1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሐዋላን ወደ መደበኛው ሥርዓት ለመመለስ ያቀደው የኢትዮጵያ የ100 ቢሊዮን ብር ዕቅድ ይሳካል?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ መስከረም 1 2017

ባንኮች ሐዋላ ለሚላክላቸው ደንበኞች እስከ 17 በመቶ የሚደርስ የአዲስ ዓመት ስጦታ ቃል ገብተዋል። የአንዳንዶቹ ባንኮች ስጦታ ከመደበኛው የዶላር ምንዛሪ ሲደመር በተለምዶ ጥቁር ከሚባለው የጎንዮሽ ገበያ የሚያቀራርባቸው ነው። የኢትዮጵያ 31 ባንኮች ሐዋላ ለሚልኩ የ100 ቢሊዮን ብድር ማዘጋጀታቸውን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ይፋ አድርገዋል

ሐዋላ ዩሮ
የኢትዮጵያ 31 ባንኮች ሐዋላ ለሚልኩ የ100 ቢሊዮን ብድር ማዘጋጀታቸውን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ይፋ አድርገዋልምስል Friso Gentsch/dpa/picture alliance

ሐዋላን ወደ መደበኛው ሥርዓት ለመመለስ ያቀደው የኢትዮጵያ የ100 ቢሊዮን ብር ዕቅድ ይሳካል?

This browser does not support the audio element.

መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞቹ “በዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል” ገንዘብ ከተላከላቸው “የ6.82 በመቶ የአዲስ ዓመት ስጦታ” ለማበርከት በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ባሰራጨው ማስታወቂያ ቃል ይገባል። የባንኩ አማላይ ማስታወቂያ ዌስተርን ዩኒየን፣ መኒግራም እና ደሐብሺልን በመሳሰሉ የሐዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው የሚልኩትን ገንዘብ የተመለከተ ነው።

በዌስተርን ዩኒየን በኩል ጳጉሜ 2 ቀን 2016 በውጪ ሀገር ከሚኖር ልጃቸው 250 ዶላር የተላከላቸው እናት ገንዘቡን ሲቀበሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ500 ብር የሞባይል ካርድ እንደተሞላላቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። እኚህ እናት በማስታወቂያው መሠረት 17 ዶላር ገደማ ወይም በዕለቱ ምንዛሪ 1800 ብር ጉርሻ ባገኙ ነበር።

ሌላ አንዲት የአዲስ አበባ ነዋሪ በኩላቸው 200 ዶላር ሲላክላቸው ባንኩ የ300 ብር የሞባይል ካርድ እንደሞላላቸው ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ንግድ ባንክ ባሰራጨው ማስታወቂያ ስሌት ቢሆን ኖሮ የአዲስ አበባዋ ነዋሪ 13 ዶላር ወይም 1400 ብር ገደማ ተጨማሪ ስጦታ ሊያገኙ ይገባል።

ማስታወቂያዎቹ ግን ደንበኞች ገንዘብ በሐዋላ ተልኮላቸው ከባንኩ ገንዘብ ሲወስዱ ሥጦታውን ለማግኘት ተፈጻሚ የሚሆኑ ደንቦች እና ሁኔታዎችን በግልጽ አያቀርቡም።

“ኢትዮ-ዳይሬክት” ወይም “ካሽጎ” በተባሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መተግበሪያዎች በኩል ገንዘብ ለተላከላቸው ደንበኞች በአንጻሩ “16 በመቶ የአዲስ ዓመት ስጦታ” ሊያበረክት ተቋሙ ቃል ይገባል። እንደ ንግድ ባንክ ሁሉ ዳሸን ባንክ እና ዓባይ ባንክ 16 በመቶ፤ ኦሮሚያ ባንክ 17 በመቶ፣ የኢትዮ-ቴሌኮም ገንዘብ ማስተላለፊያ የሆነው ቴሌ-ብር በተመሳሳይ 17 በመቶ ጉርሻ ሊሰጡ ቃል ይገባሉ።

እነዚህ ግልጽነት የጎደላቸው ማስታወቂያዎች ከውጪ ሀገር ዶላር፣ ፓውንድ እና ዩሮን በመሳሰሉ መገበያያ ገንዘቦች የሚላከውን ሐዋላ የኢትዮጵያ ባንኮች ወደ ካዝናቸው ለማስገባት የሚያደርጉት ፉክክር አካል ናቸው።

ብር በአዲስ ዓመት

በኢትዮጵያ ባንኮች ጳጉሜ 4 ቀን 2016 የዶላር ዕለታዊ አማካኝ የምንዛሪ ተመን 114 ብር ገደማ እንደደረሰ የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል። ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን በአንድ ወር ውስጥ ብቻ 11.5 በመቶ ተዳክሟል።

ከሁለት ዓመታት በፊት “ፈጣን” የምንዛሪ ተመን ለውጥ ተግባራዊ ሲደረግ ብር በዚህ መጠን እንዳልተዳከመ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ያስታውሳሉ።

በዌስተርን ዩኒየን በኩል በውጪ ሀገር ከሚኖር ልጃቸው 250 ዶላር የተላከላቸው እናት ገንዘቡን ሲቀበሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ500 ብር የሞባይል ካርድ እንደተሞላላቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Inna Talan/PantherMedia/IMAGO

ሒደቱ አሁን በተያዘው ፍጥነት ከቀጠለ በታኅሳስ ወር መገባደጃ  አሁን ካለው የምንዛሪ ተመን በ30 በመቶ የብር አቅም ሊዳከም እንደሚችል ዶክተር አብዱልመናን ይጠብቃሉ።

የመንግሥት የፖሊሲ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጳጉሜ 5 ቀን 2016 ከፍተኛ የምንዛሪ ተመን በማቅረብ ቀዳሚ ሆኗል። ባንኩ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ116 ብር ገደማ ገዝቶ 122 ብር ገደማ ሲሸጥ ነበር። በዕለቱ አዋሽ ባንክ 115 ብር፣ ወጋገን ባንክ 112 ብር፣ ብርሀን ባንክ 111 ብር፣ ጎሕ ቤቶች ባንክ 110 ብር ገደማ አንድ የአሜሪካ ዶላር ሲገዙ ነበር።

ባንኮቹ ለተወሰኑ ቀናት የሚሰጡት ጉርሻ ከመደበኛው የዶላር የምንዛሪ ተመን ጋር ሲደማመር በተለምዶ ጥቁር ከሚባለው የጎንዮሽ ገበያ ጋር እንዲቀራረቡ ያደርጋቸዋል። በጎንዮሹ ገበያ በአንጻሩ አንድ ዶላር እስከ 125 ብር እየተመነዘረ እንደሚገኝ ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል።

በሁለቱ ገበያዎች መካከል ያለው ልዩነት የመቀራረብ አዝማሚያ ቢያሳይም ኢትዮጵያ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት መከተል ከጀመረች ወዲህ የነበረው የውጪ ምንዛሪ እጥረት ለመቀረፉ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም። በባንኮች የምንዛሪ ተመን እና መንግሥት በሚከተለው የገንዘብ ፖሊሲ መሠረት የጎንዮሹ ገበያ ጠባይ እንደሚወሰን የሚናገሩት ዶክተር አብዱልመናን የዕቃዎች የመሸጫ ዋጋ ሲጨምር የበለጠ ግልጽ እንደሚሆን ያስረዳሉ።

የዋጋ ግሽበትን የሚያባብስ የገንዘብ ፖሊሲ በሀገር ውስጥ እና በውጪ የተመረቱ ሸቀጦች በኢትዮጵያ ገበያ የሚሸጡበት ዋጋ እንዲጨምር ስለሚያደርግ ነጋዴዎች ወደ ባንክ ሲያመሩ የሚፈልጉትን ዶላር ካላገኙ ወደ ጎንዮሽ ገበያው እንደሚያመሩ አብዱልመናን ገልጸዋል።

“አሁን ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ ስለሚከተል የዕቃዎች ዋጋ እንደፈለገ እየጨመረ አይደለም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ወደ ፊት የዕቃዎች ዋጋ በግልጽ እየታወቀ ይመጣል” ሲሉ ተናግረዋል።

ሐዋላ “በደቦ”

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሣምንት ሕጋዊውን ሐዋላ ለማበረታታት “ደቦ” የተባለ አዲስ ዘመቻ ጀምሯል። ለስድስት ወራት የሚቆየውን ዘመቻ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ይፋ ሲያደርጉ “በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን” ከፍተኛ መጠን ያለው የውጪ ምንዛሪ ሊገኝ ይችላል የሚል ተስፋ አላቸው።

ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን በአንድ ወር ውስጥ ብቻ 11.5 በመቶ ተዳክሟል።ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በእርግጥ በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በትክክል አይታወቅም። አቶ ማሞ ግን ባንኮች ለዲያስፖራው ብድር፣ በውጪ ምንዛሪ በኢትዮጵያ ለሚኖራቸው ተቀማጭ “ልዩ እና ሳቢ ወለድ” እንዲሰጡ ይፈልጋሉ። አቶ ማሞ እንዳሉት የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች “ለሐዋላ አገልግሎት የሚያስከፍሉትን ወጪ ተመጣጣኝ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።”

አቶ ማሞ እንዳሉት “ባንኮች ለውጭ ሐዋላ ላኪዎች አበረታች የሆነ የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲሰጡ ይበረታታሉ።” የብሔራዊ ባንኩ ገዥ “መመዘኛውን የሚያሟሉ ሐዋላ ተቀባዮች” እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ መክፈት እንደሚችሉ ገልጸዋል። “ላስቀመጡት እና ለሚያስቀምጡት የውጪ ምንዛሬ ሒሳብ የተሻለ ወለድ ይከፈላቸዋል” ብለዋል።

ብሔራዊ ባንክ በአዲስ አበባ ከሌሎች ባንኮች ጋር በመሆን ይፋ ያደረገው ዘመቻ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከውን ሐዋላ በተለምዶ ጥቁር እየተባለ ከሚጠራው የጎንዮሽ ገበያ ወደ መደበኛው ለመመለስ ያቀደ ነው። በመደበኛው እና በጎንዮሹ ገበያ መካከል ያለው የምንዛሪ ተመን ልዩነት ከሐምሌ 22 እስከ ነሐሴ 29 ቀን 2016 ባሉት ቀናት ብቻ ወደ 4 በመቶ መውረዱን አቶ ማሞ ምሕረቱ ተናግረዋል።

የጎንዮሹ የውጪ ምንዛሪ ገበያ “የሚፈለግበት ምክንያት ሕገ ወጥ ገንዘብ ከኢትዮጵያ ለማውጣት ነው” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን የዶላር ምንዛሪ የቱንም ያክል ቢጨምር “ጥቁር ገበያ የተወሰነ ይኖራል” ሲሉ ተናግረዋል። በተለይ የፖለቲካ ብልሽት ለዚህ ዋና ሚና እንደሚኖረው አብዱልመናን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሐዋላ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሪ ከጎንዮሹ ገበያ ወደ መደበኛው ለማስገባት የጀመረው ዕቅድ ግን በርካታ ፈተናዎች ይኖሩበታል። በተለምዶ ጥቁር እየተባለ የሚጠራው የጎንዮሽ የውጪ ምንዛሪ ገበያ መደበኛ ካልሆነ ስደት ጋር ጭምር የተቆራኘ ነው። በሌሎች ሀገራት እየኖሩ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ባለመያዛቸው በባንኮች መገልገል የማይችሉ ኢትዮጵያውያን ባገኙት ገንዘብ ቤተሰቦቻቸውን ለመደጎም ሲሞክሩ ወደ ጎንዮሽ ገበያው ለማማተር ይገደዳሉ። በሀገሪቱ ሕግ የማይፈቀዱ ዕቃዎች ግብይቶችም ሌላው ለጥቁር ገበያው ኅልውና መሠረት ነው።

100 ቢሊዮን ብር ለዲያስፖራ ብድር

 የውጪ ምንዛሬ ሐዋላን ለመሳብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥው አቶ ማሞ “ከፍተኛ ዋጋ ያለው እጅግ ፈጣን ከፍተኛ ዕምነት የሚጣልበት” ያሉትን መተግበሪያ ይፋ አድርጓል። ይኸ መተግበሪያ ተጠቃሚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ በርካታ ባንኮች እንዲሁም በመረጧቸው የውጭ ባንኮች በቀላሉ መመዝገብ እና አካውንት መክፈት የሚያስችል እንደሆነ የተዘጋጀለት ማብራሪያ ይጠቁማል።

ለስድስት ወራት የሚቆየውን ዘመቻ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ይፋ ሲያደርጉ “በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን” ከፍተኛ መጠን ያለው የውጪ ምንዛሪ ሊገኝ ይችላል የሚል ተስፋ አላቸው።ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

“ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ መላክ ብቻ ሳይሆን ከሐዋላ ጋር የተገናኘ የብድር አገልግሎት ከአጠቃላይ ከባንክ ሥርዓቱ ማግኘት ይችላሉ” ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ሐዋላ ለሚልኩ የሀገሪቱ 31 ባንኮች በጋራ “ለብድር የሚሆን አጠቃላይ 100 ቢሊዮን ብር” ማዘጋጀታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ይኸ ለብድር የተዘጋጀ ገንዘብ “ቀላል አይደለም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን ባንኮች እስከ ሰኔ ለመኖሪያ ቤት እና  ለመኪና መግዣ ያቀረቡትን ጨምሮ ለደንበኞቻቸው የሰጡት አጠቃላይ ብድር  ጋር የሚቀራረብ እንደሆነ ገልጸዋል።“በአንድ ዓመት ለዲያስፖራ ይኸን ያህል አዘጋጅተናል ሲሉ በአንጻራዊነት ስናየው ትርጉም አይሰጥም” ሲሉይተቻሉ።

የፋይናንስ ገበያውን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለበት ብሔራዊ ባንክ ባለፉት ወራት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ባንኮች የሚሰጡትን ብድር የሚገድቡ መመሪያዎች ሥራ ላይ አውሏል። አቶ ማሞ የሚመሩት ብሔራዊው ባንክ በዕቅዱ ከገፋበት ተግባራዊነቱ አንድም “በባንኮች ላይ የተጣለውን ገደብ ማንሳት” አንድም “ገደቡ ሳይነሳ ለሌሎች ዘርፎች የሚቀርበውን ብድር መቀነስ ያስፈልጋል።”

“ሁለቱም የሚሆኑ አይመስለኝም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ከእውነታ የበለጠ ለማስታወቂያ የቀረበ ነው የሚመስለኝ” የሚል አቋም አላቸው።

ብሔራዊ ባንክ እና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሐዋላን ለማሳደግ የያዙት ዕቅድ ሌላ ፈተና የሀገሪቱ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ነው። በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ብርቱ ጉዳት ባደረሰው ጦርነት እና አሁንም በመካሔድ ላይ ባሉ ግጭቶች ሳቢያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ላይ ጥርስ የነከሱ በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል አይደለም።

መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር መቀመጫቸውን በውጪ ሀገራት ያደረጉ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች ባለፉት ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ሐዋላ ከመደበኛው ሥርዓት ውጪ እንዲሆን ግፊት ሲያደርጉ ታይተዋል።

ዲያስፖራው በሀገሩ አንዳች ሥራ ለማከናወን ሲያቅድ ግንዛቤ ውስጥ የሚያስገባቸው ሌሎች ጉዳዮች መኖራቸውን የሚናገሩት ዶክተር አብዱልመናን የሰላም እጦት፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተንሰራፋው የሰዎች ዕገታ እና የአስተዳደር መበላሸትን የመሳሰሉ ፈተናዎች ብሔራዊ ባንክ ይፋ ባደረገው ዕቅድ ላይ አሉታዊ አንድምታ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW