1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስልጣኔ ፈር ቀዳጅ ከተማ

ሐሙስ፣ መጋቢት 12 2011

ባለ ታሪክ፤ ጥንታዊት ከተማ፤  የባህል ፈርጥ ናትም ይሏታል። ተፋቅረው የሚኖሩባት የአብሮነት ከተማ ሲሉም ይመሰክሩላታል፤ ይህቺው ታሪካዊት ከተማ ከተቆረቆረች 1,000 ዓመት የሆናት ቀደምት ስልጣኔን ያስገባች የኢትዮጵያ ባለውለታ፤ ሀረር። የንግድ ማእከል ሆና አገልግላለች።

Interview mit Abdulsemed Idris
ምስል DW/M. Faysel

የጁገል ግንብ አንዱ የሀረር ጥንታዊ ስልጣኔ መገለጫ

This browser does not support the audio element.

ባለ ታሪክ፤ ጥንታዊት ከተማ፤  የባህል ፈርጥ ናትም ይሏታል። ተፋቅረው የሚኖሩባት የአብሮነት ከተማ ሲሉም ይመሰክሩላታል፤ ይህቺው ታሪካዊት ከተማ ከተቆረቆረች 1,000 ዓመት የሆናት ቀደምት ስልጣኔን ያስገባች የኢትዮጵያ ባለውለታ፤ ሀረር።
በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የምትገኘው ሀረር፤ ከአዲስ አበባ በ526 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ሀረር 343.2 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ጥንታዊት ከተማ ናት። በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦችን ያቀፈች ከተማ ናት። ሀረሪ ፣ ኦሮምኛ፣ አማርኛ ፣ ትግርኛ፣ ጉራጌኛ እና ሱማሌኛ ቋንቋዎች ይነገሩባታል።
ከኢትዮጵያ ታሪካዊና የስልጣኔ ፈር ቀዳጅ ከተማነቷም ትጠቀሳለች። ሀረር ጥንታዊ ስልጣኔ መገለጫዋ ከሆኑት ባህላዊ ቤቶች እና የከተማዋ የውስጥ ለውጥ መንገዶችን ያቀፈው የጁገል ግንብ ነው። እነዚሁ አምስቱ በሮች በተለያዩ ቋንቋዎች የመጠሪያ ስያሜዎች ይጠራሉ።  ይሄው የጁገል ግንብ ከሀረሪ ቋንቋ በተጨማሪም በአረብኛ፣ በአማርኛና በኦሮምኛ ስያሜ መጠሪያዎች አሏቸው።
የጁገል ግንብ በከተማዋ ይሰነዘሩባት የነበሩ ጥቃቶችን ለመከላከል በሚል መገንባቱን ታሪክን አጣቅሰው ብዙዎች ይናገራሉ። ሆኖም ዛሬ ላይ ቅርሷ ለመሆን ሚና ተጫውቷል።  
በአንድ ወቅት የራስዋ መንግሥትም ኖሯት ታስተዳድር የነበረችው ሀረር፤ የኢትዮጵያ ዘመናዊነት በር ከፋች የሆነች ከተማ እንደሆነች የማኅበረሰብ ጥናትና የታሪክ ተመራማሪ አቶ አብዱልሰመድ እድሪስ ይገልጻሉ። 
“ሀረርን ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ለየት የሚያደርጋት እድሜ ጠገብ መሆኗ ነው። ለ1000 ዓመታት ታሪካዊ ሆና የኖረች ከተማ ነች። በኪነ ህንጻ ፣ በአከባቢን መንከባከብ፣ በውሃ አጠባበቅ ከሌሎች የሀገራችን ከተሞች ለየት ትላለች። በራስዋ አስተዳደር የነበራት፤ አራት ስርወ መንግሥት ያሳለፈች፤ 72 ነገስታት የነገሱባት፤ ለኢትዮጵያ ዘመናዊነት በር ከፋች የሆነች ከተማ ነች።”

ምስል Reuters/T.Negeri

የማህበረሰቡ የቤት አሰራር ጥበብ ጥንት ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው አቶ አብዱልሰመድ እድሪስ ይገልጻሉ። 
“ሀረር የቤት አሰራርዋ ለየት ይላል። ግንቡም ሆነ ቤቱ በአንድ ዓይነት አሰራር የተገነባ ነው። የቤት መስሪያው ድንጋይ ለየት ያለ ነው። በሀ ድንጋይ ይባላል። የቤቱ ረጅም ዓመት እንዲቆይ ያደረገው የድንጋዩ ዓይነት ነው። ሌላው የማጣበቂያው ጭቃ አዘገጃጀቱ ለየት ይላል። ከብዙ የአፈር ዓይነት የተደባለቀበት ሆኖ ለሁለት ወር ጭቃው ይቦካል።  በሃላም ጭቃው የመሳሳብ ደረጃ ላይ ሲደርስ ቤቱ ይሰራበታል። የመስሪያ ጥሬ ዕቃ ነው እንጅ የማይመሳሰለው አሁን ያለውም የሀረሪ ቤት በስነ ህንጻ አሰራር አሁንም ተመሳሳይነት አለው።”

ምስል AP / bilderbox.com / Fotomontage DW

የሀረር ከተማ የቤት አሰራር ጥንታዊ የሆነ ቅርጽ ተገንብቷል። በየትኛውም የሀረሪ ብሄረሰብ ዘንድ የሚሰሩ ቤቶች ተመሳሳይ እንደሆነ የብሄረሰቡ ተወላጅ የሆነው ሙባረክ ፈይሰል አጫውቶናል።
የሐረሪ ባህላዊ ቤት የሚገነባው በድንጋይ ሲሆን፤ ጣሪያው በጥድ ወይም በዋንዛ እንጨት የሚሰራ ነው። በዚህም ከቤት ውጪ ከፍተኛ ሙቀት ሲኖር ቤቱ ውስጥ ካሉ ግን ሙቀቱ አይሰማዎትም። ቤቱ ውስጥ ምቾት የሚሰጥ ቅዝቃዜ ይኖረዋል ይላሉ የብሄረሰቡ ተወላጅ። የሐረሪ ቤት ከዚት ከሚታየው ክፍል በተጨማሪም ሌሎች ሁለት ክፍሎት አሉት። አንድ ፎቅም አለው። በቤቱ ውስጥ እንደሚሰጡት አገልግሎት ስያሜና ትርጉም ያሏቸው አምስት ለመቀመጫነት የሚያገለግሉ መደቦች ይገኛሉ።
“ቤቱ ሁለት ምሰሶዎች አሉት። በአምስት የመቀመጫ መደቦች የተከፋፈሉ ናቸው። የንጉስ መደብ የቤቱ አባወራ የሚቀመጥበት፣ ትልቁ መደብ የተማሩ ሰዎች የሚቀመጡበት ሆኖ በዚሁ ቦታ ላይ ትምህርት ያስተምሩበታል። ሌላው ሽማግሌዎች የሚቀመጡበት መደብ ነው። ትንሿ መደብ ወጣት ወንዶች የሚቀመጡበት ሲሆን ከበሩ ጀርባ ያለው መደብ የእናቶች መቀመጫ ነው። ወለሉ ላይ ህጻናት ይቀመጣሉ።”

ምስል Reuters/T.Negeri

በሀረሪ የቤት የውስጥ ገጽታን ለማስጌጥ የሚጠቀሙበት የተለያዩ የስፌት ስራዎች አሉ ይሉናል ወ/ሮ ሩሚያ ኡመር። ጥቂቶቹም በቤቱ ግድግዳ ሲሰቀል ትርጉም አላቸው። 
“ሰሀኖች፣ በእንጨት የተሰሩ ቆሪዎች፣ ስፌቶች፣ ሌማት ፣ ወስከንባ የተለያዩ ስፌቶች በግራና በቀኝ ይሰቀላሉ። በድሮ ጊዜ ሴቶቹ ራሳቸው ነበር ሰፍተው የሚያመጡት አሁንም ይሄው ባህል አለ”

ሀረር ጥንታዊ የነበሩ ታሪካዊ ቤቶች ቅርስነቱ እየደበዘዙ እየሄዱ እንደሆነ የሀረሪ ነዋሪዎች ይናገራሉ። በዚህም ታሪካዊ ከተማነቷ እየደበዘዘ እንዳይሄድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይጠቅሳሉ። 

ነጃት ኢብራሂም 

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW