ሐሰተኛ መግለጫ እንደወጣበት ሶዴፓ አመለከተ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 14 2017
“የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ሶዴፓ)ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የፓርቲውን ምክትል ሊቀምንበር ከኃላፊነት አገደ” በሚል በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የወጣው መግለጫ ከእውነት የራቀ ነው ሲል ፓርቲው አስታወቀ፣ መረጃውን ያሰራጨው አካል በህግ እየተፈለገ እንደሆነም አንድ የሶዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ተናግረዋል፡፡
ይህ የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አወጣው የተባለው መግልጫ፣ የሶዴፓ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ራሔል ባፌ “...ፓርቲውን አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ በማድረግ በቅርቡ በድጅታል መገናኛ በተደረገ ዘመቻየፓርቲያችን እምነትና አቋም ባልሆነ አግባብ ከተለያዩ ቡድኖች ጋር በመሆን ያደርጉት ንግግር የፓርቲያችን ሥራ አስፈፃሚ የሚቃወመውና ፓርቲውን የማይወክል በመሆኑ ገለሰቧ ከሰኔ 1/2017 ዓ ም ጀምሮ ሥራ አስፈፃሚው ባልተለየ ድምፅ አግዷቸዋል” ብሏል፡፡ወጣ የተባለው መግለጫ ታግደዋል በተባሉት ዶ/ር ራሔል ምትክ ሌላ ምክትል ሊቀምነበር መተካቱንም ያብራራል፡፡
ወጣ የተባለውን መግለጫ መነሻ በማድረግ ከፓርቲው የአመራር ቦታ ተነሱ የተባሉትን የሶዴፓ ምክትል ሊቀምንበር ዶ/ር ራሔልን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ጠይቀናቸው የተባለው ሁሉ ሐሰት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ሥራ አስፈፃሚወም አመራር የመሾምም ሆነ የመሻር መብት የለውም ነው ያሉት፡፡ በየሶስት ዓምት አንዴ የሚደረገው ጉባዔ ነው የመሾምም ሆነ የመሻር መብትና ኃላፊነት ያለበት ነው ያሉት፡፡
የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባልና የሶዴፓ የህዝብ ግንኙንት ኃላፊ ዶ/ር ተከተል ርገኔ እንዲሁ የተባልው ነገር ሐሰት ነው መሆኑን ገልጠው የድርጊቱ ፈፃሚዎች በህግ እየተፈለጉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የደረጀቱን ዓርማ በመጠቀምና ህገውጥ (forged) ማህተም ተጠቅመዋል ነው ያሉት፡፡
የድርጊቱ ፈፃሚና ተባባሪዎቹ ከዚህ በፊት ተገምግመው ከድርጅቱ ሥራ የታገዱ ናቸውም ብለዋል፡፡
ድርጊቱን ፈፅሞታል የተባለው ግለሰብ በአሁኑ ሰዓት በፖሊስ እየተፈለገ እንደሆነም አመራሮቹ ገልጠዋል፡፡ ዶይቼ ቬሌም ድርጊቱን ፈፅሞታል የተባለውን ግለሰብ ለማግኘትና ሀሳቡን ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
ዶ/ር ራሔል የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ህልፈት ተከትሎ ሶዴፓን በምክትል ሊቀመንበርንት እየመሩ ይገኛሉ፡፡
ዓለምነው መኮንን
ፀሐይ ጫኔ