1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ሔማን በቀለ፤ ታይም መፅሄት የመረጠው የዓመቱ ምርጥ ታዳጊ ሳይንቲስት

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 29 2016

ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ሄማን በቀለ በታይም መፅሄት የተመረጠው የቆዳ ካንሰርን ለማከም የሚውል ሳሙና በመስራቱ ነው። ታዳጊው ከዚህ በፊትም ስሪ ኤም 3M የተባለ ኩባንያ ባካሄደው የወጣት ሳይንቲስቶች ውድድር በማሸነፍ 25,000 ዶላር ተሸልሟል።

USA | 3M Young Scientist Challenge | Hamam Bekele
ምስል 3M

ለቆዳ ካንሰር ሳሙና የሰራው ታዳጊ በታይም መፅሄት የዓመቱ ምርጥ ልጅ ሆኖ ተመረጠ

This browser does not support the audio element.

የ15 ዓመቱ ሄማን በቀለ በታይም መጽሔት የዓመቱ ምርጥ ታዳጊ /Kid of the Year /ተብሎ ከሰሞኑ ተመርጧል። አዲስ አበባ የተወለደው እና በአራት ዓመቱ ከወላጆቹ ጋር ወደ አሜሪካ ያቀናው ሄማን፤ ሰሞኑን በታተመው የታይም መጽሔት ሽፋን ላይ የወጣው የቆዳ ካንሰርን ለማከም እና ለመከላከል የሚያስችል ሳሙና በመስራቱ ነው።
አንድ ቀን የእኔ ሳሙና በሌላ ሰው ሕይወት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብሎ ማሰብ በጣም የሚያስደንቅ ነው። የሚለው ሄማን ከዚህ በፊት ለዝግጅት ክፍላችን በሰጠው ቃለ መጠይቅ የሀሳቡ መነሻ የትውልድ ሀገሩ ናት።
«ውልደትና ዕድገቴ ኢትዮጵያ ነው።በርካታ ሰዎች በከባድ ፀሐይ ላይ ለረጅም ሰዐት ሲሰሩ እመለከት ነበር።እያደግኩ ስሄድ ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ እየገባኝ ሄደ።ካንሰርን ለመከላከል  በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በማደግ ላይ ባሉ ሃገሮች ያለው ችግር በዚህ ጉዳይ  በትኩረት እንድሰራና የካንሰር ህክምና ሳሙና እንዳዘጋጅ አድርጎኛል።» በማለት ገልጿል።

የአዳጊው ሳይንቲስት የሄማን ወላጅ እናት ወይዘሮ ሙሉእመቤት ጌታቸው በዚህ የልጃቸው ውጤት ደስተኛ ናቸው። «በጣም ደስ ብሎኛል።እግዚያአብሄር ይመስገን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሀገሬን ማስጠራቱ ደስ ብሎኛል።»ብለዋል።

የምርምሩ መነሻ ሃሳብ 

ሄማን እና ቤተሰቦቹ ኑሯቸውን  ከኢትዮጵያ ፤ አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ሲያደርጉ ብዙ ጌዜ ከቤት ውጭ ያለፀሐይ መከላከያ ወይም ትክክለኛ  ልብስ ሳይለብሱ መውጣት ጉዳት እንዳለው ወላጆቹ ለእሱ፣ ለታላቅ እህቱ ሃሴት እና ለታናሽ እህቱ ሊያ ያስተምሯቸው ነበር። በዚህም ለከባድ ፀሐይ የሚጋለጡ ሰዎች የ«አልትራቫዮሌት» ጨረር በቆዳቸው ላይ ትልቅ ችግር እንደሚያመጣ ተገነዘበ።እናም በልጅነት አእምሮው የሚያስታውሳቸውን ሀገር ቤት በጠራራ ፀሃይ የሚሰሩ የጉልበት ሰራተኞችን አሰበ እና አንድ ነገር መስራት እንዳለበት ማሰላሰል ያዘ።  
ከዕለታት በአንድ ቀን ኢሚኩሞድ/imiquimod/  ስለሚባል የቆዳ ካንሰር መድሃኒት አነበበ። ኢሚኩሞድ ዕጢዎችን ለማጥፋት የሚረዳ እና አብዛኛውን ጊዜ በቅባት መልክ የሚቀርብ መድሃኒት ሲሆን፤ በሀኪሞች ትዕዛዝ ለቆዳ ካንሰር ህክምና  ይውላል። ነገር ግን ሄማን በሽታው ስር ሳይሰድ የመጀመሪያ ደረጃ እያለ  ሰዎች በቀላሉ ሊጠቀሙበት የሚችል ሌላ ቀላል ዘዴ ፈለገና ደረቅ ሳሙና መስራት ጀመረ። 

ከልጅነቱ ጀምሮ ሳሙና በመደበላለቅ መጫወት ይወድ ነበር 

ወላጅ እናቱ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ለወትሮውም ቢሆን ቤት ውስጥ የተለያዩ ፈሳሽ ሳሙናዎችን በመቀላቀል መጫወት ይወድ ነበር ይላሉ።ለዚህም ልጆቻቸው የሚጫወቱበትን ነገር ከመግዛት ይልቅ ራሳቸው እንዲሰሩ ማድረጋቸው ብዙ ነገር እንዲሞክር ዕድል ሰጥቶታል።
«እኛ ያለን አቋም ምንድነው ልጆች ራሳቸው በሚሰሩት ነገር መጫወት አለባቸው የሚል ነው።ከበፊትም ጀምሮ አሻንጉሊት ወይም ዕቃ አንገዛላቸውም።በዚያም የተነሳ ይመስለኛል መፈጣጠር መቀላቀል ይወዳል።በጣም ከማስታውሳቸው ግን በቃ ውሃ ጠጥተን በምንጥለው ላስቲክ ኢትዮጵያ ሀይላንድ በምንለው አልጋው ስር የምናገኘው የዕቃ ሳሙና የላውንደሪ ሳሙና መዓት ነገር ነው ውስጡ የሚጨምረው እና ደባልቆ ይደብቀዋል አልጋው ስር ብዙ ጊዜ።ሽታ ሁሉ ሊፈጥር ይችላል አንዳንድ ጊዜ።ምንድነው የሚለው ምን እንደሚያመጣ ውጤቱን ማየት እፈልጋለሁ ይላል።እና እሱ በቅርብ የምናስታውሰው ነው።በጣም መቀላቀል ይወዳል መደበላለቅ ይወዳል።ያው  ቤቱን ያፈነዳል በሚል ሁል ጊዜ «ቸክ»እናደርጋለን አልጋው ስር።ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ነው።እሱ አንዱ ነገር ነው።» ሲሉ ነበር ወይዘሮ ሙሉእመቤት ያብራሩት።

በዚህ ሁኔታ ቤት ውስጥ የተጀመረው ሳሙና የመስራት ምርምር ባለፈው ጥቅምት ወር ስሪ ኤም 3M የተባለ ኩባንያ ባካሄደው የወጣት ሳይንቲስቶች ውድድር እንዲያሸንፍ አድርጎታል።በውድድሩም 25,000 ዶላር ተሸልሟል።ይህም ምርምሩን በተሻለ ሁኔታ እንዲቀጥል ጥሩ ዕድል ሰጥቶታል።
 ይህ ሳሙና ለአጠቃቀም ቀላል መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለቆዳ ካንሰር ሕክምና የሚወጣውን 40,000 ዶላር በማስቀረት በአነስተኛ ዋጋ ተደራሽ መሆን የሚችልም  ነው።ከዚህ አንፃር የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሀገራት የሄማን ፈጠራ ጥሩ ዜና ነው። 

የሄማን ሳሙና ለቆዳ ካንሰር ሕክምና የሚወጣውን 40,000 ዶላር በማስቀረት በአነስተኛ ዋጋ ተደራሽ መሆን የሚችልም  ነውምስል picture-alliance/dpa/FotoFinder Systems GmbH

በጆን ሆፕኪንስ ብሎምበርግ ቤተሙከራ የቀጠለው ምርምር

የሄማን ሳሙና በተጨባጭ የታቀደለትን ዓላማ ለማሳካት ጊዜ ሊወስድ ይችላል።ሆኖም ግን ሔማን ህልሙን ለማሳካት ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ባሊቲሞር በሚገኘው የጆን ሆፕኪንስ ብሎምበርግ የሕብረተሰብ ጤናትምህርት ቤት ቤተሙከራ ውስጥ ቪቶ ሬቤካ ከተባሉ ረዳት ፕሮፌሰር ጋር ምርምሩን ቀጥሏል።
«አሁን ሳሙናው ቴስት እየተደረገ ነው ያለው።ወደ ሁለት ወር ገደማ ጆንሆፒኪንስ የሚባለው የዩንቨርሲቲው ላብራቶሪ ውስጥ ሪሰርች ሲያደርግ ነበረ።እስካሁን በአይጦች ተሞክሯል።የሚቀጥለው ነገር ምንድነው በሰው ደግሞ  እንደገና ይሞከራል፤ ያው መድሃኒት በአይጥ ብቻ ተሞክሮ አይወጣም ወደ ገበያ። ስለዚህ ቀሪ ምርምሮች ይደረጋሉ።ይቀጥላል ማለት ነው።»ብለዋል ወላጅ እናቱ ወይዘሮ ሙሉ እመቤት።
ወይዘሮ ሙሉእመቤት እንደሚሉት ሄማን፤ በባህሪው ጠያቂ ፣ በትንሽ መልስ የማይረካ፣አንባቢ ፣ራሱን እና የሰራውን ስራ በደንብ መግለፅ እና መተንተን የሚችል ነው። እናም ከወላጆቹ ያላሰለሰ ድጋፍ ባሻገር እዚህ የደረሰው በራሱ ጥረት ነው ይላሉ።
«እዚህ የደረሰበት ጥረት በአብዛኛው የራሱ ነው።ከልጅነቱ ጀምሮ ያው ከዚህ በፊትም ብየዋለሁ ከልጅነቱ ጀምሮ መመራመር ነገሮችን መቀላቀል ይወዳል።ምን አይነት ውጤት እንዳለው ቀጣዩን ነገር ለማወቅ በጣም ይፈልጋል።ብበዛት የራሱ ጥረት አለበት።ያው እንደ ወላጅ ደግሞ እኛ ያደረግነው ነገር ምንድነው ተግቶ የመስራት።በተለይ በተለይ ደግሞ ከሀገራችን ስንወጣ የመጣንበትን ዓላማ በደንብ ማስጨበጥ።የሀገሩ ባህል ሰምጠው እንዳይቀሩ ዓላማቸውን እንዲይዙ እንዳይረሱ ለማድረግ ብዙ ነገር ሰርተናል።በስተጀርባ።ሳይንስ ላይ እኛ ሳይንቲስቶች አይደለንም።እኔም አባቱም ግን በአጠቃላይ ህልም እንዲኖረው ህልሙን ለማሳካት እንቅፋት እንዳይኖርበት አግዘነዋል።»በማለት የሄመን እናት ገልፀዋል።

ሄማን በቀለ ይህ ሳሙና ምርምሩ ተጠናቆ እና በሰፊው ተመርቶ በአነስተኛ ዋጋ ለተጠቃሚ እንዲደርስ ትልቅ ምኞት እና ህልም አለውምርምሩ ተጠናቆ እና በሰፊው ተመርቶ በአነስተኛ ዋጋ ለተጠቃሚ እንዲደርስ ትልቅ ምኞት እና ህልም አለው.ምስል 3M

ልጆችን ውጤታማ ለማድረግ የወላጆች ድጋፍ 

ከዚህ አንፃር ወላጆች የሚፈልጉትን ሳይሆን የልጆችን ዝንባሌ ተከትሎ ማገዝ እና ማበረታታት ልጆችን ውጤታማ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይገልፃሉ። 
«በመጀመሪያ ኢትዮጵያዊነትን በደንብ አስጨብጦ ማሳደግ። እሱ ይቀድማል ከሁሉም።ኢትዮጵያዊነት ለኛ ታታሪነት ነው። ውጤት ማምጣት ነውና እሱ መጀመሪያ ይቀድማል።ሲመጡ አራት ዓመቱ ነበር እንግሊዝኛ አይችልም ነበር።እንደምንም ብሎ ግን እንግሊዥኛ ተምሮ ብዙ ጓደኞችን ማፍራት ችሏል።ያንን «ቫሊዩ»ከያዙ በኋላ ደግሞ ምንድነው ውጤታማ የሚያደርጋቸው ነገር።ስንፈጠር አብሮ የሚፈጠር ነገር አለ።አካባቢው በደንብ ኮትኩቶ የሚያሳድገው ችሎታ ደግሞ አለ።ልጆች ያስታውቃሉ ምን ላይ ዝንባሌ እንዳላቸው።እኛ የምንፈልገውን ሳይሆን እነሱ ያላቸው ጥንካሬ ላይ በደንብ ማገዝ።እኔ አሁን በሄመን ሳይንስ ላይ ነበር።በልጅነቱ ይህንን መቀላቀሉን ሳናይ።በእርግጥ ብዙ ዋጋ ይጠይቃል በሰው ሀገር።»ብለዋል።
ኤስ ሲ ቲ ኤስ/STCS/ የተሰኘው የሄማን ሳሙና ከአሜሪካ የምግብ እና የመድሃኒት አስተዳደር /FDA/ ማረጋገጫ ሲያገኝ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የቆዳ ካንሰርን በደረቅ ሳሙና ለማከም እና ለመከላከል ያስችላል።

የወደፊት ህልም

ከልጅነቱ ጀምሮ ለሳይንስ የተለዬ ፍላጎት እና ፍቅር ያለው፤ የ15 ዓመቱ ተመራማሪ ሄማን በቀለ ይህ ሳሙና  ምርምሩ ተጠናቆ እና በሰፊው ተመርቶ በአነስተኛ ዋጋ ለተጠቃሚ እንዲደርስ ትልቅ ምኞት እና ህልም አለው።ወይዘሮ ሙሉ እመቤት ደግሞ ለልጃቸው ከዚህ ያለፈ ምኞት አላቸው።
«እኔ ጥሩ ዜጋ እንዲሆን እመኛለሁ።ሀገሩን የሚወድ።ለሀገሩ የተለዬ ትኩረት የሚሰጥ።እሱ ያገኘውን እድል ለሌሎች የሚሰጥ።የተለዬ የ«ፕሮፌሽን» ምርጫ የለኝም።ምንም ቢሆን ግድ የለኝም።ብቻ ጥሩ ሰው፣እግዚአብሄርን የሚፈራ፣ ሀገሩን የሚያስታውስ ልጆችን የሚያግዝ ትምህርት ቤት የሚሰራ እንደዚያ አይነት መልካም ልጅ እንዲሆንልኝ ነው የምፈልገው።»ብለዋል።

ፀሐይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW