሉ የገለፁት የዚሁ ታጋች ወላጅ አባት የሚታገቱ ሰዎችም በአርሶ አደሮች ቤት እንዲያድሩ፣ እንዲቀለቡ እንደሚደረግ አስረድተዋል፣ በዚህም የአካባቢው አርሶ አደሮች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መጋለጣቸውን ነው የአብራሩት፤ ከዚያም አልፎ አርሶ አደሮቹ ለታጋቾች የግል ልብሳቸውን ጭምር በማካፈል ለልጀቻቸው ውለታ እንደዋሉ ነው የተናገሩት፡፡
አንድ የአማራ ክልል ነዋሪ በየቀኑ እየጨመረ የመጣው የሰዎች እገታ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጭንቅና ፍርሀት እየፈጠረ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
“ሰው ወጥቶ ለመግባት ለነገ እርግጠኛ አይደለም፣ ማንም ሰው ነገ አለሁ ብሎ የሚናገርበት ነገር አይደለም ያለው፣ አጠቃላይ ሁኔታው ሰው ሆኖ መፈጠር የሚያስጠላበት ወቅት ነው፣ ቤተሰብ መፍጠሩማ ጨርሶ ያስጠላል፣ እኔ ሌላ ቦታ 3 ልጆች አሉኝ፣ ሌሊት እንቅልፍ አይወስደኝም፣ ዛሬ ታግተው ተወሰዱ፣ ነገ ታግተው ተወሰዱ፣ በሚል ስጋት ውስጥ ነኝ፣ እና አጠቃላይ በህብረተሰቡ ውስጥ የፈጠረው ጭንቀትና ስጋት በቃላት ለመግለፅ ይከብዳል፣ የእገታው ጉዳይ እጅግ፣ እጅግ፣ እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰኔ 11/2015 ዓ ም በአማራ ክልል ከሰሜን ሜጫ ዞን ወደ ምዕራብ ጎጃም ዞን አንድን ሰው አግተው ገንዘብ ሲጠይቁ የነበሩ ሁለት ሰዎች በህብረተሰብ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በምዕራብ ጎጃም  የይልማና ዴንሳ ወረዳ  ፍርድ ቤት ሰኔ 14/2015 ዓ ም በዋለው የተፋጠነ ችሎት በ11 ዓመት እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የይልማና ዴንሳ ወረዳ የዜና፣ ህትመት ዝግጅትና ስርጭት ቡድን መሪ አቶ ክንዱ ዳምጤ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW