ሕንድና ቻይና ተሻራኪ ወይስ ተቀናቃኝ
ረቡዕ፣ ጥር 19 2002ከአለም ከፍተኛዉን የሕዝብ ቁጥር የያዙት ቻይና እና ሕንድ የምጣኔ ሐብት እድገታቸዉ አሁን ባለዉ እድገቱ ከቀጠለ ምናልባት የአለም ትልቅ ኢኮኖሚ ሊሆኑ ይችላሉ።ሕንድ ዲሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥቷን ያፀደቀችበትን 60ኛ አመት ዛሬ ስታከብር አምባገናናዊቷን ጎረቤትዋን ቻይናን እንደ ተቀናቃኝ ታያት ይሆን? ወይስ በፈጣን እድገት ላይ የሚገኙት ሁለት የእስያ ግዙፎች በአለም ላይ የራሳቸዉን ማሕተም ለማሳረፍ በጋራ መስራት ይችሉ ይሆን? ቶማስ ቤርትላይን የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።
እየፋፋ እየጠረቃ እየዳጎሠ የመጣዉ የቻይና እና የሕንድ አቅም የምዕራቡን ትኩረት ከሰባ ዉሎ አደረ።ሁለቱ የእስያ ፈርጣማ ሐገራት አንዳዴ «ቻንዲያ» በሚል የወል ሥም እንደ አዲስ ልዕለ-ሐያል ይታያሉ።ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱ ሌላዉን ለመብለጥ የሚፎካከሩ የእስያ ተቀናቃኞች ተደርገዉ ይገለጣሉ።
እዉነታዉ ግን በርግጥ ብዙም የሚጋነን አይደለም።ሁለቱም የየራሳቸዉ ጉድለት አላቸዉ።ሁለቱ መንግሥታት በአለም አቀፍ ጉዳዮች ብዙ ጊዜ በቅርብ ተባብረዉ ይሠራሉ።የአዋሳኝ ድንበራቸዉን የመሳሰሉ የሁለትሽ ችግሮቻቸዉን በጋራ ለመፍታት እንደሚጥሩ ይናገራሉ።የዚያኑ ያክል፥ በጃዋሐራላል ኔሒሩ ዩኒቨርስቲ የሕንድና የቻይና ግንኙነት ባለሙያ አልካ አቻርያ እንደሚሉት ከትብብራቸዉ ይልቅ ልዩነታቸዉ ደምቆ ይታያል።
«በሁለቱ ሐገሮች መካካል ብዙ አለመተማመን አለ።አለመተማመኑ ታሪካዊ ምክንያት አለዉ።ይሕ ሲተረጎም ሁለቱ ሐገሮች በቅርብ ተባብረዉ መስራት እንዳይችሉ አድርጓል።ምክንያቱም በመካከላቸዉ ፉክክር አለ።ያኛዉ ወገን ሥለሚያስበዉ ግን በትክክል አናዉቅም።»
የሕንድ ምክር ቤት ጥናት ለአለም አቀፍ የምጣኔ ሐብት ግንኙነት በተሰኘዉ ተቋም የቻይና ጉዳይ አዋቂ ራጂቭ አናንታራም ደግሞ ከዚሕም እልፍ ብለዉ ቻይኖች በሕንዶችን እንደ ተቀናቃኝ ነዉ-የሚያዩት ባይ ናቸዉ።
«ምንም አያጠራጥርም።የፈለገዉን ቢናገሩም እኛን የሚያዩን እንደተፎካካሪ ነዉ።ቅምጥ ሐብት ለመቆጣጠር በመልካዓ ምድራዊ ሥልታዊነት ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ እንፎካከራለን።»
ሕንድ በምጣኔ ሐብት እድገት ቻይናን በጥቂት አመታት ዉስጥ ለመብለጥ መመኘቷ አልቀረም። በተጨባጭ ግን ባለፉት አስርታት ከቻይና ብዙ ወደ ኋላ እንደቀረች ነዉ።ሕንዶች የልዩነቱ ምክንያት በቻይና ጠንካራ ሥርዓት ላይ የተመሠረዉ ዉልፍጥ የማይል የመሪዎች ዉሳኔ ነዉ-ይላሉ።እንደገና አቻርያ
«ነገሮችን በፍጥነት ያከናዉናሉ።ዉሳኔዎች በየደረጃዉ ተቃዉሞ አይገጥማቸዉም። አይታጎሉምም። ዉሳኔዎችን ከላይ እስከታች ለማስፈፀም በጣም ዉጤታማ ናቸዉ።»
ሕንድ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓቷ ትኮራለች።በምጣኔ ሐብቱ እድገት ግን በቻይና ዉጤት ትቀናለች።
«የዉጪ ባለሐብቶች ወደ ሕንድ አይመጡም።ምክንያቱም እኛ ዲሞክራሲያዉያን ነን።ወደ ቻይና ነዉ-የሚሔዱት።ምክንያቱም በግልፅ እንደሚታወቀዉ የካፒታል ዝዉዉር ከዲሞክራሲያዊቷ ሕንድ ይልቅ ቁጥጥር በሚደረግባት ቻይና አስተማማኝ ነዉና።»
በጣሙን በሥልታዊና በወታደራዊ መስኮች ነገሮች በተደጋጋሚ እንደተጋጋሙ ነዉ።ሕንዶች በተደጋጋሚ ቻይና ታሰጋናለች ይላሉ።ሕንድ የኑክሌር ቦምብ ከመታጠቅ የባሕር ሐይሏን በዘመናዊ መልክ እስከ ማደራጀት ለደረሰዉ የጦር ዝግጅቷ ከቻይና ሊሰነዘር የሚችል የምትለዉን ሥጋት ምክንያት ታደርገዋለች።
ሁለቱ ሐገሮች እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ1962 ላጭር ጊዜ ባደረጉት ዉጊያ ቻይና ሕንድ ክፉኛ መምታትዋ ከሕንዶች አዕምሮ አልጠፋም።የፖለቲካ አዋቂ አናንታራም ግን ተፎካካሪ ማለት ጠላት ማለት አይደለም።
«አመታት ያስቆጠረ አለመተማመን አለ ማለት ወዳጆች መሆን አልቻልንም ማለት ነዉ።ነገር ግን ተቀናቃኝ ማለት ደመኛ ማለትም አይደለም።እና ጠላቶች መሆን አያሻንም።»
ቶማስ ቤርተላይን
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ