ሐገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል እስረኞች እንዲፈቱ መጠየቁን
ቅዳሜ፣ መጋቢት 6 2017
የታቀደውን አገራዊ ምክክር በአማራ ክልል ውጤታማ ለማድርግ የአማራ ክልል እስረኞችን እንዲፈታና ሌሎች እርምጃዎችንም እንዲወሰድ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጠየቀ። እስካሁን በአማራ ክልል ሁለት አበይት ሥራዎች ማከናወኑንም ኮሚሽኑ ገልጧል፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰሞኑን በአማራ ክልል ተገኝቶ የኮሚሽኑን ተግባራት በክልሉ እውን ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ ኮሚሽኑ በሰሞኑ ውይይቱ የአማራ ክልል መንግሥት አሁን ካለው የክልሉ የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የታሰሩ ሠዎችን በመፍታት ውይይቱ በአማራ ክልል ተግባራዊ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡ ተመልክቷል።
ይህን ጉዳይ በተመለከት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ለዶይቼ ቬሌ ተጨማሪ አስተያየት ሰጥተዋል።
“... ሁሉ አቀፍ አገራዊ ምክክር ልናደርግ ስለሆን፣ ይህንን ምክንያት በማድረግ ህዝቡም በተከታታይ ስለጠየቀ፣ በህዝብና በመንግሥት መካከል እምነት እንዲፈጠር ስለምንሰራ ህዝቡ ያነሳውን ለነርሱም (ለክልሉ መንግሥት) አነሳን፣ ፍርድ ቤቱ በራሱ ውሳኔ ሊሄድ ይችላል፣ ክልሉም እንደዚሁ፣ ምክክሩ የበለጠ በስኬት እንዲሄድ፣ በተመሳሳይ ደግሞ “ወንድሞቻችን” ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ የቤተሰብ ጥል፣ ጦርነትና ግጭት በመሆኑ እነርሱ ወደ ምክክሩ እንዲመጡ፣ የታሰሩ ወንደሞቻቸን የሚፈቱበትን መንገድ ታመቻችሉን ዘንድ ብለን ጠይቀናል።” ብለዋል፡፡
በባሕር ዳር ቆይታቸው ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን የገለፁት ዶ/ር ዮናስ፣ በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ወገኖችም በውይይት እንደሚያምኑ አመልክተዋል። ምናልባት በአካሄድ ልዩነቶች ሊኖሩ እንደሚችል ጠቁመው ያንንም በመነጋገር ማስተካክል እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
ክልሉ በፀጥታ ችግር ውስጥ ቢሆንም ሁለት አበይት ሥራዎች በስኬት ተጠናቀቀዋል ብለዋል። የመጀመሪያው በክልሉ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን ከየዞኑ፣ ከየወረዳው መምረጠ ሲሆን፣ ሌላው የተከናወነው ተግባር ደግሞ የአጀንዳ መነሻ ሀሳቦችን መሰብሰብ እንደሆኑ ገልጠዋል፡፡ በቅርብ ቀን ደግሞ በክልሉ አጠቃላይ ውይይት ለማድረግ እቅድ መያዙን ዶ/ር ዮናስ አመልክተው ለተግባራዊነቱ ሁሉም ባለድርሻ እንዲተባበርም ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልሉ ለሚያደርጋቸው ማናቸውም ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም እንደተገለፀላቸው ኮሚሽነሩ ገልጠዋል፡፡
አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በዋናንት ሶስት ዓላማዎች እንዳሉት ያብራሩት ዶ/ር ዮናስ፣ አንዱ የምክክር ልምድና ባህል በኢትዮጵያ እንዲዳብር ማድረግ፣ በመንግሥትና በህዝብ መካከል እምነት እንዲፈጠር መስራትና አገራዊ መግባባት እንዲመጣ ማድረግ ናቸው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሰራ ጊዜው የተጠናቀቀ ቢሆንም ቀሪ ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የሥራ ጊዜው ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል፡፡
አለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር